በቀደም አንድ የተባረከ ዜጋ “የዶሮ በሽታ ገብቷል” ሚል ወሬ ነዝቶ የእንቁላልን ዋጋ ቁልቁል ወሰደው፤ አጋጣሚውን ለመጠቀም ሞከርኩ፤ የቤት ሰራተኛየ “ዛሬ ምን ይሰራልህ?” ስትለኝ “ ቆንጆ ሽሮ አንተክትኪልኝና አንድ አምስት የተቀቀለ እንቁላል ጣል አርጊበት” እላታለሁ፤ ከጥቂት ቀናት በሁዋላ የሆነ ክሊኒክ ምርመራ አደረግሁ፤ ኮሌስትሮል ውጤቴን ሲመለከቱ፥ ዶክተሮችና ነርሶች ተሰብስበው ተላቀሱ ፤ የክሊኒኩ ዘበኛ ግን “ አይዞህ ! በርሀብ ሞተ ከምትባል በኮሌስትሮል ብዛት ሞተ ብትባል ለስምህ ጥሩ ነው “ በማለት አጽናናኝ።
በማግስቱ እዚህ ሀያ ሁለት ማዞርያ -ቺቺኒያ በሚገኘው ጂም ቤት Fitness dancing ተመዘገብኩና መስራት ጀመርኩ፤
“ምንድነው እምታደርጉት?” አለኝ ምኡዝ ፤ መስራት መጀመሬን የነገርኩት ቀን፥
“በጋራ እንወዛወዛለን፤ እንደንሳለን፤ “
“አላማው?”
“ክብደት ለመቀነስ ይጠቅማል”
ምኡዝ መሳቅ ጀመረ፤
“ምን ያስቅሀል?”
“በውዝዋዜ መክሳት ቢቻል ኖሮ ፥ ሰማኸኝ በለው ይከሳ ነበር”
“ተው! ተስፋ አታስቆርጠኝ”
“በውዝዋዜው ቀጥል! የወረቀት ዋጋ ስለተወደደ ከዚህ በሁዋላ በደራሲነት መኖር ይከብዳል፤ ስለዚህ ተጠባባቂ ሙያ ይዞ መገኘትህን አልጠላሁትም”
በሀሳቤ ፥ በቅርቡ ሀገር ፍቅር ትያትር የቅጥር ቃለመጠይቅ ሳደርግ ታየኝ፥
ቃለመጠይቅ አድራጊው “የውዝዋዜ ልምድ አለህ?” ሲለኝ፥የሚከተለውን እምነግረው ይመስለኛል፤
ድሮ ጎረምሳ እያለሁ ባልተጠራሁበት ሰርግ የመታደም ልምድ ነበረኝ፤ ተበልቶ ተጠጥቶ ሲያበቃ” እስቲ አምጣው የደሙን ሸማ” እሚል ዘፈን አየሩን ይሞላዋል፤ እንግጣ (ጭፈራ) ይጀመራል፤ ሴቶች ጠልሰሙና ድሪው ደረታቸው ላይ እስኪነጥር ድረስ ይንቀጠቀጣሉ፤ ወንዶች ይወረገረጋሉ፤
ድንገት “ያ ልጅ መጣ! በውቄ መጣ” ይባላል፤ እስክታ መቺዎች እስክስታውን አቁመው አንገታቸውን ደፋ አድርገው ማጨብጨብ ይጀምራሉ፤ ባልቴቶች “ሰፋ አርጉለት“ እያሉ መለፈፍ ይጀምራሉ፤ አረጋውያኑ በበኩላቸው ”አየየ! ዳሱን ካላፈረስንለት በቀር አስፍተን አንችለውም” ብለው ይተክዛሉ፤ እጀምራለሁ፤ እርግፍ እርግፍ እላለሁ፤ ክንዴ ባይብሬተር ሞድ ላይ እንዳለ ኖኪያ ሞባይል ሳያቁዋርጥ ይንቀጠቀጣል ፤ ደረቴ እንደ እፉየ ገላ ይገላበጣል ፤መላው ዳሞት፥ ድፍን ጎጃም “በውኑ ይሄ ልጅ አጥንት አለውን” በማለት ይደነቃል፤ ወድያው ካጥንትም፥ ብርቱ አጥንት እንዳለኝ ማረጋገጥ የፈለግሁ ይመስል በእግሬ ወለሉን መደለቅ እጀምራለሁ፤ እንዲያውም፥ የሆነ ጊዜ ላይ መሬቱን በሀይል ደጋግሜ ከመደለቄ የተነሳ ውሀ ፈለቀ፤ በውሀው እንዳትሌት ፊቴን አረጣጥቤ እስክስታውን ቀጠልኩ፤
ቃለመጠይቅ አድራጊው አድምጦኝ ሲያበቃ፤-
“ወደ ቤትህ መሄድ ትችላለህ! በቀደዳ ዘርፍ ክፍት የስራ ማስታወቂያ ስናወጣ እንጠራሀለን”
One Comment
Wawu