አይደለም ምኞቴ
ለምለም አንገትሽ ላይ : ክንዶቼን መጠምጠም
ዳሌሽ ላይ መንሳፈፍ: ጭንሽ ማሃል መስጠም
እይደለም ምኞቴ
ከንፈርሽን ማለብ
ቀሚስሽን መግለብ
ከገላሽ ቆርሼ :ገላየን መቀለብ
ደረትሽን ማለም
ጡትሽን መሳለም
በቁንጅናሽ ጅረት : ገነቴን ማለምለም
አላማየ አይደለም::
ምኞቴን ልንገርሽ?
ካለሺበት ቦታ: ቀልቤን ማሰማራት
ወትሮ ካንቺ ጋራ: ቡና መጠራራት
ሰላም መገባበዝ: ትዝታ መጋራት
የጨለመ ፊቴን : ባይንሽ ጮራ ማድመቅ
በቃላትሽ መስከን: በሳቅሽ መጠመቅ
በጎ መንፈስሽን :ካይንሽ ላይ መሻማት
ርጋታሽን ማጥመድ : ዝምታሽን መስማት::