Tidarfelagi.com

እየተደማመጥን፤ (በዳምጠው)

የሆነ ጊዜ ከሬድዮ ጣቢያዎቻችን እንዱን ሳዳምጥ ጋዜጠኛው፤
“አድማጮቻችን እንዴት ዋላችሁ ፤ ሰላማችሁ ብዝት ይበል ፤ በዛሬው እለት የምንወያየው ካንገብጋቢ የማህበራዊ ችግሮቻችን ባንዱ ዙርያ ነው ፤ አንድ እንግዳ ስቱድዮ ድረስ ጋብዣለሁ … እስቲ ስምዎትን ለአድማጮቻችን አስተዋውቁ”

እንግዳው : “ የመቶ አለቃ ገረመው እባላለሁ”
“እሺ ሃምሳ አለቃ ገረመው ይቀጥሉ “
“ባሁኑ ጊዜ ትልቁ አንግብጋቢ ችግር አመት በአል ጠብቆ ዋጋ መቆለል ነው፤ ነጋዴው ባዘቦት ቀን ሰላሳ ሺህ ብር የሚሸጠውን በሬ ፤ የገና በአል ሲቃረብ በትራክረት ዋጋ ይሸጥልናል፤ ይሄ በእውነት ነውር ስለሆነ መንግስት አንድ ነገር ቢያደርግ ጥሩ ነው ባይነኝ”

ጋዜጠኛው – እንግዲህ ሻምበል ገረመው የሚሉትን ሰምተናል፤ ሻለቃው በድፍረት እንዳስቀመጡት ከሆነ፤ የአመት በአሎቻችን አለቅጥ መብዛት አገራችንን ለከፋ ድህነት ዳርጉዋታል ፤ መንግስት በአመት በአላት መብዛት የሚባክነውን ጊዜ ለመቀነስ ከአመቱ ቀናት አንዱን ቀን መርጦ የገናን ፋሲካንና የመውሊድን በአል ባንድ ላይ እንዲከበሩ ቢያደርግ ጠቃሚ ነው ባይ ናቸው፤ እንደኔ አረዳድ! በዚህ አነጋጋሪ ጉዳይ ላይ የአድማጮቻችን ምላሽ ምን ይሆን?”

አንድ አድማጭ ገባ፤
“ሬድዮየን ገና አሁን ስለከፈትኩት የተናገራችሁትን አላዳመጥኩትም፤ ያም ሆኖ ስለ መቶ አለቃ ገረመው ጥቂት ለመናገር ያክል፤ በጣም አስቸጋሪ ሰው ናቸው፤ በጎረቤትነት አምስት አመት ቆይተናል፤ እድርም ነበረን፤ ተጨቃጫቂና ሰካራም መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ሶስት መቶ ብር ተበድረውኝ አልመለሱም! ያኔ ሶስት መቶ ብር እንደዛሬው አልነበረም፤አንድ ሄክታር የከረንቦላ ጠሬጴዛ ይገዛል”

“በተነሳው ሃሳብ ላይ ብናተኩር” አለ ጋዜጠኛው አቁዋርጦ።
“ኦኬ ፤ ሲጀመር ስለጃንሜዳ የተናገሩት ነገር በሙሉ አንድም እውነት የለውም፤ ታከለ ኡማ በቲማቲምና በጎመን ሳያጨማልቀው በፊት ጃንሜዳ በየትኛውም ዘመን የገበያ ቦታ ሆኖ አያውቅም፤ ካጤ ምኒልክ ዘመን ጀምሮ ጊዮጊስና ቡና የፈረስ ጉግስ የሚወዳደሩበት ቦታ ነበር፤ ለዚህ ደግሞ ከመቶ በላይ የፎቶ ማስረጃ አለኝ ! ባስፈለገ ጊዜ አወጣዋለሁ”

“ይቅርታ አድማጫችን፤ ከርእሰ ጉዳያችን በጣም እንደራቁ ላስታውሰዎት ነው፤ ስለጃል መሮ አለኝ ያሉትን መረጃ በሙሉ ለሚመለከተው አካል መሰጠት ይችላሉ፤ እኛ ወደ ጀመርነው ውይይት እንመለሳለን፤ አድማጮቻችን ! ደውሉልልን”

ፌስቡክ ላይ የሚደረግ ክርክር ባጭሩ መንፈሱ ከዚህ አይርቅም!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *