. . . እየተስለመለምኩ ፊትዋን በእጆቼ ያዝኩ። አሟልጮኝ እንደሚወድቅ ሁሉ። እንደሚፈስ ሁሉ።
ፊቴ ገነት ላይ ወደቀ –
አፌ ውስጥ ከንፈሮቿን እንደቢራቢሮ ክንፎች (እንዲህ የሚቀስሙት አበባ ላይ አርፈው ምናልባትም በወለላ ሰክረው ልባቸውን ነስቷቸው እያሉ ክንፎቻቸውንም እንደመፅሐፍ ገጾች ገጥመው – በቀስታ ከበስተሁዋላቸው ተጠግቼ በአውራ ጣቴና በአመልካች ጣቴ አጣብቄ እንደማጠምዳቸው) ይዤአቸዋለሁ።
በገላዬ ውስጥ አየር እንደሚያልፍ ሁሉ ነበር።
እንኮይ እንኮይ ከሚል . . . . . . . ውሃ እናቶች ከሚከናበሉበት የአምቦ ምንጭ ውስጥ እንደተኛሁ ነበር።
አይኖቿ ወተት መሃል እንደወደቁ አጋሞች ነበሩ።
ልቤ እንዳይፈነዳ እጸልያለሁ፤ ልቤ እንዳይፈርስ እንቀጠቀጣለሁም።
ጣቶቼ በጀርባ ቆዳዋ ላይ ተማስለው እንደተኙ ነበሩ።
ደማችን ተደባልቆ ሲፈስ – ፈረሰኛው ከተራሮች በላይ ነበር።
መዝፈን አማረኝ።
እንደ ጥላሁን መጮህ አማረኝ።
እንደ አስቴር መተከዝ አማረኝ።
እንደሙሉቀን መጨፈር አማረኝ።
ከእግሮቻችን ስር የዚህች ከተማ የልብ ምት ከተቀበረበት ይሰማኛል።
የዚህች ከተማ የልብ ምት ከተቀበረበት ይሰማኛል።
የዚህች ከተማ የልብ ምት ከተቀበረበት ተሰማኝ መሰል።
በከንፈሮቼ ተሰማኝ መሰል።
በጉበቴ፣ በጣፊያዬ ተሰማኝ መሰል፣
በብልቶቼ ሁሉ ተሰማኝ መሰል።
ገና ከሩቅ እንደሚሸት
ትኩስ
ሕብስት
ነበረች።
ይቺ ልጅ ተጣጥፋ አፌ ውስጥ እንደ ናና ከረሜላ ነበረች።
ናናዬን አገኘሁ
በፍቅር ልምጠጣት፣
መይሳው ዕድል ነው
ወደ እኔ ያመጣት።
ከዚህች አስደሳች የሚገድበኝ ማን(ምን) ነበር?
ከዚህች ከገነት የሚያቆመኝ ማን(ምን) ነበር?
እግዚአብሔር ተመልሶ እስኪመጣ እስከ ፍካሬ ኢየሱስ አቅፌአት ልጠብቀው ተመኘሁ።
ልቦቻችን እጆች ቢኖሯቸው ደረቶቻችንን ሰብረው ወጥተው ያጨበጭባሉ።
…….. እንዴት ይቀላል ፍቅር! ደ’ሞ እንዴትስ ይከብዳል!
እንዴትስ ትንሽ . . . ደ’ሞ እንዴትስ ትልቅ ነው።
አንጀቴ እስዋን ምን ላድርግሽ? አላት …….. አንጀቴ በእርዝመቱ ተንሰፈሰፈ …….
ምናለበት ትንሽ በሆንሽ? ……. ምናለ እጆቼ መሐል ሀባ ዘቢብ ብትሆን ኖሮ…….
ውጬአት ብተነፍስ ተመኘሁ …….
ቢሉኝ –
ውጠሀት እንደሆን ትፋት እንያት
ምድር ላይ ያለችው እሷው አንዲት ሴት
ቆዳዬ ስር በደም ሥሬ ግድግዳዎች ላይ እንደረቂቅ ነገር ተሸክሜአት እንደምዞር ገባኝ …….
ቆዳዬ ስር ደም ሥሬ ግድግዳ ላይ ከውስጥ ተለጥፋ……
አይፍቁኝ፣ እሷን አይበጡኝ ነገር።
……… እየተስለመለምኩ ፊቷን በሁለት እጆቼ ያዝኩ። ሾልካ እንደምታመልጠኝ ሁሉ፣
ኮለል ብላ እንደምታመልጠኝ ሁሉ …….
ፊቴ ፊቷ ላይ አረፈ …….
***
ግራጫ ቃጭሎች