Tidarfelagi.com

የዚህ ትውልድ አባል ነኝ!

በመውደድ ወይ በመጥላት አልፍቀውም። ያለፈው ትውልድ ውላጅ ነኝ። የመጪው ትውልድ ወላጅ ነኝ።

ያለፈው ትውልድ “አዬ ልጅ” እያለ ያሾፍብኛል፤ መጪው ትውልድ ይኮርጅኛል( ወደፊት “አይ አባት” ብሎ ይስቅብኝ ይሆናል -ግድ አይሰጠኝም)

ለሁሉ ፈጣን ነኝ። ሁሉን በፍጥነት አይቼ በፍጥነት አልፋለሁ። ችክ ማለት አልወድም። ሌሎች ግልብ ነህ ይሉኛል፤ እኔ ፈጣን ነኝ እላለሁ።

የነገሩኝን አምናለሁ። ላመንኩት እጮሃለሁ። መውደድና አድናቆት ይምታታብኛል። ያደነኩትን እወዳለሁ። ለወደድኩት ታማኝ ነኝ። የወደድኩትን የጠላ ጠላቴ ነው። የምወደውን የወደደ ወዳጄ ነው። የወደድኩትን ድርጅት በክፋ ዐይን ላየ እከፋለሁ(ይህን ይወቅ)
የጠላሁትን ለወደደ የተከፈተ ልብ የለኝም። የሆነ አዕምሯዊ ጤንነት የሚጎድለው ይመስለኛል፤ ጤነኝነቱን እጠራጠራለሁ።

ሃሳቤን በጩኸት ማስረዳት ይቀናኛል። የሃሳብ ልዩነትና የግል ጠብ ይምታታብኛል። በአስተሳሰቡ የተለየኝንም በግል የተጣላኝንም እኩል እሰድባለሁ።
የዚህ ትውልድ አባል ነኝ። በዙሪያዬ ካሉት አብዛኞቹ ይመስሉኛል።
የማይመስሉኝም አሉ።

ተከታይ ነኝ። ለመመርመር ጊዜ የለኝም (ፈጣን ነኝ አላልኳችሁም?) በፍጥነት እከተላለሁ። ጥለውኝ እንዳይሄዱ፣ የያዝኩትን ጥዬ እከተላለሁ። ጊዜ የለኝም! (ለመከተል የማይደክም ብርቱ እግር ግን አለኝ)
ሰዎች በሄዱበት መንገድ እሄዳለሁ። ያልተሄደበት መንገድ ያስፈራኛል። የዘህ ትውልድ አባል ነኝ። የሚመስሉኝ ይበዛሉ፤ በዚህም ደስ ይለኛል።

ባህሌን የማይካፈል፣ ቋንቋዬን የማይናገር፣ ያልታወቀ ህመም ያለበት ይመስለኛል። በታሪክ እጣላለሁ፤ የተጣላሁትን እጠላለሁ። ቋንቃ መግባቢያ ነው ሲሉኝ እስቃለሁ። መጣያም እንደሆነ በማሳየት ስህተታውን እነግራለሁ። ታሪክ ካለፉ ስህተቶች መማሪያ ነው ሲሉኝ እደነቃለሁ። በታሪክ ስህተት እየሰራሁ ለስህተትም እንደሚውል አሳያለሁ፤ በዛውም አዲስ ታሪክ እሰራለሁ። ከላይ ሲያዩኝ ዓለማቀፋዊ እመስላለሁ፤ገልጠው ሲያዩኝ ሰፈር ዓቀፋዊ እሆናለሁ።

ከእርቃን ተባዕት ልቤ በላይ፣ እርቃን የሴት ገላ ያስቆጣኛል ( ባህሌን ያስብለኛል)
የዚህ ትውልድ አባል ነኝ።
የማይመስሉኝ ያናዱኛል።

ውሳኔ ይቀናኛል። የውሳኔዬ ምክንያት አያሳስበኝም። ከኋላ ሆኜ፣ “ወደ ፊት ” እላለሁ። “ለምን ከኋላ ሆንክ?”ሲሉኝ፣
” ማንም እንዳልቀረ ለማረጋገጥ። ” እላለሁ። ቅደሙ ስል እንጂ፣ ቅደም ሲሉኝ አልወድም( በጎ አስበው ቅደም ያሉ አይመስለኝም። ጠርጣሪ ነኝ። “ያልጠረጠረ …” ) የቀደን ለመለከተል ግን ፍቃደኛ ነኝ― ከሰኞ እስከ ሰኞ፣ ከሰኔ እስከ ሰኔ!

የዚህ ትውልድ አባል ነኝ። እንዲህ የሆንኩት የዚህ ትውልድ አባል ስለሆንኩ ነው ብዬ አላምንም። ግን ማነህ ሲሉኝ የዚህ ትውልድ አባል ነኝ እላለሁ።
ቀደምቶቼ ከኔ የተሻሉ አልነበሩም። ልጆቼ ከኔ ላለመባሳቸው ማስረጃ የለኝም።

“ለምን አታነብም ” ሲሉኝ፣
“ለዐይኔ ደኸንነት ስል ” ብያለሁ( ይህን ስል ዐይኔ ጌም የምጫወትበት ሞባይል ላይ ተተክሎ ነበር)
በመልሴ ስቀዋል። በመሳቃቸው ስቄያለሁ።

ጭንቀት አልወድም። ሳተኩር ይጨንቀኛል። አንድ ነገር ደጋግሞ ማድረግ ይጨንቀኛል።
በሚተቹኝ እስቃለሁ። አለማወቄን ለሚተቹ፣ በማወቃቸው እሳለቃለሁ። ሲያዝኑብኝ አዝንላቸዋለሁ።
የዚህ ትውልድ አባል ነኝ።
ብዙ የሚመስሉኝ አሉ (ስወዳቸው)
የማይመስሉኝም አሉ (ስጠላቸው)
እንዲህ የሆንኩት የዚህ ትውልድ አባል ስለሆንኩ ነው ብዬ አላምንም።
ቢሆንም ባይሆንም፣ “ማነህ” ሲሉኝ፣
የዚህ ትውልድ አባል ነኝ እላለሁ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *