በቀደምት ቴክሳስ ከተማ የበረዶ ውሽንፍር ጥሎ የከተማው መብራት ተቁዋረጠ፤ በማግስቱ የከተማው አስተዳዳሪ ደውሎልኝ ለከተማው ህዝብ ልምድ እንዳካፍል ጋበዘኝ። “ያለመብራት የመኖር ጥበብ“ እሚል ጥናታዊ ፅሁፍ አዘጋጀሁና ናሙናውን ላክሁለት፤ በጣም ተደስቶ መጠኑን እዚህ ገፅ ላይ የማልገልፀውን ቀብድ ላከልኝ ፤ በህይወቴ ለመጀመርያ ጊዜ የኢትዮጵያ መብራት ሃይል ውለታ እንደሰራልኝ ገባኝ ፤ ጭራሽ ቴክሶች፥ ፅሁፍህን ከማቅረብህ በፊት ቢልቦርድ ላይ ልናወጣህ እንፈልጋለንና ፎቶ ላክ አሉኝ፤ ፓስፖርት ሳይዝ ላክሁላቸው።
ጊዜው ደርሶ ነድቼ ሄድኩ፤ ከተማው በር ላይ የኾቪድ መርማሪ ግብረሃይል ተቀበለኝ፤
“ከየት ነህ?” አለኝ ዶክተሩ
“ከኢትዮጵያ “ አልሁት’
“ የጠራኸው አገር ከደቡብ አፍሪካ ምን ያህል ይርቃል? ”
“ እረ ጎረቤት ነን ፤ እሳት እንጫጫራለን”
“ እዚህ ስራህ ምንድነው?” አለችኝ ነርሲቱ፤
“ ቻተም የተባለ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ እሰራለሁ” በማለት በደፈናው ላልፍ ስል
“ የስራ መደብህ ?’ ብላ አፋጠጠችኝ፤
፤“ የዩንበርሲቲውን ማህበረሰብ በየአቅጣጫው አሰማራለሁ”
“ ኦ! የዩንቨርሲቲው አስተዳዳሪ ነህ?”
“ በምን እድሌ! የካምፓሱ አውቶብስ ሹፌር ነኝ”
ወድያው ዶክተሩ የትኩሳት መለኪያ አነጣጠረብኝ ፤
በዚህ አላበቃም ፤የሆነ ትልቅ ግራምጣ ነገር አፍንጫየ ቀዳዳ ውስጥ ውስጥ ሰምድዶ ሊያማስል ሲቃጣ፥
“ ተው ! ነስር አለብኝ! ምንም ቢሆን ለሰው አገር ደሜን አላፈስም” ብየ ተቃወምሁ፤
“ ምን ይሻላል? ”
“ ለምን በሌላ መንገድ አትመረምሩኝም? ”
“በምን መንገድ?”
“ የሆነ ምግብ ስጡኝና የምግቡ ጣእም ከጠፋብኝ ተይዣለሁ ማለት ነው”
“ እሺ ምን ይምጣልህ? ”
“ እኔ ነኝ ያለ የጣልያን ቲማቲም ስልስ ይምጣልኝ ፥ በላዩ ላይ የህንድ ቂጣ ጣል አድርጉበት ! የተጠበሰ የቬትናም አሳ ከተገኘ እሰየው ነው ! ካልተገኘ ሰለሞን ፥ ማለቴ ሳልመን ጥበሱልኝ ! ደረቅ ይበል ታድያ! በቀኝ ጎኑ አቮካዶ ሳንዱች ፥ በግራ ጎኑ የበቆሎ እሸት ቅቅል ሻጥ አድርጉበት ፥ ድንች ዝልዝሉ አያስቸኩልም፥ ከላዛኛው ቀጥሎ ሊመጣ ይችላል፤’”
ነርሲቱ አድምጣኝ ስታበቃ ትንሽ ተካክዛ እንዲህ አለች
“ አሁን ከተናገርከው ተነስተን hyperphagia የሚል በሽታ እንዳለብህ መገመት ችለናል፤ የዚህ በሽታ ዋና ምልክት ጅብ የሚያስንቅ የምግብ ፍላጎት ነው ! ለማንኛውም ለጊዜው ጣእም መለየት አለመለየትህን ቼክ ለማድረግ በጀታችን የሚፈቅደው ይሄንን ነው” አለችና አንድ ዘለላ ጦር ማስቲካ አውጥታ ሰጠችኝ ፤ ከዚያ ምን አጋጠመኝ? የፊጥኝ ይዘው መረመሩኝ ? ወይስ እንዴት ሆንኩ? ተከታዩን በሚቀጥለው ፅሁፍ ይጠብቁ ይሆናልኮ መቸም እርም የለዎትም!