ዜጎቻችን ቀጠሮ ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ቢደመር ለፍርድ ቀን፡ በዓለም የመጠናቀቂያ ዕለት የተከመረ ሐጢያት ሆኖ መንግስተ ሠማያት የሚባል ቦታ አንድ ሀበሻ አይገባም ነበር።
መልካም ቀጠሮ አክባሪዎች በእግዜር ቀኝ ሲሰለፉ፤ 80ሚሊዮን የሚደርሰው ሀበሻ በጠቅላላ በእግዜር ግራ። ግራ ይግባንና።
የማይገባኝ ግን ምክንያቱ ነው። ስድስት ሰዓት ላይ ተቀጥረህ 6:05 ከመጣህ የአገሪቷ እድገት በ 5 ደቂቃ ዘገየ ማለት ነው….. ቢያንስ።
ስለ አገር ማደግ ወይም መንቀራፈፍ እንርሳና …የእኔ የግል ጉዳይ ስላልሆነ……… ስለዚያች ፉሲ የሴት ጓደኛዬ ላውራችሁ……..
ሁሉ ነገር አሟልታ የቀጠሮ ነገር ግን ተሳክቶላት አያውቅም።ብዙ ጊዜ የራሴ ትዕግስት ይገርመኛል። አስራ አንድ ሰዓት ተቀጣጥረን 12:00 ላይ ትመጣለች። ጊዜው ደግሞ እያጫወተ ያልፈኛል። 5…10… 15… 20… 30 ደቂቃ እያለ ሙሉ ሰዓት። ለመንፈቅ ሳውቃት አንድ ጊዜ እንኳን ቀጠሮ አክብራ መጥታ አታውቅም። የፈጠነች ዕለት 20 ደቂቃ ዘግይታ ትመጣለች። ያኔ ኩራት ኩራትም ይላታል።
ከቴም ተኮራ።
ዛሬ ግን ተማርሬ ነው የመጣሁት። የመጨረሻ መለያያችን ቀን ነው ብዬ …… ያው ለራሴ። ብዙ ጊዜ ነግሬያት አልሰማ ብላኛለች። ትምህርት የሚመልሣት አይነት አይደለቸም።….
ቆይ አንድ ነገር ሳልረሳው በፊት ልወሽክላችሁ።
ሌላ ወዳጅ አላት።
ብሔራዊ ትያትር አጠገብ ከሚገኘው ባንክ ውስጥ የሚሰራ…ቀይ ፊያት መኪና አለው። ወዳጅዋ እንደሆነ ስጠይቃት ‘ምነው አንተ እስከዚህ?’ ትለኛለች።
አታምኑኝም እንጂ አብረን ሆነን አንገቷን ሳሸተው የብር ጠረን አለ። ሰውየው ቴለር ሳይሆን አይቀርም።
እሱ ስለኔ መኖር የሚያውቅ አይመስለኝም። ቀጣፊ መሆንዋን ስለምታውቅና በዐይኔም ስላየኹዋት ስለእሱ ሳነሳባት …. ‘የወንድሜ አብሮ አደግ ጓደኛ ነው።እንተዋወቃለን’ ትለኛለች። ከዚያ ደሜ ይፈላል።
‘እያወቁ መሸወድ አለ እንዴ? ቂል ነህ? አትረባም እንበልህ? ትሉኝ ይሆናል።
አላያችኋትማ!!
በመጀመሪያ እንዲህ ፊት ለፊት የተከሰተውን ዕውነትና፤ ከካይሮ እስከ ፕሪቶሪያ መላ አፍሪካ ያየውን ዕውነት ሞልጫ የመካድ ችሎታ ብቻ ሳይሆን ሳታፍር ማሳመን ትችላለች።
‘ኔልሰን ማንዴላ የሰፈራችን ሰው ነበር። አባታቸው ጎረቤታችን ናቸው፣ በዙ ይባላሉ፣ አውቀው ደብቀውት ነው እንጂ ሙሉ ስማቸው ሞንዳላው በዙ ነው’ ብላ ድርቅ ማለት፤ መዋሸት፤ መከራከር ከተፈለገም እስከ አራተኛው ሚሊኒየም ሳትረሳው መዋሸት ትችላለች። እኔ ባላምናትም እንኳን ሌሎችን ስታታልል ሳይ ባግራሞት እሞላለሁ።
ከዚህ በፊት ያወጣችውን ሰው አብሮኝ ቢያገኛት ፍጥጥ ብላ ‘አጎቴ ነው’ ካለች ለረጅም ጊዜ ሳትረሳው አጎቷ ማድረግ ትችላለች። አጠገቧ ቆሜ ድርቅ ካልኩ አጎቴ ነው ያለችውን ሰውዬ ‘እማማ ደኽና ናት?’ ብላ ትጠይቀዋለች።
(አቦ እናቶቻቸውን አይተዋወቁም እኮ!)
“እስዋን ያልተሳፈራት የለም” ሲሉኝ።
“ያላገኛት ወሬኛ ሁላ ” እላለሁ። ….
ዛሬ እንደልማዴ አንድ ቦታ እየጠበቅሁዋት ነው። የምሰራው ስለሌለ ኒውስ ዊክ መጽሔት አነባለሁ። ከሴት ጋ ሳይሆን ከፈላስፋ ጋር ወይም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባልደረባ ጋር ፍጥምጥም የያዝኩ እመስላለሁ።
‘የሴት ፈላስፋ የለውም እንዴ? ‘ እንዳትሉኝ። አዎ የለውም። ቢኖረውማ ኖሮ እየተነጋገሩ ቀጠሮ ማክበርን ይለምዱ ነበር።
አምባሳደርስ አይሆኑም እንዴ? ሊሆኑ አይችሉም። ምክንያቱም ከጉዳይ እየዘገዩ ያበላሹብናል። ሲመረኝ አንድ ቀን ይህን አነበብኩላት
ቀጠሮ ማለት የሰዓት ልክ፣ የጊዜ ውሳኔ፣ ሰው ተገናኝቶ ጉዳዩን የሚፈፅምበት፣ ዳኛ ፊት ቀርቦ የሚነጋገርበት
ቀጠሮ አፍራሽ ማለት ቀጠሮ የማያከብር ፣ ተቀጣጥሮ የሚቀር….
እንዲህ እየዘረዘርኩ ልትሰማ ነው?