አውላቸው እባላለሁ … ተወልጀ ያደኩት እዚሁ ሰፈር ነው (ሌላ ምን መሄጃ አለኝ) ሰዎች ታሪክህን ንገረን ይሉኛል … ለማንም ታሪኬን ተናግሬ አላውቅም … እኔ,ኮ የሚገርመኝ እስቲ አሁን ማን ይሙት ይሄ ህዝብ ታሪክ ብርቅ ሁኖበት ነው የኔን ታሪክ ለመስማት የሚጓጓው ? … ነገ መንገድ ላይ ሲያየኝ መልሶ እኔኑ የሚዘልፍበትን ስድብ ከታሪኬ ለመምዘዝ እንጅ ! አንተዋወቅም እንዴ … ካጤ ቴውድሮስ ሹርባ አንዲት ሽበት ፍለጋ ሲራወጥ … የሚለው ቢያጣ የአጤው ሹርባ ከቱርክ የተገዛ ዊግ ነው አለ… አሉ አንዱ (ሹርባውን ለጠላቶቹ በመስጠት ያዋረደ መስሎት !) … ይሄንኑ ሞነጫጭሮ የታሪክ ሙሁር ነው ምንትስ ተብሎ መጣ … ምናለበት ቢፅፍ ይላል አንዳንዱ የዋህ ….ታሪክን መካድ ሹርባውን ከመካድ ነው የሚጀመረው … ቆይቶ መላጣነት በኛ አልተጀመረም ሊለን ዳር ዳር ማለቱን መቸ አጣነው ….ሃሃ ለመላጣው ፀጉር ማብቀል ለሹርባም ሹርባ መንጨት ይች ናት የታሪካችን ክንድ ብርታት ….!!
እንግዲህ ይሁና… ከጠቀማችሁ ታሪኬን እናገራለሁ ….አውላቸው እንደሆንኩ ትነጩት ሹርባ ታወሩበት መላጣ የለኝ ….ከላይ እንደነገርኳችሁ አውላቸው እባላለሁ … በሽ ዘጠኝ መቶ አምሳ ምናምን እዚሁ ሰፈር ተወለድኩ … ይሄ ጊዜ ‹‹የታህሳሱ ግርግር ›› ተብሎ በታሪክ ይታወሳል ….መፈንቅለ መንግስቱን ግርግር ያሉት ለማናናቅ እንደሆነ እንጠረጥራለን ….ግን የአገራችን እጣ ፋንታ የሚወሰነው ከዛም በፊት ሆነ በኋላ በግርግር ነውና እንኳን ግርግር አሉት ! (((ግርግር ላይ ሌላ ቀን አወራችኋለሁ)))…እና … አዋላጇ እትየ ማንትስ አገላብጠው አዩኝና ….‹‹ይሄ ልጅ ወደፊት ንጉስ ነው የሚሆን ግንባሩ ያስታውቃል›› አሉ ይሄው ሁለት ነው ሶስት ንጉስ አለፈ ወፍ የለም ! እንግዲህ እንደታክሲ ወረፋ ንግስናን ተሰልፌ እስኪደርሰኝ እየጠበኩ እንደሆነም እንጃ ! ማን ያውቃል እዚህ አገር እንደሆነ የነገሰውም ንጉስ መሆኑ ትዝ የሚለው ሰው ሲቃወመው ነው ! እስካሁን ጎረቤቶቸም ጓደኞቸም ተቃውመውኝ ስለማያውቁ ንጉስ እንዳልሆንኩ ይገባኛል ! ሃሃሃ
እድሜየ ለትምርት እንደደረሰ ደጃዝማች ይፍሩ አንደኛ ደረጃ ትምርት ቤት በር ላይ ቆም አልኩና አሰብኩ … ‹‹እዚች አገር የተማረ ምን ፈየደ …ንግድ ነው የሚያዋጣው›› አልኩና ደብተሬን ጥየ የሊስትሮ ሳጥን ባልጠና እጀ አንጠልጥየ ወጣሁ ….ከዛን ቀን ጀምሮ እንደወጣሁ አልተመለስኩም ! ያልጠረኩት የጫማ አይነት አልነበረም …. የዘመንን መለወጥ ክረምትን አልፋ መስከረም ላይ በምትወጣው ፀሃይ ሳይሆን ሰዎች ጫማ ላይ ተምርጎ በማየው ጭቃ ልክ ነበር የምለካው …. የአገዛዝንም መለወጥ ሰዎች የሚጫሙትን ጫማ በማየት ነፍሴ ትረዳው ነበር … የወታደር ጫማ የሊስትሮ ሳጥኔን ሲረግጣት ዚያድ ባሬ በምስራቅ መተናኮሱን መንግስት አወጀ …. እንዲህ እያልኩ የተራማጁን ጫማ ሁሉ አሳመርኩ …አገሪቱ ግን ወዴትም አልተራመደች ! አገር ታቦት ነበረች …ትውልዱ ተሸክሟት ሲጓዝ ትውልዱን የምትባርክ ሲገፏትም መርገምቷ ለዘመናት የሚያቀጭጭ ….ይሄው ይችን ቅድስት ታቦት የሚሸከም ንስሃ የገባ ቅዱስ ዜጋ ጠፍቶ አለች ወዴትም ሳትንቀሳቀስ ‹‹ቅዱስ›› ብቻ እየተባለች !!
አገሬን የሊስትሮ ሳጥኔ ላይ ከነግሳንግሷ ተመልክቻታለሁ ….ዘመን መጣ ዘመን ሄደ …ቀይ ሽብር ነጭ ሽብርን እያባረረ በሊስትሮ ሳጥኔ አጠገብ አለፈ … አንድ ቀን አንድ ጎልማሳ ጫማውን እያስጠረገኝ አንድ እግሩን ቦርሸ ሌላኛውን ልቦርሽ እግሩን እንዲቀይር ሳጥኗን በቡርሽ ኳኳ ሳደርክ እኩል ከሳጥኗ ድምፅ ጋር አንዳች የፍንዳታ ድምፅ ሰማሁ … ጫማውን የሚያስጠርገኝ ወጣት በደረቱ እኔ ላይ ወደቀ …ደሙ ፊቴን ሸፈነው … እግሩን ሳይሆን አለሙን ቀየረ …የቅድሙ ሰውየ እሬሳ ሆነ ….ማን እንደተኮሰው ባላወኩት ጥይት ደንበኛየ ፊዳ ሁነ ….ይሄ ልጅ ለግዜር ሰው ነው …ለተኳሹ ጠላት ነው ..ለእኔ ደንበኛ ነው ….ይሄ ሁሉ ሰው ነው በአንድ ጥይት እንደሚዳቋ ገለው የጣሉት !
ሰዎች እየተጯጯሁ ሬሳውን ሲጎትቱት ለእኔ ሊከፍል በእጁ የያዛት ስሙኒ ከእሬሳው እጅ ወድቃ እየተሸከረከረች አጠገባች ያለ ቱቦ ውስጥ ገባች ….የአንድ እግሩም ጫማ መቦረሽ ይቀረው ነበር …ለፍርድ ቀን እግዜር ዙፋን ፊት አንድ እግሩ ባልተቦረሸ ጫማ ቁሞ ገዳዮቹን ሲከስ ታየኝና ከት ብየ ሳኩ …መራር ሳቅ …ለካስ ደሙ ላይ ምናምን ለክፎኝ ነው …እስካሁን ሞት ያስቀኛል …ተኩስ ያስቀኛል… ፖለቲካ ያስቀኛል…. ሟችም ገዳይም የአንድ እግር ጫማቸው የተቦረሸ አይመስለኝም . . . እኔም ሁልጊዜ ለዚች አገር ያልጨረስኩት ስራ ያለ ይመስለኛል ….ሁሉም ዜጋ የጀመረው ስራ ከየት እንደተተኮሰ በማያውቀው ጥይት ደመከልብ እየሆነበት የሚያደርገው አጥቶ የቆመ ይመስለኛል ….ማን ያውቃል ነገ ….የገዳዩን ጫማ እንቦርሽ ይሆናል … ቢሆም እኔ አውላቸው ነኝ . . . ሌላ ቀን ሌላውን ታሪኬን የምነግራችሁ ….እኔ አውላቸው ነኝ !!