Tidarfelagi.com

የቋንቋ ነገር

ለአዲሳባ ከንቲባነት ልወዳደር ወይስ ለክቡር ገና ልተውለት? ምን ያንሰኛል? ሌላው ቢቀር ሁለት ቋንቋ እችላለሁ – የአራዳና የገጠር አማርኛ አቀላጥፌ እናገራለሁ፤

የዛሬ አመት ገደማ ይመስለኛል: በካፒታል ሆቴል ጀርባ ባለው አቋራጭ መንገድ ሳልፍ ሁለት ጎረምሶች ይተናነቃሉ፤ ገባሁና ገላገልኩ፤ ሳጣራ አንዱ በቅርቡ ከታክሲ ረዳትነት የተቀነሰ ከተሜ ሲሆን ሁለተኛው ከገጠር የመጣ መፅሀፍ አዙዋሪ ነው፤ ምን እንዳጣላቸው ጠየኳቸው ፤

ከተሜው:-” መፅሀፍ ልገዛው በሰላም ቀረብኩት ፤ ጀለስ ለካ የመጨረሻ ፋራ! በቅርቡ በኮንትሮባንድ የገባች እንደሆነ አላወቅሁም የሾዳየን መጣመም አለባበሴን ከልማ ሃንግ እምሰራት መሰላት፤ የሌለ ተከመረችብኝ! ጭራሽ እንደ ቴርሞሜትር ቤቢቶውስ ከቶ አልጨመቀኝም! በዚያ ላይ ፤ ጣራው የተነሳለት ቤተመፀሀፍት ተሸክሞ የሚውለው ክንዱ የሌለ ፌሮ ነው! የቤቢቶው ኬሚካል ሳይደፋኝ ደርሰህ ስለገላገልከኝ አመሰግናለሁ “

ወደ መፅሀፍ አዙዋሪው ዙሬ ” አንተስ ምን ትላለህ?”

-“አየ ጌታው! የመፀሀፍቱን ነዶ አውርጀ የጫማየን ሲባጎ ላጠባብቅ ጎንበስ ስል ይሄ ግንጭላም የግንጭላም ልጅ ተሁዋላየ መጥቶ ተዘበበ ! አልፎሃጅ ይሆናል ብየ ዝም አልኩት! አድብቶ ዳናውን እንደ መብራት አጥፍቶ ተጠጋኝ፤ ተጠጋኝና በጃኬቱ ኪስ ስር ባለ ብረት ጠቆም አድርጎኝ ! “ አባ ያለሽን ከቻሳ አድርጊው “ አለኝ፤ ውጥንቅጡ የወጣ አማርኛው ባይገባኝም ቀናለቀን ስዘርፍህ ተባበረኝ ማለት መሆኑን ግብኔ ነገረኝ ! ወይ አለመተዋወቅ ብየ በልቤ ስቄ ዝም አልሁ! “ አባው! ብቻየን እንዳልመስልሽ ለጀለሶች ምልክት ብሰጣቸው ከቻሳ ብለው አጉዋጉል ያደርጉሻል እያለ ቀባጠረ ፤ እኔ በወገን ልመካ ብል አባይ ማዶ በጥይት ወፍ የሚያረግፉ ዘመዶች አሉኝ፤ ግን ላንተ እኔ አላንስም! እግዜርን ታልፈራሁ እንደ አደፈ ጨርቅ ጨፍጭፌ አሰጣሀለሁ! ለነፍስህ ካዘንክለት ተዚህ ወግድ ብየ ቁርጡን ነገርኩት! እንዲህ አንድ አንድ ስንመላለስ ፤ጉርምቦየን ሊያንቀኝ ተንጠራራ፤ አልሞት ባይ ተጋዳይ ተጋፈጥሁት! ብቻ ሁለት ደቂቃ ሳይሞላ ብን ብሎ ጠፋብኝ! የት ገባ ብየ ወድያ ወዲህ ሳጣብር ክርክርየ (ብብቴ) ስር ተሰንቅሮ አገኘሁት! መጣህ ማርያም ታምጣህ ብየ ፤ ባለ በሌለ ሃይሌ እንደ ተልባ ሳሸው ፤ምላሱ እንደ ማግ ተጎለጎለ! እርስዎ እንደ ሊቀ መላኩ ደርሰው ባያስጥሉት ኑሮ በእጄ ላይ ጠፍቶብኝ ነበር! “

እኒህን አማርኞች አቻችላ የምትኖረውን አዲሳባን ለመምራት ከኔ በላይ ማን ይኖራል?

2
የሆነ ጊዜ ላይ አሜሪካ ውስጥ የሚገኝ አንድ ከተማ ጎበኘሁ፤ የተቀበለኝ ልጅ ጥሩ ልጅ ነው፤ አብረን ከሰነበትን በሁዋላ ግን እንዲህ አለኝ “ በውቄ! to be honest with you እንግሊዝኛ ስትናገር እንደ ግእዝ ነው፤ስለዚህ የምትፈልገውን ነገር ለኔ ንገረኝና አስተረጉምልህለሁ”
እየመረረኝ እሺ ብየ ተስማማሁ ፤
የሆነ ቦታ ስንደርስ ካፌ ውስጥ ይዞኝ ገባና
“ምን ልዘዝልህ አለኝ?
“ በዝንጅብል የፈላ ሻይ “ አልኩት፤
ራሱን እያከከ ለረጅም ደቂቃ ቆየ ፤
ተግባብተናል፤
በመጨረሻ እንዲህ አለ፤
“ እዚህ አገር ዝንጅብል አያውቁም፤ ሌላ ነገር እዘዝ”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *