Tidarfelagi.com

ኖረሽ እይው በቃ

(ለoptimistቶች)

ጨለማ ነህ ብለሽ እኔን ስትተቺ
ዘልለሽ አትጠግቢ ስቀሽ አትሰለቺ
ወርሃ- ፅጌ ነው አመት ሙሉ ላንቺ።
ደሞ በየቀኑ
ፋሲካ ነው ኑሮሽ
ያለም ሰቀቀኑ
ሩቅ ነው ለጆሮሽ
(የፍጥረት ሰቆቃ)
ለጋ ነው አእምሮሽ
ገላሽም ነው ጮርቃ
ሌላም አልልሽም ኖረሽ እይው በቃ።

በየጎዳናሽ ላይ አደይ የሚያነጥፍ
በየዛፉ ቅርፊት ስምሽን የሚጥፍ
በዝቶልሽ ፈልቶልሽ አንቺን ሚያሽሞነሙን
ቀምሰሺው አታቂም የብቻነት ሸክሙን
አዎ
መፈቀር መታጀብ ከኔክታር ይጥማል
ግን ደግሞ ይገጥማል
በተወደሱበት አንደበት መነቀፍ
ውብ ገላ ጠብቆ ርጥብ ንፋስ ማቀፍ
አንዳንዴ ይገጥማል
የማይሰምር ምኞት የማያልቅ ጥበቃ
ሌላም አልልሽም ኖረሽ እይው በቃ።

አንቺ ደስታ ወዳጅ!!
በለምለም አፀድ ውስጥ ቢራቢሮ አሳዳጅ
ኑሮ ምትታይሽ እንደ ጣኦስ ቀልማ
እንዳትሽወጂ ባዝማሪዎች ዜማ
በሸንጋዮች ቃላት
ህይወትም እንደጃርት የሾህ ቀሚስ አላት።

ተድላም ከሀዘን ጋር ያልፋል በፈረቃ
ከሳቅ በስተጀርባ ይሰለፋል ሲቃ
ሌላም አልልሺም ኖረሽ እይው በቃ።

——

-ወርሃ ፅጌ( ያበባ ወር-spring
-ጣኦስ( በሚያምር ህብረቀለማት የተዋበች ወፍpeacock

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *