Tidarfelagi.com

ይሰለቻል

በመጀመሪያ እግዜር ብቻውን ነበር። ብቸኝ ት ሰለቸው። ብቸኝነት ሰለቸውና ዓለምን ፈጠረ። የፈጠረውን አይቶ ደስ አላለውም፣ ሰለቸው እንጂ። የሰለቸውን ዓለም ትቶ ሌላ አዲስ ነገር ፍለጋ ሄደ። ዓለምም ከዛን ወዲህ መሰልቸት ወለል ላይ ሆና የአምላኳን መምጣት በጥፍሯ ቆማ ትጠብቃለች። እኔ የዓለም አካል ነኝ። ቶሎ ይሰለቸኛል። ሁሉ ይሰለቸኛል። ያልተፈጠረ ብቸኛ ነገር ቢኖር የማይሰለች ነው። የተፈጠረ ሁሉ ይሰለቻል። የማይሰለች ወይም የማይሰለቸው አልተፈጠረም። የሚሰለቹ ሕያዋን ናቸው። የማይሰለቹ ግን አፈሩን ገለባ ያድርግላቸው።

ስወለድ እንደማንኛውም ህፃን አለቀስኩ። እያለቀስኩ ማልቀስ ስለሰለቸኝ መሳቅ ጀመርኩ ። ግን መሳቁም ስለሰለቸኝ ከቆይታ በኋላ መሳቅም ሰልችቶኝ ማልቀስ ጀመርኩ። እስከዛሬም እንደፊልም ተዋናይ አንዴ እየሳኩ አንዴ እያለቀስኩ አለሁ። ሁለቱም ግን ይሰለቻሉ። ሕይወት ደግሞ አንደ አምባገነን መንግስት ምርጫ አትወድም።

**************************

ይሰለቸኛል። ማንኛውም ነገር እንደአፍሪካ መሪዎች የስልጣን ዕድሜ ከረዘመ ራሴን ያዞረኛል። እኔ ራሴም ስልችቱን ሽሽት እንደ ሎተሪ እዞራለሁ። ሰማይ አይሰለችም? ሰዎች አድማስ እያዩ ትዝታ ይፈትላሉ፣ ለኔ መታከት እና መሰልቸትን ብቻ ነው የሚያዳውረው።

ባለስልጣኖች ለምን እንደማይሰለቻቸው ይገርመኛል። በየቀኑ ሲዋሹ፣ በየቀኑ በከረባት ሲታነቁ፣ በየቀኑ በአጀብ ሲንቀሳቀሱ …ኡፍፍፍ ለነሱ ሰለቸኝ። እብድ ነው ማይሰለቸው። እብድ እብደቱ ይሰለቸዋል? ባለስልጣኖች እብዶች ይመስሉኛል። ፀዓዳ ልብስ የሚለብሱ ወፈፌዎች። የማይሰለቻቸው ወይ እብዶች ናቸው፣ ወይ ባለስልጣኖች ናቸው፣ ወይ በሕይወት የሉም። ስላላበድኩ፣ በዘሬ ባለስልጣን ኖሮ ስለማያውቅ፣ በሕይወት ስላለሁ ይሰለቸኛል።

አሁን ባለፈው ፍቅረኛዬን እንዲህ አልኳት፣
“ረም ጊዜ አብረን ቆይተን ከምንስለቻች ለተወሰነ ጊዜ እንለያይ”
እብዱ ሆነች! (እብድ ደግሞ አይሰለቸውም አላልኳችሁም?)
እያለቀሰች፣
“ደደብ ነህ ፍቅር የማይገባህ! ዘወትር አቧራ ፍልስፍና እያቦነንክ የምትኖር ከንቱ…. ቢገባህ ፍቅር አይሰለችም። በፍቅሬ ያሾፍቅበት ቀን….” በመሃል እሷን ማድመጥ ስለሰለቸኝ ከዚህ በኋላ ያለችውን አልሰማሁም። በዛው ተለያየን። ቆይቶ ግን ብቸኝነት ሰለቸኝ። ፍቅሬ ጋር ሄድኩ። “ዓይንህን እንዳላይ” አለችኝ ( ዐይኔ ላይ አፍጣ እኮ ነው ሊያውም!) ለቀናት ተመላለስኩ፣ ተለማመጥኳት። ልክ ፍቃደኛ ሆና ግንኙነታችንን እንድንቀጥል ስትስማማ ግን እሷን መለማመጥ ሰልችቶኝ ነበር።

ሰው ሰው መሆን አይሰለቸውም? መላዕክት መላዕክት መሆን አይሰለቻቸውም። ሴጣን ሁሌ ሴጣን መሆን አይሰለቸውም? ሴታን ግን ይሰለቸዋል መሰለኝ። ስለሰለቸው ነው በእግዜር ዙፋን ላይ ያመፀው። እግዜር ግን እግዜር መሆን ስላልሰለቸው ወይም ስለማይሰለቸው ቁልቁል ጣለው። ሴጣንም ከኛ ተስማምቶ ይኖራል። ( ነው ዕኛ ከሱ ተስማምተን?)

ይሄን መፃፍም እየሰለቸኝ ነው። ይሄ ፅሁፍያ ልገባው ማንኛውም ሰው ቢያንስ መሰላቸት ከፈጠረበት ዓላማውን በትልቁ መቷል( ባጭሩ… በረጅሙም የፅሁፉ ዓላማ መሰላቸትን መፍጠር ነው)

ትንሽ ቆይቶ መሰልቸት ከለቀቀኝ ልቀጥለው እችላለሁ።
የናንተው ስልቹ አሰልቺ!

One Comment

  • ሠለሞን መኮንን commented on August 5, 2019 Reply

    ያንተን ፅሁፍ ማንበብ መቼም አይሰለችም ማለትም ግቡን አልመታም፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *