ፈቅደን ሲመሩን፤ ችቦ ተቀባይ
ለሚነዱን ግን ፤ አሻፈረን ባይ
ካልነኩን በቀር፤ ቀድመን ማንዘምት
ከጋሻ በፊት ፤ ጦር የማንሸምት
ኢትዮጵያዊ ነን!
ህብር ያስጌጠው፤ ህይወት ለማብቀል
ዘር ሳናጣራ ፤ የምንዳቀል
ለነዱን ሰይጣን፤ ለመሩን ሰናይ
ጌታን ከገባር፤ ለይተን ምናይ፤
ኢትዮጵያዊ ነን!
ብዙ ህልሞችን፤ ወዳንድ ዐላማ
የሰበሰበ ገርቶ፤ ያስማማ
በደምና ላብ፤ ያቆምነው ካስማ
አገዳ አይደለም፤ የሚቀነጠስ
የዝምድናችን መተሳሰርያ
ሺ ጊዜ ቢከር፤ የማይበጠስ
ኢትዮጵያዊ ነን!
ምን ሆድ ቢብሰን፤ ምን ብንቸገር
እድር አይፈርስም፤ እንኩዋንስ አገር
ብለን በትግስት፤ የምንሻገር
ሲገፈትረን ፤ግፈኛና አጥቂ
ቁልቁል ሲሰደን ፤ሽቅብ መጣቂ
ለውርደት ሲያጩን፤ የምንጀነን
ኢትዮጵያዊ ነን!