Tidarfelagi.com

ከምነቴ ጋር ቀረሁ

አውቃለሁ !
አታምኝም በማምነው
ያንደኛው ሰው መንገድ – ለሌላው ገደል ነው።
ቢቀና ጎዳናው -ቢወለወል አስፋልት
አብሮ ከማያልም -አብሮ መሄድ ልፋት
ያንደኛው ሰው እግር -ለሌላው እንቅፋት።
ባልጮህ ባደባባይ
ምኩራብ ባልገነባ-መዝሙር ባላሰማ
ከጥላየ በቀር ባይኖረኝ ተከታይ
በቃል ወይ በዜማ
ተገልጦ ባይታይ
በልብ ተጠንስሶ-ባይን የሚገነፍል
እኔም እምነት አለኝ-ዋጋ የሚያስከፍል።
“እምነት -ተስፋ -ፍቅር”
መች ባንድ ላይ ሁኖ
ለሰው ልጅ ይሰጣል
በምነቱ የፀና -ድንገት ፍቅሩን ያጣል፤
ፍቅርሺን ሸኝቼው-ተስፋየን አባረርሁ
ከምነቴ ጋር ቀረሁ።
(አዳምኤል)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *