Tidarfelagi.com

ጉደኛ ስንኞች

ከጥቂት ኣመታት በፊት የሆኑ ሸበቶ ሽማግሌ እኔንና ኣብሮኣደጌን ኣንተነህ ይግዛውን ኣፈላልገው ኣገኙንና ለጠቅላይ ሚኒስተር መለስ የሚላክ ኣቤቱታ እንድንጽፍላቸው ማለዱን፡፡የሆነ ጉልቤ በድሏቸዋል፡፡ምሬት ኣባርሮት ወደዚህ ገጽ የመጣውን ኣንባቢ ተጨማሪ ምሬት ላለማካፈል የሰውየውን በደል ኣልጽፈውም፡፡
ተገናኝተን ስንጨዋወት ስለግጥም ተነሳና ኣንድ ግጥም በቃሌ እንድወጣላቸው ጠየቁኝ፡፡እሺ ብየ ኣንድ ሰባት መስመር እንዳነበብኩ ”ምነው እንደ ረፋድ መንገድ ኣስረዘምክብኝሳ ?”ብለው እያፍዋሸኩ ኣቋረጡኝ፡፡
“እንግዲህ የኔ ካልጣመዎት የርስዎን እንስማዋ”ኣልኩ ባኮረፈ ድምጥ ፡፡
“በጀ! ብትቀጥንም ጠጅ የሆነች ግጥም ኣለችኝ ፤ኣድምጥ እንግዲህ”
“ይቀጥሉ”
“ዘመም ዘመም ብለን፤ እንደጤፍ ዘመመን
ዘመናችን ኣልቆ፤ ኣለን በሰው ዘመን”
ዘመመን የሚለውን ቃል ከዚያ በፊት ሰምቸው ስለማላውቅ ቤቴ ሂጄ መዝገበቃላቴን ጠየኩት፡፡( ዘመመን= ሞላላና ዥልጥ ጉቾ ድርድር፡፡
ደስታ ተክለወልድ ፤ ኣዲስ የኣማርኛ መዝገበ ቃላት፤ገጽ496)
2
ኣንድ ገጠር ቀበሌ ውስጥ ኣንዲት ስትፈጭ የምትኖር ሴት ኣለች፡፡ከጎደሎ ቀኖች ባንዱ ባሏ ታሞ ይተኛል፡፡ጎረቤቷ ይህንን ኣጋጣሚ በመጠቀም ኣጥሯን ገፋ ኣድርጎ ቤት ይሰራል፡፡፡ ጎረቤትየው ያዲሱን ቤት ግድግዳ ያቆመበት (የገደገደበት )ቦታ ሴትዮዋ ሽንቷን የምትሸናበት እንዲሁም ግብርውሃ የምትወጣበት Rest rooሟ ነበር ፡፡የታመመው ባሏ ሲሞት ቀብሩ ላይ እንዲህ ኣለቀሰች፤
“እንኳን ኣንተ ሞተህ ፤እያለህልኝ
በሽንት መሽኛየ ላይ፤ ገደገዱብኝ”
ይህንን ሲሰማ ለቀስተኛው ሁሉ ሳቀ፡፡ጥርሱ ይርገፍ ብለን ወደ ቀጣዩ ስንኝ እንለፍ፡፡
3
ውድነህ የተባለ የንጉሥ ተክለሃይማኖት ሎሌ ነበረ፡፡ውዴ ለተክልየ ከማደሩበፊት ጋፋት በሚገኘው ያጤ ቴዎድሮስ መድፍ ፋብሪካ ውስጥ ተቀጥሮ ሳይሆን ተገድዶ ይሰራ ነበር፡፡ውዴ በጋፋት በቀሰመው ጥበብ ተጠቅሞ “ከወዳደቁ ነገሮች” መድፍ ሰራ ፡፡ንጉስ ተክለሃይማኖት ከሚኒሊክ ጋር እምባቦ ላይ ሲዋጉ ውዴ ቤት- ያፈራውን መድፉን የሚሞክርበት ኣጋጣሚ ኣገኘ፡፡ ኣንድ !ሁለት!ሦስት! ድውውው! ወድያ ማዶ የቆመው ባላጋራ ወታደር ሲወድቅ ታየ፡፡ ይሄኔ ውዴ እንዲህ ብሎ ፎከረ፤
ዘራፍ ውድነህ፤ የኮሶ እሸት
በሰራው ገዳይ ፤ እንደመለኮት
የመጨረሻዋ ስንኝ እንዴት ያለ ፍልስፍና ተሸክማለች!! ኣጅሬ የመድፉን ኣስራር ምሥጢር ባይነግረንም የመለኮትን ምስጢር በሁለት ስንኞች ነግሮን ዞር ኣለ፡፡
3
ባንድ ጊዜ ኣሪፍ ኣባትም ቆራጥ ኣብዮተኛም መሆን ይከብዳል፡፡ ሲፈርድብህ ለልጅህ ስትል ጥቃትን ትሸከማለህ፡፡ለጥቃት ፊት ኣልሰጥም ብለህ ብትሸፍት ደግሞ የምትወዳት ልጅህን ኣባት ኣልባ ታደርጋታለህ ፡፡ ወይ ፍቅር ወይ እህል ታስርባታለህ፡፡ እና እንዲህ ኣይነቱን ስሜት እንዴት እንደምትገልጸው ግራ ገብቶህ ኣያውቅም? ደግነቱ፤ ኣዝማሪው በኒህ ጉደኛ ስንኞች ያግዝሃል፡፡
እንዳይቀር- ነዶ
እንዳይሄድ- ወልዶ
እንዴት ያለው ጀግና ቀረ ተጨማዶ

3 Comments

  • አለነው ውለታው commented on August 9, 2015 Reply

    የተከበራችሁ ሸገር ብሎጎች፣
    በእውነት ልባዊ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ፡
    እኔ አይነ ስውር ነኝ። መጽሃፍትን በጓደኞቼ መልካም ድጋፍ ካልሆነ በስተቀር የማንበብ እድሉ የለኝም። ሁል ጊዜ ሰው ለምኖ መጽሀፍትን ያክል ነገር ማንበብ በጣም ያስቸግራል። \
    ይሁን እንጂ በኮምፒውተር ላይ አማርኛንም ሆነ እንግሊዘኛን ለማንበብ የሚረዳኝ ሶፍትዌር በመኖሩ በድህረ ገጽ ላይ ያሉ ጽሁፎችን ያለ ማንም ድጋፍ አነባለሁ፣ አስተያዬቴንም የምጽፍላችሁ ራሴ ነኝ።
    ውድ ሸገሮች የጡመራ ገጻችሁ እጅግ በጣም ቃል በሚያጥረኝ ደረጃ ምርጥ፣ የምርጦች ምርጥ ነው።
    በርካታ ብሎጎችን አነባለሁ፣ እንደ እናንተ ያለ የተደራጀና ቀላል የሆነ ብሎግ ግን አላየሁም።
    ለመሆኑ ለልፋታችሁ ክፍያችሁ ምን ይሆን፧ እኛ ድንቁርና የተጫነን ብዙ ኢትዮጵያዊያን ከብሎጎቻችሁ ተጠቃሚ ነን። ለገጻችሁ ቀጣይነትም የሚገባችሁን ሁሉ ተመኘሁ።
    መቼም አንባቢ ትልቁ ሀብት ቢሆንም ብቻውን ግን አስቸጋሪ ነው፣ ስራችሁን ለመቀጠል የሚገባችሁ የገንዘብ ጥቅም ሁሉ ይገባችኋልና።
    ቀጥሉበት አቦ

    • Admin commented on August 14, 2015 Reply

      ውድ አለነው
      የሰጠኸን አስተያየት እጅግ በጣም የሚያበረታታና ልብ የሚነካ ነው፡፡ የብዙሃንን ፍላጎት ልብ ማርካት የሁልግዜም ምኞታችን በመሆኑ እንደዚህ አይነት አስተያየት ይበልጥ እንድንተጋ ያደርገናል፡፡ እናመሰግናለን!!

  • መሲ commented on August 23, 2016 Reply

    እንወዳቹሃለን

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *