Tidarfelagi.com

የወንዶች ዓለም!

እንደ መፀሐፉ፣ እንደ ዘፍጥረት ቃል፣
የሰው ዘር መፈጠር፣ በአዳም ይጀምራል- ከአዳም ይለጥቃል፣
የአዳምን ብቻነት፣ አምላክ አስተዋለ፣
ረዳት እንድትሆን፣ ከገዛ አጥንቱ፣ “ሴት ብፈጥርስ” አለ፡፡

እዚህ ጋ፣ አስተውሉ፤ እግዜር ለሴት ብሎ፣ አፈር አላቦካም፣
ከአዳም ተስተካካይ፣ ጊዜን አልወሰደም፣
ብቻ ከግራ አጥንቱ፣ ወሰደ ፈጠራት
ለምን እንደሁ እንጃ፣ ጊዜን የነፈጋት፡፡

አዳምን ለመስራት፣ ጥሬ እቃ አስፈለገ፣ “አፈር” የተባለ፣
ሴትን ግን ለመፍጠር፣ እግዜር ምን አለፋው፣ የተሰራ እያለ?

የአዳም አጥንት እንጂ ቅርፁን የቀየረ፣
በስም`ንጂ በግብር፣ ሴት መች ተፈጠረ
ይህችን ለአፅኖት፣ አንድ`ዜ ልድገማት፣
ወንድ እንጂ መልክ የቀየረ፣
ሴት ይሉት መች ተፈጠረ?

ሩዝን ፈጭተውት ቢያደርጉት እንጀራ
ወይ ቅርፁን ሳይለውጥ፣እንዳለ ቢሰራ
በሩዝነቱ ላይ፣ አይኖርም ቅየራ፡፡
…በሶን ግማሽ ከፍሎ፣ አንዱ ቢበጠበጥ፣
ሌላኛው ቢጨበጥ
አንደኛውን በጭብጥ፣ ሌላኛውን በብጥብጥ
ቢጠራ ነው እንጂ፣ በሶነቱ አይለውጥ፡፡
ስንዴን በመጠቀም፣
ከፊሉን በፓስታ፣ ሌላኛውን ዳቦ፣ አርገኝ ብናበጃጅ፤
ዳቦ፣ ፓስታ የሚል፣ ልያት ስም ቢዘጋጅ
ስንዴ ነው ዘራቸው፣ ስንዴ ነው ነብሳቸው፡፡

እንዲህ ነው የሴትም ውል አፈጣጠሯ፣
ከቀደመ ነገር መልክ የመቀየሯ
ይሄ ነው ሚስጥሩ፣
ሴት በሚል መጠሪያ፣ ከወንድ አጥንት ላይ ወንድ የመፈጠሩ፡፡
ይልቅስ ወንዱ ነው፣ ከልብ የሚያሳዝን
አንድ አጥንቴ ብሎ፣ ለራሱ `ሚባዝን፡፡
ለወንዱ ነው ማዘን፣
ትዳር ከምትባል፣ ትንስ ዛኒጋባ
ሴት ነች ብሎ አስቦ፣ ወንድን ለሚያገባ፡፡

ማዘንስ ለወንዱ፣
ቅርፅ ከለወጠች፣ ካልተፈጠረች ሴት
ዘር ልቀጥል በሚል፣ ወንዶችን መውለዱ- ወንድ ማስወለዱ፡፡
ሴት ይሏትም ወንዷ፣
ደርሶ መጃጃሏ
ወንድ አይደለሁኝም ብላ መታለሏ
– ቢለወጥ አካሏ፡፡

እና ማነሽ አንቺ?
“የሴት እኩልነት” ይሉት ውድቅ ተረት የምትተርቺ፣
አንዱ አጥንት ከሌሎች፣ ካልበለጠ ብለሽ የምትሞግቺ
ፊት ለፊት ነው ሃቁ፣ ያልተሸፋፈነ፣ ያልተቀላቀለ፤
ማስተዋል ለሰጠው፣ ማየት ለታደለ

ዓለም ሴት የሚሉት በስም እንደሁ እንጂ፣
ለይታ ፈጥራቸው አላየም፣ ዐይናችን
ዓለም የወንዶች ናት፣ ወንድ ነን ሁላችን፡፡

One Comment

  • najib commented on May 13, 2015 Reply

    ምርጥ ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *