Tidarfelagi.com

‹‹ፌዴራል ነፍሴ››

 

ረቡዕ አምስት ሰአት ገደማ ነው። ከጥንቃቄ እና ምቾት መዘነጥ በልጦብኝ ክፍትና ስፒል ጫማ አድርጌ …ቂቅ ብዬ ቀጠሮዬ ቦታ ደረስኩና ከመኪና ወረድኩ። ሲዘንብ አይደል ያረፈደው? የምሄድበት ህንጻ ውስጥ ለመግባት ጎርፉ እንዴት ያሳልፈኝ! በቀኝ ጎርፍ። በግራ ጎርፍ። ፊት ለፊቴ ጎርፍ። በጀርባዬ ደግሞ ቱር ቱር እያሉ የሚያልፉ በትእግስት አልባ ሹፌሮች የሚነዱ መአት መኪኖች።

ግራ ተጋብቼ በዙሪያዬ የሚጎርፈው ውሃ የእግሮቼን ጣቶች ሲነካ‹‹ እችክ እችክ›› እያልኩ እንጣጥ እንጣጥ ብዬ ቀና ስል የታጠቀ ፌዴራል አተኩሮ ሲያየኝ ተመለከትኩ። አፈር ብዬ አየሁትና በየት መሄድ እንደሚሻለኝ ለመወሰን ሳንገራግር ከየት መጣ ሳልለው አጠገቤ ደረሰ።

– እዚጋ መቆም አይቻልም…ቶሎ ተንቀሳቀሽ ምናምን ሊለኝ ነው ብዬ ደንገጥ ስል…
– አሁን በክረምት እንዲህ አይነት ታኮ ጫማ ይደረጋል ? አለኝ

ተማታብኝ።

በቀልድ የሚቆጣ ታላቅ ወንድም ነበር የሚመስለው። ድምፁም ፊቱም በቁጣና በተረብ ስሜቶች መሃል እንደሆነ ያስታውቃል።

– አይደረግም…አልኩ ቀልቤን ሰብስቤ፣ እንደመሽኮርመም እያደረገኝ…

ወዲያው ጠመንጃውን ወደኋላ ገፋ አደረገና…

– በይ ነይ ላሻግርሽ…. ብሎ ለሸክም ሲዘጋጅ ፍዝዝ ብዬ አየሁት።
– ነይ እንጂ…!
– እሺ…አልኩና ታቀፍኩ።

የፈራሁትን ጎርፍ በፌዴራል ታቅፌ፣ ተደግፌ ተሻገርኩ።

– በጣም አመሰግናለሁ…ወንድሜ…. አልኩኝ ወንድሜ ስል አፌን ማር ማር- ምላሴን ስኳር ስኳር እያለኝ…
– ችግር የለውም…ግን ለሌላ ቀን በክረምት እንደዚህ አይነት ጫማ እያደረጋችሁ ስራ አታስፈቱን….አለኝ ሳቅ ብሎ እያየኝ።
– አናደርግም…አናስቸግርም….አልኩ ገንዘብ በማይገበየው፣ ጊዜ በሰጠኝ ደግነቱ እየተደሰትኩ…

ከአሁን በኋላ መስከረም ሳይጠባ፣ አደይ ሳይፈነዳ፣ የቅዱስ ዮሃንስን ዶሮ ሳልበላ፣ የልጆችን አበባየሽ ሆይ ዜማ ሳልሰማ፣ ክፍትና ታኮ ጫማ አድርጌ የፌዴራል ፖሊስን ጊዜ አላባክንም። ስራም አላስፈታም።

በጥይት ከሚደበድብ ፌዴራል ጠብመንጃውን ወደ ኋላ አድርጎ ጎርፍ ወደ ሚያሻግር ፌዴራል ያሸጋገረን ታሪክ ቀያሪ አምላክ ግን ይመስገን።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *