የመሲሁ ስቅየት
ግርፊያ ስቅላቱ
አምላክ ነኝ ስላለ
በድምቀት ተሳለ
የኛንስ ስቅላት ማነው ያስተዋለ?
ተመልካች ጠፍቶ እንጂ ዐይን የሚቸረን
እኛም መስቀል ላይ ነን፣ ቄሳራዊ ሚስማር ዘልቆ የቸነከረን
ዘውትር ዱላ እና አሳር
ዘውትር ችንካር ሚስማር
የሚገዘግዘን የሚጠዘጥዘን
እኛም ክርስቶስ ነን!
ሺ ዱላ ሺ ግርፊያ
ጀርባችን ላይ ያርፋል
“ስቀለው” የሚል ድምፅ በጆሯችን ያልፋል
ባደባባይ መሀል ልብሳችን ተገፎ
ሲያዙት በሚታዘዝ ጀርባችን ተገርፎ
ስንቶች ተሳለቁ; ስንቶቹ ተፉብን
ዕርቃን ገላችን ፊት ዕጣ ተጣለብን!
ዕዩት ይህን ሀገር ይህን ጎለጎታ
ስንት ዓይነት ሰሪ እጅ በምስማር ተመታ!
ዕዩት ይህን ሀገር አጉል ተቸንክሯል
“ለምን ተውከኝ” ብሎ ጌታውን ይጣራል
ወዲያ ቄሳር አለ፣
ሰቃይ እየላከ ስንቱን የሰቀለ
ከወዲህ ሰቆቃ
ዘመነ-ቄሳሩ ጨርሶ እስኪያበቃ!
እዩን መስቀሉ ላይ
ተሸክመን ስቃይ
አታምኑ እንደሁ ዳሱ
ከእጃችሁ አይርቅም; ሚስማር ሰራሽ ብሱ!
ቄሳራዊ መስቀል እየቀያየርን
ኤሎሄ ያላዳነን
የተቸነከርን
እኛም ክርስቶስ ነን!
የዳግም ትንሳኤ ተስፋ ስናበቅል
ሌላኛው ይመጣል ተክቶ ሚሰቅል
ጩኸት ስቃያችን ሰማይ አልተሰማም
በተስፋ እጦት ጦር ግን፣
ልባችን አልደማም።
መሰቀያችንን መስቀል ተሸክመን
ተራራውን መውጣት አጣምኖ ያደከመን
እኛም ክርስቶስ ነን!
ከሸክማችን ላይ ያገዘን ሰው የለም
በታሪክ ክፍላችን ይህ እንግዳ አይደለም
“ተጠማን” ብንልም ውሀ አላጠጡንም
የቄሳር ወዳጆች፣ ቢያውቁም አያውቁንም!
መቼም ታሪክ ያልፋል፣
ግን ትዝብት ይተርፋል
ፃፈው ከመዝገቡ፣
እኚያ በላኤ ሰብ፣ ከዋሻ እስኪገቡ
መስቀል የለመዱ በሰልፍ የሚነዱን
እኛም ክርስቶስ ነን
አዝነው እስኪያወርዱን!
One Comment
አንተንማ በደንብ መስቀል ነዉ እንጂ