Tidarfelagi.com

እያንዳንድሽ!

ወገን! ግጥሙ በሁዋላ ይደርሳል፤ ይሄ አጭር ማሳሰቢያ ነው!

እያንዳንድሽ!
ከናትሽ ሙዳይ ሰርቀሽ ፤ኮኮስ ቅባት የተቀባሽ
በፀደይ ወቅት፤ የስሚዛ አበባ የጠባሽ
ድድሽን ባጋም እሾህ ፤የተነቀስሽ
ጡትሽን ለማስተለቅ፤አጎጠጎጤሽን በውሃ እናት ያስነከስሽ
ቤት ባፈራው ጌጥ ብቻ፤ በዛጎል በዶቃ ያማርሽ
በቃቃ ጨዋታ ወግ፤ በሽቦ መኪና አጀብ የተዳርሽ
ሳይማር በሚያስተምር፤ መምህር የተማርሽ፤

ሲያደንቁሽ የተሽኮረምምሽ፤
ሲነኩሽ የተስለመለምሽ
ሲስሙሽ ፤አገር ለቀሽ ለመመነን ያለምሽ
በቸርቺል ጎዳና ላይ፤ ሰኞ ማክሰኞ የተጫወትሽ
የኔ ትውልድ አባል ነሽ
ብትኮሪ ምክንያት አለሽ

እያንዳንድህ
በጅምር አስፋልት ላይ ፤ሽኩኔታ የነዳህ
ወይራ ከታጠነ ማድጋ ፤በመርቲ ጣሳ የቀዳህ
በጥቂቱ የረካህ ፤በመናኛው የተደነቅህ
ድንኩዋን ሰብረህ፤በቅልውጥ ፤የጎረቤት ሰርግ ያደመቅህ፤
ካባትህ ሽልንግ ሰርቀህ “ዲስኮ ዳንሰርን” ያየህ
ባስር ሳንቲም ፤ትኩስ ሽልጦ የገበየህ

በየመስኩ በየፈፋው፤ ፋንድያህን የነሰነስህ
በብሳና ቅጠል፤ የጅራት ማብቀያህን ያበስህ፤

በችፍርግ ጥርስህን ያነጣህ
ከጆሮህ ውስጥ፤ ሰርጎ ገብ በረሮ ያወጣህ፤
በቃቃ ጨዋታ ላይ፤ የህልምህን ቆንጆ ያጨህ
ራስህን በቤሳ ምላጭ የተላጨህ
ጎረምሳና ኮረዳ ተቃቅፈው ሲሄዱ ስታይ፤ እየተከተልህ ድንጋይ የወረወርህ
ገራም ፍቅርን የወገርህ፤
የሩፋዔል ቀን ታጥበህ፤ ዐመቱን ሙሉ ያደፍህ
በውሃ ቀጠነ የተገረፍህ
ከፖሊዮ በክትባት፤
ከብሄራዊ ውትድርና በብልሃት –
የተረፍህ፤
ከገበሬ ማሳ ላይ በቆሎ እሸት የዘረፍህ
በዳጥና በሸርተቴ ፤ቁምጣ ሱሪህን የጨረስህ
ስሚዛ ስር ተደብቀህ፤የሲጃራ ቂጥ ያጨስህ
ያያትህን የማያልቅ ተረት ፤ያባትህን የማያባራ ኩርኩም የታገስህ
ያለህን ያልቆጠብህ፤ በስስት ያልተንገበገብህ
እንደ አቡየ አይንህን ለወፍ ማጠጣት ባትችል እንኩዋ፤ ጣትህን ለሙጀሌ የመገብህ
የኔ ትውልድ አባል ነህ
ብትኮራ ምክንያት አለህ!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *