«ወንድ ልጅ አይደለህ እንዴ? እንዴት ፖለቲካ አትወድም?» ብላኝ አረፈችው። እሰይ!
«እዚህ ሀገር ከፖለቲካ ጋር ያልተነካካ ብቸኛ ገለልተኛ አካል የኔ አክሱም ነው። ተያ!…… የፓርላማ ጭብጨባ ካልሰማሁ አልቆምም ብሎ አያውቅም። አያደርገውም! እዝህች ሀገር ላይ ሰላማዊ ሰልፍ በረደ ብሎ ለግሞብኝም አያውቅም። ሽለላ ቀረርቶ ካልተደረደረልኝ አልዋጋም ወጥቶት አያውቅም። ተያ አታነካኪው! »
ትስቃለች። ውብ እኮ ናት ደሞ። የሆነማ ከሰማየ ሰማያት የተወረወረች መልአክ ነገርማ ናት። ሲመስለኝ እዛም አምልኮውን ፖለቲካዊ ይዘት አላብሳበት ፣ የሉሲፈር ከሰማይ አወራወር ታሪካዊ ዳራ ሲጣራ……… ምንምን በሚል ታሪካዊ ትንተናዋ ነዝንዛው ፣ የቅዱስ ገብርኤል ወግ አጥባባቂነት እና የቅዱስ ሚካኤል ለዘብተኝነት የሰማየ ሰማያቱን ህግ የሚፃረርና የተቀረነውን መልአክት ምልከታ ከግምት ውስጥ ያላስገባ… ምናምን ምናምን……… እያለች ስታውከው ፈጣሪም ምን ባደርግ ይሻላል ብሎ አይኑን ቦዘዝ አድርጎ እንደማሰብ እያለ ሳለ የቦዘዙት አይኖቹ ኢትዮጵያ ላይ እርፍ! ፈገግ ያለ ይመስለኛል። መልአክቱን ግራ እንዳጋባሽ ግራ ተጋቢ ብሎ ውርውር!
«የምሬን ነው! ሀገሪቷ ባለችበት የለውጥ ሂደት ትኩሳት ሁሉም እንደዜጋ የራሱን አስተዋፅኦ ማበርከት አለበት። ብረትን መቀጥቀጥ እንደጋለ ነው።» እያለችኝ ግለቱ ተሰምምቷት ይሁን ባልገባኝ ምክንያት የሸሚዟን ቁልፎች እስከ እንብርቷ ድረስ ከፈተችው።
ልመልስላት የነበረው እኮ <ከዚህ አባባል ውስጥ ይሄ ትውልድ ምን የምትለዋን ወሰደ? <መቀጥቀጥ> ጎሽ! እንደጋለ ድው ድው ድው……… አካፋ ሊሰራ አቅዶ የነበረው ቆንጨራ ፣ ማጭድ ያሰበው ጩቤ ብቻ ምን አለፋሽ መቀጥቀጥ ነው…… ትንንሽ ብትንታኝ እስኪሆን መቀጥቀጥ።> ግን ያሰብኩት ከአፌ ከመውጣቱ በፊት ሲጋራዋን ለኮሰችው……
«በአሁኑ ሰአት ከሀገሪቷ የነውጥ ማለቴ የለውጥ ትኩሳት ይልቅ የራሴ ትኩሳት እያነደደኝ ነው።» አልኳት በአንዴ ስበት ግማሽ ያደረሰችለትን የሲጋራ ጭስ ለሰከንዶች አፍዋ ውስጥ ይሁን ሳንባዋ ወይ ጉሮሮዋ ውስጥ እርግጠኛ ያልሆንኩበት ቦታ አቆይታው በዝግታ በቀይ ሊፒስቲክ የደመቁ ከንፈሮቿን ለቆ አየሩ ውስጥ ሲመሰግ እሷ ትዝብት ባዘሉ አይኖቿ ትዳስሰኛለች። ክፋቷ ታውቃለች ጭሷ እብደቴን እንደሚጠራው ሆነ ብላ ይመስለኛል በቄንጥ ከጭሱ ጋር የምትጫወተው ።
«የሆነኛውን የፖለቲካ አቋም ወይ ፅንፍ መያዝ አለብህ።» ይሄኔ ነዋ መሸሽ!
አንዳንዱ ሰው ግን ዝም ሲል ምነኛ ውብ ነው? የዝምታዋን ውበት ለመታደም ከንፈሮቿን ሳምኳቸው።በእጇ የያዘችውን ቀሪ የሲጋራ ቁራጭ ተቀብዬ አሽትሬው ላይ እያጠፋሁ
«ማሬዋ የግድ አቋም ያዝ ካልሽኝ ካንቺ ተክለ አቋም በላይ ገዢ አቋም እዚህ ሀገር ላይ መች ተፈጥሮ ያውቅና ……. ያዝኩኝ።» አልኳት መክፈት ጀምራ የነበረውን የሸሚዟን ቁልፎች እያገዝኳት።
«ፅንፍ መያዝ አለብህ ካልሽኝም በአሁኑ ሰአት የአልጋውን መሀከልኛ ፅንፍ ፤ የሶፋው የሆነኛ ጽንፍ…… አይ ካልሽ የቤቱን ኮሪደርኛ ፅንፍ…… ካንቺ ጋር ይሁን እንጂ ሁሉም ፅንፍ ይመቸኛል። » ትፍነከነካለች። አሁን በሚያግባባን ቋንቋ አወራሁላት መሰለኝ ራሷ የሶፋውን ፅንፍ አስደገፈችኝ ። እንዲህ ነው እንጂ መፀነፍ ። ከሆነኛው አቋቋማችን በኋላ መቀጠል አቃተኝ። እየደጋገመች የኔ ያልሆነ ስም ስትጠራ ማን ተንቀዥቀዥ እንዳለኝ ማነው? ማለቴ…… እሷስ አለማፈሯ
«ባሌ ነው » ማለት…
«ላጭስልህ?» ትለኛለች ደግሞ አጭሳኝ ስታበቃ
«አይደለም ሲጋራ ከርቤ ብታጨሺ ከአሁን በኃላ አይቆምልኝም።»
እናንተ ደግሞ በዚህ ሰአት የኔ አክሱምና የጪስ ቁርኝት ይጠየዋል? ወይ አንባቢ መሆን? ሶስት ወር ያለመታከት ዴት ያደረግኳት ሴትኮ ናት።
«በህግ አልተፋታንም እንጂኮ ጥሎኝ ከሄደ ወራት አልፈውታል። » የምትለኝ ዛሬ ላይ።
የሚገርመኝ ደግሞ ሴቶቹ አብረውኝ ከሰነበቱ በኋላ አግብቻለሁ ወይም ፍቅረኛ አለኝ የሚሉኝ ምን እያሰቡ ነው? የዝህች ደግሞ ይባስ ሶስት ወር ሙሉ ከድንጋይ ዘመን ጀምሮ ያለ ታሪክ ስትተርክልኝ ፤ ያን ሁላ የፖለቲካ ጥናት ከየት ወዴት ስትዘረዝርልኝ ውልብ ያላለላት ባሏ እቤቴ እራት ጋብዣት ከተዋደቅን ኋላ ነው የምታፈርጠው? በጀርባዬ ተንጋልዬ እያሰብኩ እሷ ምን አለባት እንቅልፍ ወሰዳት። ቀስ ብዬ ቤቴን ትቼላት ወጣሁ።
«እኔ እኮ ችግሬ የምታሻፍደኝ ሴት ለትዳር የምመኛት አትሆንም ለትዳር የምመኛት ሴት ደግሞ አታሻፍደኝም። በስህተት……… »
«…… በስህተት ሁለቱንም ያጠናቀቀች ከገጠመችህ ወይ አግብታለች ወይ ደግሞ ፍቅረኛ አላት። ባለትዳር ናት?» ይህቺ ደግሞ የማወራውን የምትቀማኝ ነገር አላት። አሚ ናት!!
«ይህችኛዋማ አግብታለችም አላገባችምም! »
«እሺ ወደቤት ግባና ታወራኛለህ። በመድሃንያለም ምን ሆነክ ነው ዝግዛግ እስክትረግጥ ያንቃረርከው በናትህ? ድምፅህን ቀንስ እዛ… ጋሼ ገና አሁን ነው መኝታ ቤት የገባው»
ሁሌም እንደምታደርገው እጄን እየጎተተች ክፍሌ ወሰደችኝ።
«እንደው ፖለቲካ ወዳድነቷ ትንሽ በዛ እንጂ ፍፁም ሆና ለኔ የተሰራች እኮ ነበረች በናትሽ»
«ያቺ ባለፈው ፍቅረኛዬ ከውጪ መጣ ያለችህንም እኮ እንደሱ ነበር ያልከኝ።ሃሃሃ አሮኔ ደግሞ ፈጣሪ ስንቷን ነው ላንተ ፍፁም አድርጎ የሰራው?»
«ማሾፍሽ ነው? ማትረቢ!»
«እሺ ይህቺኛዋ ደግሞ ምን ሆነች?»
«ከወራት በፊት ጥሏት የሄደ ባሏን ከአፏ አትነጥለውም። ነቅላ ነው የምታፈቅረው።»
«እና?»
«እናማ እሱ እቤቱ ተጋድሞ እኔ አልፈጋለትም። እኔ አቅሌን ስቼ እያላብኩ የሱን ስም ነው የምትጠራው እኮ ነው የምልሽ! በራሴ ጦርነትማ እሱ ጀግና አይባላትም።»
«ሃሃሃሃሃ እና ?» እያላገጠችብኝ ጫማዬን ታወላልቃለች።
«አያስቅም እሺ! እኔ ደሞ ቂሎ ስትመሳሰጥ <ይሄ ነው ወንዱ ይህቺን የመሰለች ልጅ አቀላለጥክ ብዬ መንቀባረሬ > አጅሪትኮ literally ከሱጋ ነው ፍቅር እየሰራች ያለችው። »
በስካር ግልውጅናዬ ማስላት ከማልችለው ደቂቃ ወይ ሰአት እና ግማሽ ከሰማችኝና ግማሽ ካልሰማችኝ ልፍለፋዬ በኋላ እንቅልፍ ወሰደኝ። የስልኬ ጥሪ ነው የቀሰቀሰኝ… ከንጋቱ 11:30… ልብሴ ወላልቆ በፓንቴና በቲሸርቴ ነው የነቃሁት። አሚ! ሞቼ ነበር? ልብሴን እንዳወለቀችልኝ እንኳን አላስታውስም!
«ሄሎ? »
«ብልግና አይደል? ሴት ልጅ እቤትህ ጋብዘህ ጥለሃት ትሄዳለህ?… »
«ይቅርታ ማሬ ዛሬ የወንድሜ ሙት ዓመት ነው። እቤት ማደር ነበረብኝ።» ውሸቴን አይደለም። የወንድሜ ሙት ዓመት መሆኑ እውነት ነው። ቤቴን ትቼላት እናቴ ቤት ያደርኩበት ምክንያት ግን እሷው ነች… ያው አይባልምኣ
«ውይይይይ ታዲያ አትነግረኝም ነበር? »
«ያስታወስኩት አንቺ እንቅልፍ ከወሰደሽ በኋላ ነው።… » ቡፍ የሚል ሳቅ ሰምቼ አይኔን ገለጥኩ። አሚ ናት።
«አንቺ ደግሞ አትተኚም እንዴ? »አልኳት ስልኩን እንደዘጋሁ
«የስልክህ ጩኸት በየት በኩል ያስተኛል? » ትበለኝ እንጂ ጭራሹኑ እንዳልተኛች ያስታውቅባታል። አልቅሳለች።
«ነይ እስኪ! » አልኳት እየተጠጋሁላት። በሩን ዘግታው አጠገቤ ተጋደመች።
«ታወሪኛለሽ? »
«ምንም የማታውቀው ነገርኮ የለም።»
«አሚዬ አስር ዓመት…አስር ድፍን ዓመት… አምና ቃል ገብተሽልኝ ነበር። ሁለተኛ አላለቅስም ብለሽኝ ነበር።»
«አልቻልኩማ! » ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት እሱን ባሰበች ቁጥር እንደተንሰቀሰቀችው ተንሰቀሰቀች።
አሚ እህቴ ናት። እህት የለኝም! በደም ባንገመድም አሚ እህቴ ናት… የብቸኛ ወንድሜ ሚስት… የሟች ወንድሜ ሚስት… እንደእውነቱ አልተጋቡም ነበር።…… እሱ ሲሞት የሱን ልጅ በሆዷ ተሸክማ ነበር።… እኛ ቤት መጥታ ወለደች…… 18 ዓመቷ ነበር። እነእማዬ ልጄ ይሏታል…… እሷም እኔ እንደምጠራቸው ጋሼ እና እማዬ ትላቸዋለች።…
……… የልጇን አባት የገደለው አባቷ ነው።… በሌላ ቋንቋ ወንድሜን የገደለው የሷ አባት ነው። አስር ዓመት ሙሉ ከኛ ሌላ ቤተሰብ የላትም።………
2 Comments
አረ ሜሪዬ እስከ መቼ እንታገስ ቀጥዪው እንጂ
ይቀጥል