Tidarfelagi.com

ሙገሳ ለሞጋሳ

በ1571 ገደማ በልዑል ፋሲለደስ እና በቦረን ኦሮሞ የገዳ ሰራዊት መካከል ጎጃም ውስጥ ጦርነት ተደረገ፤ ቦረኖች አሸንፈው ልዑል ፋሲል በጦር ሜዳ ላይ ወደቀ፤አሸናፊው የኦሮሞ አባዱላ ፤ ሱስንዮስ የተባለውን የልዑሉን ልጅ አገኘው።

በጥንታዊት ኢትዮጵያ በጦርሜዳ የተሸነፈን ምርኮኛ ትንሽ ትልቅ ሳይሉ መረሸን ብርቅ አልነበረም ፤ አሸናፊው ቦረን ግን መግደል ሲችል ምርኮኛውን ወደ ቤቱ ወሰደው ፤(!!! )” አንድ በሉ! ቤቱ ወስዶ አሳደገው፤ የሱስንዮስ ዜና መዋእል እንዲህ ይላል’ ” ወደደውም ፤ እንደ ወለደው ልጁም አየው ”

እንደባርያ፤ እንደ ህያው መሳርያ ሳይሆን እንደልጅ መሆኑን ልብ እንበል፤ ከጥቂት ጊዜ በሁዋላ ተሸናፊዎች በርትተው፤ ምርኮኛው ሱስንዮስን አስመለሱት፤ሱስንዮስ ከምርኮ ሲመለስ ኮስምኖ ገርጥቶ እንደ ጀሚ ላንስተር እጁን አጥቶ አልነበረም :: አቶ አፅመጊዮርጊስ የተባሉ መዝጋቢ የፃፉትን ልጥቀስ

“ (ማራኪው) በመልካም ያኖረው ነበረ፣ ከመንጋው አይለየውም ነበረ፣…
ቋንቋቸውንና ታላላቆችን ጀግኖች በክብር የሚዘፍንላቸዉን ያዉቅ ነበረ፡፡
ልማዳቸዉና ፍርዳቸው ገብቶት ነበረ፣ 3 ዓመት ከመንፈቅ ወይስ 5
ዓመት ኖረ ይላሉ አይታወቅም፡፡ ከምርኮ በተመለሰ ጊዜ 18 ዓመት
ይሆነዋል በብርቱ ፈረሰኛ ሆኖ ነበረ፡፡ ጦርነትም ለምዶ ነበረ አንበሳም ገድሎ፤ ቁንጮም ነበረው”

ሱስንዮስ ከአሳዳጊው ቤት የወጣው፤ በዘመኑ ለኑሮም ሆነ ለስልጣን ትግል ብቁ የሚያደርጉትን ፀጋዎች( qualities) ይዞ ነው፤ ከአማርኛ በተጨማሪ አፋን ኦሮሞ ቀስሙዋል፤ ብርቱ ፈረሰኛ ሆኑዋል፤ ፤ብርቱ ፈረሰኛ የጦር መላ አዋቂ እንዲሁም አንበሳ ገዳይ ሆኑዋል፤ ምርኮኛ ሆኖ ገብቶ የማራኪ ብቃት ይዞ ወጣ ማለት ነው🙂፤ከዚያ ወደረኞቹን አሸንፎ ዙፋን ላይ ተቀመጠ።

እንኩዋን የወንዛችን ሰው፤ ፈረንጅ ሳይቀር ሞጋሳ ይቀዳጅ ነበር፤ጀርመኑ ክራፍ፤ ፈረንሳዊው ሚካየል ዲአባዲ፤ ጥልያኑ አባ ታውሪን በሞጋሳ ኦሮሞ ከሆኑ ፈረንጆች መካከል ይጠቀሳሉ።

የማህበረሰቡ አባል ሆነው በማህበረሰቡ በረከት ተካፋይ ሆኑ ማለት ነው፤ ሞጋሳ ባእዱን ዘመድ የማድረግ ድንቅ ባህል ነው፤ ሌላው እንዲኖር መፍቀድ ነው:: ሞጋሳ ይገባዋል ሙገሳ!!

(ማሳሰቢያ፤ እቺን ሀሳብ በጨዋ ደንብ መሞገት መንቆር ይቻላል፤ በተረፈ፤ አፍ እላፊ፤ ኪቦርድ እላፊ አንቀበልም።)

3 Comments

  • Anonymous commented on March 9, 2020 Reply

    በ1571 ገደማ በልዑል ፋሲለደስ እና በቦረን ኦሮሞ የገዳ ሰራዊት መካከል ጎጃም ውስጥ ጦርነት ተደረገ፤
    የትኛው ፋሲለደስ?

  • አዱኛ ሙላቱ commented on May 30, 2020 Reply

    ሱስኒዮስ እንዲነግስ እራሱ ያገዙት ኦሮሞዋቾ ነበሩ። ውጊያህ ውጊያችን ነው በማለት መሆኑ ነው። አይደል እንዴ በውቄ?

  • አዱኛ ሙላቱ commented on May 30, 2020 Reply

    ሱስኒዮስ እንዲነግስ እራሱ ያገዙት ኦሮሞዋቾ ነበሩ። ውጊያህ ውጊያችን ነው በማለት መሆኑ ነው። አይደል እንዴ በውቄ?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *