“… ዓይን ወረተኛ ነው ያመጣል እንግዳ’’ የሚል ስንኝ ያለበት የባላገር ዘፈን አውቃለሁ፤ በርግጥ ዘፈኑ እንደሚነግረን ዓይን ብቻ አይደለም አዲስ ለምዶ እንግዳ ይዞ የሚመጣው፤ ጆሮም፣ ልብም፣ እጅም፣ እግርም መጠናቸው ይለያይ እንደሆነ ነው እንጂ፣ ከአዲስ ነገር ጋር አስተዋውቀውንና አላምደውን እንግዳ ይዘውብን ይመጣሉ።
ያ እንግዳ የሆነው ሰው አውቆም ይሁን ሳያውቅ፣ ትቶልን ወይም ጥሎብን የሄደው አዲስ ዕቃ፣ ለሕይወት ያለንን ትርጉም ሊያዛባው ወይ እንደ አዲስ ሊገነባው ይችላል።
እንደምታውቁት የኢትዮጵያ ሕዝብ በመጨባበጥ ሰላምታ መለዋወጥ ከጀመረ 90 ዓመት አልሞላውም፤ ይህን እጅ የማነካካት ሰላምታ የወረስነው ከጣልያን ነው፤ ከዚህ ሰላምታ በፊት የአዲስ አበባም ሆነ የክፍለ ሀገር ሰዎች፣ ከትከሻ ዝቅ ካንገት ጎንበስ በማለት የ“እንደምን ዋሉ?”፤ የ‘እንደምን አደሩ’፣ ‘… ሰነበቱ’፣ ‘… ከረሙ? ቃላትን ያዥጎደጎድ ነበር እንጂ መጨባበጥን አያውቅም ነበር።
‘ቻዎ’ የምትለዋን የስንብት ቃል አይጠቀምባ ትም ነበር። እንደወልደጊዮርጊስ ወልደዮሐንስ ያሉ የዘመኑ ፀሐፍት፣ ሕዝቡ በ‘መጨባበጥ’ ሰላምታውን እንዲገልፅ፣ ነባሩ ሰላምታ ኋላቀር እና አይረቤ እንደሆነ እንዲገባው፣ ከማደግደግ ይልቅ ቀና ብሎ፣ እጅ ዘርግቶ፣ የሰላምታ ተቀባዩን ዓይን እያዩ መነጋገር በእግዜር ዘንድ የተመረጠና የተወደደ መሆኑን ግጥም እየፃፉ፣ ለፋሽስቱ የቅስቀሳና የፕሮፓጋንዳ ሥራ ሰሩለት።
የሆነው ሆኖ ፋሽስት ጣልያንን አባረርነው። ሰላምታ አሰጣጡን ግን ይዘህ ሂድ አላልነውም። ከሰባ ከሰማንያ ዓመታት በፊት እንደ እነ አክሊሉ ሀብተወልድ ያሉ ሹማምንት አንድ ሰው በሰላምታ አሰጣጡ ብቻ ለየትኛው መንግስት እንዳደረ ያውቁ ነበር። ከፋሽስት ጉቦ እየተቀበሉ ደመወዝ እየወሰዱ ነው ተብለው የተጠረጠሩ፣ ወይም “ጣልያን የመጣው ብርሃን ሊያሳየን፣ እውቀት ሊያስተዋውቀን ነውና ወድቀን ለመላላጥ ካልሆነ በስተቀር አንታገለው፣” የሚል ፅኑ አቋም ይዘው ይኖሩ የነበሩ ሰዎችና ቤተሰቦቻቸው፣ በሰላምታቸው ተመሳሳይነት ይለዩ ነበር። ዛሬ ግን ሁላችንም በመጨባበጡ ሰልጥነንበታል…
እንግዳ ሆኖ ለጥቂት አመታት ኢትዮጵያን ሲያውክ እና በአርበኛ ኢትዮጵያውያን ሲታወክ የቆየው ፋሽስት ጣልያን፤ የሰራውን መንገድ እና ድልድይ ብቻ ሳይሆን፤ የፋሽስት ሰላምታውን ትቶልን ወይም ጥሎልን ሄደ…
ሀዲስ ዓለማየሁ በአንድ ወቅት ወደ ጎጃም ሄደው ነበር። የሄዱበት ቦታ እልም ያለ ገጠር ነው። ከገበሬ እና ግብርና ውጪ ዘመናዊ ስልጣኔ የማይታወቅበት ቦታ ነው። አቶ ሀዲስ ድንገት አንድ የሰው ስም ሰምተው ደንገጥ አሉ ። የአካባቢው ሰውም ስሙ ያልተለመደ እንደሆነ ያውቃል። እናም የልጁን አባት አስጠርተው ጠየቁት ፣ ‘ማን ነው ያልከው ስሙን?’
አባትም በኩራት መልስ ሰጠ፣ ‘ኦክስጂን!’
‘ የኦክስጂንን ትርጉም ታውቀዋለህ?’
‘ኧረ እኔ የት አውቄ?’
‘ታዲያ ምን ሆነህ፣ ከየት አምጥተህ ነው፣ ልጅህን ኦክስጂን ያልከው? ትርጉሙን ሳታውቀው?’ አሉት፣ አቶ ሀዲስ።
ገበሬውም ፣ ‘ ፊታውራሪ ተክለሃዋርያት ተክለማርያም በጨዋታ መሃል ሲናገሩ ሰምቼ ነው። በትላልቅ ሰዎች መሀል ሆነው አስር ጊዜ ኦክስጂን፤ ኦክስጂን ይላሉ። መቸም ከእሳቸው አፍ ክፉ ነገር አይወጣም፤ ኦክስጂን ጥሩ ነገር ቢሆን ነው አልኩና ስሙን ኦክስጂን ብዬ ሰየምኩለታ!’ አለ።
አቤት አቶ ሀዲስ በዚህ ጊዜ የሳቁት ሳቅ !
… በቃ ይኸው ነው። አንዳንድ ጊዜ እንግዳ ሆነህ በምትሄድበት ቦታ ቀርቶ እንግዳ ሆኖ የተገኘ ሌላ ሰው ያልሰጠኸውን ነገር ካንተ ወስዶ ይጠቀምበታል። መቸም ካፍህ ክፉ አይወጣም ብሎ!
አፄ ኃይለስላሴ የእንግሊዛዊው ስመጥር የተውኔት ፀሐፊ፣ የጆርጅ በርናንድ ሾው መጽሐፍ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይገባ ከልክለው እንደነበር ያውቃሉ? ነገሩ እንዲህ ነው። ጣልያን ሀገራችንን ወርራ በነበረቻት ጊዜ በስደት ላይ የነበሩት ጃንሆይ እና ሲልቪያ ፓንክረስት ወደ ጆርጅ በርናንድ ሾው ቤት ይዘልቃሉ። ወደዚህ ቤት ለመዝለቅ የፈለጉት ‘አርስዎ ተሰሚነት ያለዎት እና የተከበሩ የእንግሊዝ ሰው ነዎትና ጣልያን ጓዟን ጠቅልላ እንድትወጣ ድምፅዎን በማሰማት ይደግፉን’ ለማለት ነው በአጭሩ! ፀሐፊ ተውኔቱ ግን እኝህን የተከበሩ የሀገር መሪ በስርዓት ቢያስተናግዱም ሀሳባቸውን ግን አልተቀበሉም። ‘ይቅርታ! ለዘመናት በጭለማ ታስራ የቆየች ሀገር ፣ጥቂት የብርሀን ጭላንጭል ለማየት አጋጣሚው ሲመቻችላት፣ የለም በርዋን ቆልፋ፣ መስኮታን ከርችማ ትቀመጥ ብዬ አልወስንም!’ አሉ.. በዚህ ጊዜ ጃንሆይ ተናደዱ። አበሻ ቢሆን ኖሮ፣ ‘ከእንግዲህ ደመኛዬ ነህ መቃብሬ ላይ እንዳትቆም’ ይሉት ነበር ግን ባዶ ነው እና አንድ ሀሳብ መጣላቸው ‘የዚህ ሰውዬ መጽሐፍ በምንም ተዓምር ቢሆን ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ!’
በርናንድ ሾው ይህንን ውሳኔ ቢሰሙ ኖሮ፣ ውሳኔውን መነሻ አድርገው የሚጨበጨብለት ቲያትር ይደርሱ የነበረ ይመስለኛል።
ይህ ሁሉ ምሳሌ ስለእንግዳ ነው። እንግዳ ስለሆኑ ሰዎች ፣እንግዳ ስለሆኑ ሃሳቦች፣ እንግዳ ስለሆኑ እቃዎች፣ ተቀብለን የሸኘናቸው እንግዳዎች ሕይወታችንን ለመገንባትም ሆነ ለማፍረስ ስለሚጫወቱት ሚና ፣ተራና ቀላል መስለው የታዩን ቃሎችና ቁሶች እኛን እንዴት እንደ አዲስ እንደሚሰሩን!
እንግዳ ሆነን በምንስተናገድበት ሆነ በምናስተናግድበት ሥፍራ ደግሞ አውቀንም ይሁን ሳናውቅ ጥለነው የምንመጣው ነገር ይኖራል። የትምህርት ቤቶች፣ የመፃሕፍት፣ የመገናኛ ብዙሃን እና የሃይማኖት ሊቃውንት ዓላማም ይኸው ነው። ከአዳዲስ ‘እንግዶች’ ጋር በማስተዋወቅ እኛን ለለውጥ ወይም ለነውጥ ማነሳሳት!…
እነዚህን እንግዶች ሳንፈልጋቸው ቀርተን ብናባርራቸው እንኳን፣ ሙሉ ለሙሉ ከልባችን እና ከቤታችን ማስወጣት ይከብደናል። ሳይፈልጉን እና ሳንመቻቸው ቀርተን ቢለዩን እንኳን ስለነሱ ጠብታ ትዝታ ይኖረናል። በአስተሳሰባችን ላይ አሻራቸው ታትሞ ይቆያል።