Tidarfelagi.com

ምክር እስከመቃብር

የሆነ ጊዜ ላይ ባንድ እውቅ ሆስፒታል ውስጥ ያማካሪነት ሥራ እሠራ ነበር። የሥልጠና መርሐችን ከአሜሪካኖች በቀጥታ የተኮረጀ ስለነበር ምክራችን ድሐን መሠረት ያደረገ አልነበረም።
ከእለታት አንድ ቀን አንዱ ጎስቆል ያለ ሰው ወደ ቢሮየ መጥቶ ምርመራ ተደረገለት። ውጤቱን ተመልክቸ በደሙ ውስጥ ሻይረሱ እንደተገኘበት ከገለጽኩለት በኋላ ፤ “አይዞህ ምግብህን በተገቢው መንገድ እያበሰልህ፤ ፍሪጅ ውስጥ እያስቀመጥክ የምትመገብ ከሆነ ቫይረሱ አይጎዳህም”አልሁት።

“ጥሩ “ አለ ሰውየው ትንሽ ከተካከዘ በኋላ “ ታድያ ምግቡንና ፍሪጁን መች መጥቸ ልውሰድ?”

መንግሥት“ ከመጸዳጃ መልስ ምግብ ከማዘጋጀት በፊት ወዘተ እጅዎን በሳሙናና በውሃ በመታጠብ አተትን ይከላከሉ”የሚለው ምክር በስልኬ በለቀቀብኝ ቁጥር ትዝ የሚለኝ ያ ጎስቋላ ሰውየ ነው። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመለሥ ዜናዊ እንዳሉት የዲሞክራሲያዊ መንግሥት ዋና ተግባር ለዜጎች ሀብትን በእኩልነት ማከፋፈል ነው ። ግን ምንዋጋ አለው? በኛ አገር የመንግሥት ዋና ተግባር ምክርንና መከራን ማከፋፈል ሆኗል።

ሌላው ይቅር ፤ አሁን ስለሳሙና ጥቅም መንግሥት ወጣቱን ሊመክረው የገባል? ሰው ምን ይለናል አይባልም?ብታምኑም ባታምኑም ወጣቱ ትውልድ ሳሙና ካተት ብቻ ሳይሆን ካባላዘር በሽታና ካልተፈለገ ርግዝና እንደሚጠብቀው ጠንቅቆ ያውቃል።

ባገራችን መጸዳጃ ቤት በጣም ብርቅ ነው። አብዛኛው የገጠር ሰው ለሦስት ሺህ ዘመን እንደ ደፈጣ ተዋጊ ቁጥቋጦ ውስጥ ሸምቆ ሲጸዳዳ ኖሯል ። ባላገር ዛሬ ድረስ “ እግዜር ሲቆጣ በዝናብ አር ያመጣ ” ብሎ ይተርታል ። ከተሜውም በጠራራ ጸሐይ ፤ ባደባባይ ከጎረቤቱ ጋር ጎን ለጎን ቆሞ ሲሸና በመኖሩ የተጠቃው በጉንፋን ብቻ አልነበረም። ከዚያ አልፎ፤ ብልቱን አጠገቡ ከሚሸናው ሰውየ ብልት ጋር በማወዳደር ለpenis envy ሲጋለጥ ኖሯል።

እኔ ራሴ ሽንትቤት ለመጠቀም ስፈልግ ታክሲ ተኮናትሬ ከሃያሁለት ወደ ካዛንችስ ለመሄድ እገደዳለሁ ። ከታክሲ ወርጀ ካዛንቺስ ወደሚገኝ አንድ ዘናጭ ሆቴል ጎራ እላለሁ። ፡ ሱፌን ግጥም አድርጌ፣ ሳምሶናይቴን አንጠልጠየ ጣደፍ ጣደፍ እያልሁ ስገባ የሆነ አህጉር – አቀፍ ስብሰባ ለመሳተፍ የምገባ እንጂ ሽንትቤት ፈልጌ የመጣሁ አልመስልም። ከዛ ሻይ አዝዝና ለሻዩ ስል እንደመጣሁ ለማስመሠል ዐሥር ደቂቃ ያክል ቁጭ ብየ ምላሴን በንፍር ውሃ እቀቅላለሁ። ተዚያ አስተናጋጂቱ ባጠገቤ ስታልፍ ” ይቅርታ እሙ? በየት በኩል ነው ሬስት ሩሙ ” ብየ እገጥማለሁ። “ሽንት ቤቱ ተይዟል።”ብላ ኩስትርትር ትልብኛለች። አዲሳባ ውስጥ አንድጊዜ በወረፋ አትቀደም እንጂ ከተቀደምክ መጠበቅ የማይታሰብ ነው። የዘንድሮ ደንበኛ ከሽንት ተቀምጦ ፤ ፌስቡኩን ሲጎረጉር ስለሚውል ፤ መንግሥት ኢንተርኔት ብሎክ ካላደረገ በቀር ከሽንትቤቱ አይፋታም፡ ፡ በየሆቴሉ እየተንከራተትሁ ደርዘን ሻይ ጠጥቸ ሳይሳካልኝ የተመለስኩበት ጊዜ ብዙ ነው።

የሆነ ነገር ትዝ አለኝ። የፈረደበት ባላገር የሆነ ጉዳይ ለማስፈጸም አዲሳባ መጥቶ ይሰነብታል። ሽንት ቤት ፍለጋ በየካፌው ጎራ ሲል “ተበላሽቷል፤ ሰው ገብቶበታል” እያሉ ያካልቡታል። በዚህ ዓይነት ሦስት ቀን ከተሰቃየ በኋላ ወደ አውቶብስ ተራ በትካዜ አሻግሮ እየተመለከተ እንዲህ አለ፤
“ እንዲያው አገሬ ገብቸ ፤አርቸ አርቸ በወጣልኝ!”

የወረፋ ነገር ከተነሣ ትናንት ለሆነ ጉዳይ ካዛንችስ አካባቢ ተሰልፌ ነበር፡ ፡ ወረፋው በጣም ረጅም ከመሆኑ የተነሣ ፊት ከቆመው ሰውየ ጋር መገናኘት የሚቻለው በስልክና በኢሜል ነው። ሰው ደግሞ ወረፋ የመጠበቅ ትግሥቱም ሆነ ጨዋነቱ ጥሎት ጠፍቷል። አንዱ ኩላሊት አለብኝ ሲል አሳለፍነው። ሌላው ሪህ አለብኝ ብሎ አልፎን ሄደ። ጤነኛ ሆኖ የመኖርን ጉዳት ለመጀመርያ ጊዜ የተረዳሁት ያኔ ነው። ካሰልቺ ጥበቃ በኋላ እኔም ” ጎበዝ ትንሽ ራሴን ስላመመኝ ታስቀድሙኝ? ብል፤ከፊቴ የቆመው ተሠላፊ“በራስህ ቆመህ ነው እንዴ ወረፋ የምትጠብቀው ?”ብሎ ገገመ።

አንዳንድ ሰዎች ሰሞኑን በኢንቦክስ ባገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ላይ አንድ ነገር በል እንጅ እያሉ ሲወተውቱኝ ነበር። ለጊዜው ፤አንድ ነገር ብየ፤ አንድ ነገር መሆን ስላልፈለግሁ ከጸሐፊነት ወዳንባቢነት ተሸጋግሬ ቆይቻለሁ! አሁን ግን በጣም በዛ ! የምሰማውና የማየውው ሁሉ “ኢትዮጵያ ከየት ወዴት እያሰኘኝ ነው!

ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ጉዲሳ ካባታቸው ከራስ መኮንን የወረሱትን የኢዮቤልዩ ቤተመንግሥት ወደ ዩንቨርሲቲነት ቀይረውት እንደነበር በታሪክ ሠፍሯል። ይህ ከሆነ ካርባ ምናምን ዓመት በኋላ ጌቶች፤ በደብረማርቆስ የሚገኘውን የንጉሥ ተክለሃይማኖት ትምርትቤት ወደ እሥርቤት ቀይረውታል። ጎበዝ እየተስተዋለ ! ባርሶ -አደሩ ድጋፍ ቆምያለሁ እያለ በአሥሮ- አደሩ ድጋፍ የሚቆም መንግስት መውደቁ አይቀርም!!ሳይንሳዊ ሀቅ ነው አልጠራጠርም! እኔም ይችን ተናግሬ አምሳ አመት አልኖርም። ግን ምናስጨነቀህ በውቄ? አዲሳባ ውስጥ መኖር የወሰንክ ቀን፤ ያኔ ከህይወት ጎድለሀል። ልማታዊ መንግሥት ባይገድልህ ልማት ራሱ ይገድልሀል።

ባለፈው እዚህ ሃያሁለት ማዞርያ አንዱ የተረፈው አስፓልት ዳር ፎቅ ይሠራል። ቡልኬትና መስታወት ያስቆልላል ቢባል ይሻላል። ግምበኞቹና አናጢዎቹ በቀን አምስት መንገደኛ ለመግደል ቆርጠው ከቤታቸው የወጡ ነው የሚመስለው። እኔ ስለኑሮና ብልሃቱ እያሰብኩ ወክ ሳደርግ ግብዳ ቡልኬት ለጥቂት ስቶኝ ወደቀ። ቡልኬቱ አተኩሬ ሳየው ራሱን የቻለ ግልገል ህንጻ ነው ። የወንቃው ጊዮርጊስ ስላተረፈኝ ላመሰግን፤ እግረ መንገዴንም አናጢውን ልሳደብ ሳንጋጥጥ፤ የስሚንቶ ሊጥ የያዘ ባሊ ቁልቁል ወዳናቴ ሲመጣ አስተዋልኩ። እረ ምን ጉድ ነው እያልሁ እያፈገፈግሁ ስሮጥ ባቡሩ ለትንሽ ስቶኝ አለፈ።ባለፈው አንዱ እንዲሁ ባቡሩ ለትንሽ ስቶት ፖሊሶች ያዙትና ” ስትክለፈለፍ ላደጋ ተጋልጠህ ነበር“እያሉ በቆመጥ ወቁት። ሰውየው ከሩምታው ድብደባ ለጥቂት ተርፎ በቃሬዛ ሸክም ወደ አምቡላንስ ሲገባ እንዲህ ሲል ተደምጧል።

”ባቡሩ እየተመላለሰ ቢገጨኝ እንኳ እንዲህ አልጎዳም ነበር“

4 Comments

  • yeabtsega negash commented on September 12, 2016 Reply

    ፡ተመለስ ዜናዊ፡ ትመቻለች በርታ እንግዲህ አንተም ሳትደበደብ አንድ መጽሃፍ መርቅልን እንወድሃለን

  • henok commented on January 3, 2017 Reply

    ያምራል
    ግን ፍቅር እስከ መቃብርን ዋጋውን ያሳነስከው መሰለኝ

  • reshid yakini commented on March 19, 2017 Reply

    ዋውውውውውውውው ምርጥጥጥጥ

  • በእምነት commented on July 4, 2017 Reply

    በጣም ጀግና ነህ አገላለጽ አንደኛ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *