Tidarfelagi.com

ጩጬ ብንሆንም ይገባናል

ምሽቱ ለዓይን ሲይዝ ቤታችን ፊት ለፊት በሩን ራቅ ብዬ እያየሁ ወዲያ ወዲህ እላለሁ፡፡ የሰፈሩ ልጆች ሁሉ በየቤታቸው ገብተው እኔ በዛ ቀዝቃዛ ምሽት አስፋልት ዳር ቀጠሮ እንዳለው ሰው ወዲያ ወዲህ እላለሁ፡፡ ቤቴ አልገባም፡፡ ታዲያ ወላጆቼ እኔን መጠበቅ ይሰላቹና..…. እናቴ ኩታዋን ተከናንባ ከቤት ትወጣለች፡፡ ባያትም እንዳላየኋት ሁሉ ፊቴን አዙሬ — ከቤቴ ለመራቅ እንደሻትኩ ሁሉ መንገዴን በቀስታ እጀምራለሁ፡፡ ትደርስብኝና ፊት ለፊቴ መጥታ ከውሸት ጉዞዬ ታቆመኛለች፡፡ በብስጭት አስፋልቱ ላይ ስቀመጥ እስዋም ተከትላኝ ቁጢጥ ትልና ዓይኖቼን በዝምታ ታያቸዋለች፡፡ ፊቴን ወደመሬት እደፋለሁ፡፡ ልታባብለኝ ሞቅ ያለ እጅዋ ራሴ ላይ በቀስታና በዝምታ ያርፋል፡፡ ወደእስዋ ሳብ አድርጋ የተላጨ አናቴ መሃል — ትስመኛለች፡፡ ቤት ከአባቴ ጋ ሆና እንግዲህ፡ ‹‹የእሱ ጥጋብ፣ አቅም ቢኖረው ይማታል›› ስትል እንዳልነበረ፡፡

ምንም ጩጬ ብንሆን ይገባናል፡፡
በጨለማ ውስጥ ስትስቅ አያታለሁ፡፡ ትከሻዬን ትይዘኛለች፡፡
‹‹የኔ ሰንደል ና እስኪ›› ትለኛለች፡፡
መሬት በእግሬ እየመታሁ ቀርባ እንድታቅፈኝ ልርቅ እዳዳለሁ፡፡ እንባዬን እውጣለሁ፡፡ ትጎትተኝና ጉያዋ ውስጥ ትከተኛለች፡፡ ለማልቀስ እንደፈለግሁ ታውቃለች፡፡ በጋቢዋ ተከናንቤ ትኩስ ምስር ወጥ አሸታለሁ፡፡ ሆዴ ይጮሃል፡፡ ትጠብቀኛለች በዚያ ብዙ ነፍስ በሌለበትና በማልሰለልበት ጊዜ እንደ ወንድ ሳልታይ ሽፍንፍንዋ ውስጥ ተደብቄ እንዳለቅስ፡፡ የምትሸፋፍነኝ ሳላፍር እንዳለቅስ ነበር፡፡

ጩጬ ብንሆንም ይገባናል፡፡
እንዲህ እንደጋረደችኝ ብዙ እንቆያለን፡፡ ሁለቱንም እጆቼን አንስቼ ለይቅርታ ሳቅፋት፣ መሃል አናቴን ጎንበስ ብላ ትስመኛለች፡፡ ሳቅፋት እንደታረቅኋት ይገባታል፡፡ ሳንነጋገረው የተግባባንበት ድርጊት ነው፡፡ አንድ እጄን ይዛኝ እየጎተተች እቤት ትገባለች፡፡ ከአባቴ ጋር አንተያይም፡፡ የመምጣታችንን ዱካ ሲሰማ መኝታ ቤት ይገባል፡፡ ከነጋ በኋላ እንኳን አላየውም፡፡ አንዳንድ ጊዜ እስ ሁለት ቀናት ድረስ አላየውም፡፡
‹ከእናት እጅ መብላት› የሚሉት አባባል ልቤ አይገባም፡፡ ዛሬ ድረስ፡፡
ማብላትማ ዩኒሴፍም ያበላል፡፡
***
አለንጋና ምስር

One Comment

  • miki commented on February 1, 2017 Reply

    ኦኦኦኦኦኦ አዳም መጣጥፎችህና በቃላት የመጫወት አቅምህ ይገርማል ዳግመኛ ኦኦኦኦኦ……

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *