Tidarfelagi.com

ጥቂት ሀሳቦች

አንዳንድ ሰዎች ‘ የብሄር ፖለቲካ በህግ ይታገድልን ሲሉ’ እሰማለሁ፤ የብሄር ፖለቲካ አይጥመኝም፤ባገራችን ወትሮ የሚታየው መከራ ምንጮች አንዱ ያልተገራ የብሄር ፖለቲካ እንደሆነም አምናለሁ፤ ያም ሆኖ ዜጎች በቁዋንቁዋና በዘመድ የመደራጀታቸውን መብት መግፈፍ ሰላምና ደስታ ያመጣል ብየ አላስብም፤ብጤውን መርጦ መቡዋደን የሰው ባህርይ ነው፤ በየጊዜው ልዩ ማንነት መፍጠር፤ ልዩ መለዮ ማበጀት፤ ድንበር ማስመር የሰው ባህርይ ነው፤ አባቶች አድርገውታል! ልጆቻችንም ይቀጥሉታል! በብሄር እንኩዋ ባይኖር ሰዎች በሃይማኖትና በስፖርት ሰበብ እየተቡዋደኑ ሊተቃቀፉም ሆነ ሊተናነቁበት የሚችሉበት እድል ሞልቱዋል፤ ሰዎች በብሄር መቡዋደናቸው በራሱ ችግር አይመስለኝም፤ ችግሩ የብሄር ቡድናቸውን የክፋት መሳርያ ሲያደርጉት ነው፤ እኔ ስጋ የማይመገቡ ሰዎች ማህበር ከተቁዋቁዋመ አባል መሆን እፈልጋለሁ፤አንድ ቀን ወፈፍ አርጎኝ፤ካዛንቺስ ወርጄ፤ የዮናስ ጨርጨር ስጋ ቤትን ላቃጥለው እስካላልሁ ድረስ የኢትዮጵያ ችግር ልሆን አልችልም፤

እና እቴዋ! የብሄር ፖለቲካን አበቃቀሉን ተረጂው፤ከልኩ እንዳያልፍ አድርገሽ ግሪው፤ብትፈልጊ አብጠልጥ ይው፤ግን ላግደው ብለሽ ስትነሺ የበለጠ ታባልጊዋለሽ!የበለጠም ታከሪዋለሽ!

በበኩሌ ፤የብሄር ፖለቲካ በዚህ ዘመን የምናየውን ለከት የለሽ ክፋት መሳርያ የሆነው በሁለት መራዦች ምክንያት ይመስለኛል ፤ቦዘንና የሾቀ የትምርት ስርአት!

_ቦዘን_
ብዙ ወጣት ስራ የለውም፤ መሬት የለውም፤ ሰንደቅ አላማ እንጂ የኑሮ አላማ የለውም፤ አፍላ እድሜውን ያባከነበት ትምርት መሰል ነገር ስራ እንዲፈጥር የሚያስችል አቅም አላስታጠቀውም፤ ዛሬ ብዙ ወጣት ሰርቼ ያልፍልኛል ከሚል ሀሳብ ይልቅ ፤ ምርኮ በመሰብሰብ ተስፋ ተጠምዱዋል፤ ችጋርና ርሀብ ፖለቲካውን ይዘውረዋል፤ የተራበ ህዝብ መሪውን ይበላል ይላል ኦቦ መረራ ጉዲና! እኔ ይመስለኝም! መሪዎች ምናቸው ሞኝ ነው?! ራሳቸውን የተራበ ህዝብ መንጋጋ የማይደርስበት ቦታ ማስቀመጥ ይችሉበታል፤ ይልቅስ የተራበ ህዝብ ጎረቤቱን ሊበላ ይችላል፤ በቀድሞ ዘመን አንድ የመንደር ጉልበተኛ ተነስቶ ጥቂት ጭፍራ ሰብስቦ ጎረቤት ግዛት ይወር ነበር፤ ከተወረረው አገር የሚገኘው የምርኮ እቃ ለመቀራመት ያሰቡ ወጣቶች በጉልበታሙ ሰውየ ስር ለመሰለፍ አያቅማሙም ነበር፤እንዲሁም፤ ዛሬ፤ የብሄር ፖለቲካ ፤ የዚያኛውን ብሄር ሀብት ወርሼ ያልፍልኛል የሚል ህልም ያደረባቸውን ወጣቶች ይማርካል፤

የትምርት ስራቱ ፈርሶ ይሰራ!

ያገራችን የትምርት ስርአቱ ቡትቶ ነው፤ ምንም አይነት ችሎታ፤ ምንም አይነት የኑሮ መላ ለዜጋው አያስታጥቅም፤ ችሎታ የሌለው ሰው ደግሞ ያገር ሸክም ብቻ አይደለም፤ ለርሻ በታጨ መሬት ላይ እንደተቀበረ ፈንጅ ነው፤ትምርት ቤቶች ልጆችን ሰብስቦ ከማቆየት ያለፈ ፋይዳ የላቸውም፤ መንግስት አገራችን ያልታደለችውን ነዳጅ ከመፈለግ ሲማስን ከሚኖር፤ የዜጎችን የተዳፈነ አቅም ቆፍሮ ቢያወጣ ይጠቅመናል! ይህን ማድረግ የሚችለው ቡትቶውን የትምርት ስርአት ወዲያ ጥሎ ፤በተግባራዊ ትምርት ስርአት በመተካት ነው፤የትምርታችንን ሹቀት ለመግለጥ አንድ ነገር ላንሳ፤ዳግማይ ምኒልክት የተማረ አናጢ ስላልነበራቸው ቤተመንግስታቸውን ያሰሩት በውጭ አገር ግንበኞች ነበር፤ዛሬም ቤተመንግስቱ ሲታደስ አናጢዎች የውጭ አገር ባለሙያዎች መሆናቸውን አይተናል! አይተንም በግብዳው አፍረናል!

የሰናይ ምግባር ችግር ይነሳል ፤ መዋደድን መከባበርን ለልጆቻችን እንዲያስተምሩልን የሃይማኖት ጌቶችን ማስቸገር የለብንም፤ የሃይማኖት ጌቶች ጊዜ የላቸውም፤ በሽቀላ ፤በቅዱስ ዘይት ሽያጭ እና ጋኔንን በቃለመጠይቅ እና በካራቲ በማባረር ተጠምደዋል! ትውልድን በሰናይምግባር ማሰልጠን የትምህርትቤት እዳ ነው፤ ልጆች ትሩፋት ቢሰሩ ምድራዊ ሽልማት ፤ክፋት ቢሰሩ ምድራዊ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው እያስረዱ መቅረፅ የዘመናይ ትምርት ድርሻ ነው፤

ስጠቀልለው፤
የረባ ትምርት እና የረባ ስራ የሌለው ዜጋ በብሄር ቀርቶ ፤በመላኣክት ስም ቢደራጅ ከማውደም አይመለስም!

One Comment

  • Agegnehu Asegid commented on May 1, 2019 Reply

    በብሔር መደራጀቱ ጉዳይ ላይ ሙግት አለን። ሰዎች በማህበር መደራጀታቸው የኖረ ልማድ ነው። ተፈጥሯዊም ይመስላል። ግን የብሔር ፖለቲካ ይከልከልና አይደራጁ ለየቅል ናቸው። ያ ስብስብ ተቋማዊ ቁመና እና እውቅና አይሰጠው፣ የፖለቲካ መደራጃ አይሁን ነው መነሻው። እንጂማ ማህበሩን የት ትከተዋለህ። በፎቶው ላይ ያለው የጋና ሕገ መንግስት ለምሳሌ፣ ብሔራዊ ማዕቀፍ የሌለውን የፖለቲካ ፓርቲ ይከለክላል። በጋና የዘውጎች ነፃነት የለም ማለት አይደለም። በሌላ ቦታ ላይም፣ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ሎጎ እና ሞቶው ሀገራዊ ውክልና እንጂ የብሔር ውክልና እንዳይኖረው ይከለክላል።
    በውጤቱ ጋና እንደኛ ትባላለች? እንደውም፣ ዓለም ላይ ካሉ ሰላማዊ ሀገሮች መሀል አንዷ ናት! ሌሎች ጉዳዮች አስተዋፆኣቸው እንዳለ ማለት ነው።
    በአጭሩ የብሔር ፖለቲካ ይታገድ ማለት ፖለቲካዊ ማደራጃ መሆኑ ይቁም እንጂ የብሔሩን ድምፅ አልስማ አይመስለኝም ለማለት ነው። ብትፈቅድም በቶሎ አፓርታይዳዊ ፀባይ ይዞ ከመበጥበጥ ውጪ ይሄ ነው የሚባል ፋይዳ የለውም! እያየን እንዳለነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *