ምኞት፥ ስለ ለመጪው አሮጌ ዐመት

አዲስ ሆኖ ይምጣ፤ መጪው አሮጌ ዐመት
ሰው በውድ ይገመት
እህልና ሲሳይ በርካሽ ይሸመት።

በጦም በፍስክም፥ ዱላ ለምንጠግብ
ጨቅላ ልጅ አስርበን፥ ጆፌ ለምንመግብ
ሰላም ይለግሰን
ከለታት አንድ ቀን ፥ የሰው ወግ ይድረሰን።

ያርሶ በሌ ልጆች
በእንግዳ ሰው እጆች
ሳናረጅ ከመጦር፥
ይሰውረን ከጦር
-ያስጥለን ከበቀል
እንደ ድንኳን ችካል
አመሻሽ ተተክሎ ፤ ጠዋት ከመነቀል ።

በእልህ ምትክ መላ
ልባችንን ይሙላ ።

ጉልበቱን ለሚያመልክ ፤ ጉልበቱን ያቅልጠው
ለደግ ሰው አክሊል
ለክፉ ልብ ይሰጠው።

ይፍለቅ ከየመስኩ
የርህራሄና የማስተዋል ጠበል
ቃል ምግባር ይወልዳል ፤ አሜን! ይሁን እንበል!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *