ከባለንጀሮቼ ጋራ ስናወራ “ እኔኮ ዲያስፖራ አይደለሁም፤ ተመላላሽ፥ ሲራራ ነኝ “ እላቸዋለሁ፤ እነሱ ግን ”እሳት ካየው ምን ለየው“ ብለው በግድ በዲያስፖራነት ይመድቡኛል፤ እሺ ለዛሬ በነሱ ሀሳብ ልስማማና ልቀጥል።
ባለፈው መንግስት ዲያስፖራውን አትመጣልኝም ወይ” እያለ ሲጀነጅነው አልነበር?! ብዙ ወዳጆቼ ልባቸው በጅንጀናው ቀልጦ ለገና በአል ትኬት ቆረጡ፤ እኔም ግፍ-ያው ትንሽ ቀለል ሲል ለመድረስ ብየ ለጥምቀት ቆረጥሁ፤ ይህ በእንዲህ እያለ“ ከውጭ አገር ለሚመጡ እንግዶች ያርሶ አደሩን ሰብል የሚሰበስቡበት እድል መመቻቸቱ ተገለጸ”! የሚል ዜና ለቀቁብን፥ እንዴት እንዴት ያለ ነገር ነው! ቀድማችሁ ብትነግሩን እኮ ደርዘን አይፎን ከገዛንበት ቀንሰን ዘመናዊ ማጨጃ እንሸምት ነበር፤ በበኩሌ አርሶ አደሩን ለማገዝ ሁሌም ዝግጁ ነኝ፤ ግን እድሜን ከግምት ያስገባ ስምሪት ቢደረግ አሪፍ ይመስለኛል፥ ከአርባ አመት በላይ ያስመዘገብን ሰዎች ከሰብል መሰብሰብ ወጣ ያለ ስራ እንዲፈለግልን ጥሪየን በማቅረብ ምክንያቱን አስከትላለሁ።
ባለፈው ቀኑን ሙሉ የመዋእለ ሕጻናት ማቲዎች የሚነጫጩበትን አውቶብስ ስነዳ ዋልሁ፤ አመሻሽ ላይ ጫማ ለማስር ጎንበስ ብል ዲስኬ ተንሸራተተ፤ እና አሁን በዚህ እድሜ ዲስኬን ልሰብስብ ወይስ ሰብል ልስብስብ? የሌላውን አላውቀም! በበኩሌ ከተፈቀደልኝ ሰብሉ ተሰብስቦ እስኪጠናቀቅ ደመናውን ቆልፎ የመያዝ አገልግሎት ልሰጥ እችላለሁ።
ዲያስፖራው ሚሊዮን ሆኖ ይመጣል ሲባል ከህብረተሰቡ ዘንድ ቢሊዮን ምላሾችን እያየን ነው፤ ባለፈው አንዱ “ወደ አገር ቤት የሚመጡ እንግዶችን በነጻ ከኤርፖርት ወደ ማረፊያ ቤት ለማመላለስ ዝግጅቴን ጨርሻለሁ” በማለት ሲናገር ሰማሁት፥
ቀድሞ የገሰገሰ ወዳጄ ከቦሌ አየር ማረፍያ እንደ ወረደ ሰውየውን ደውሎለት ተሳፈረ፤ ሰውየው ዲያስፖራ እናቱ ቤት ካደረሰው በሁዋላ አይን እና እጁን እያፈራረቀ ይሾፈው ጀመር፥
“በነጻ ነው አይደል?” አለ ወዳጄ!
“አዎ! ግን አገልግሎቴ ከተመቸህ ደስ ያለህን ክፈለኝ፥”
እኔ እምለው፤ አንዳንድ ነዋሪዎች በዲያስፖራው ላይ የሚያወርዱት ነቆራ ትንሽ ልኩን አላለፈም? በቀን በሌት፥ ሶስት አራት ስራ እየሰራ ያገራችንን የኢኮኖሚ ዋልታ የሚደግፍ ግዞተኛና ስደተኛ የውለታው ምላሽ ይሄ ነው? እኔ አሜሪካን ከግር እስከ እምብርቱ አይቻለሁ፤ የ“ኩበት ሽታ ናፈቀኝ” እሚል ዲያስፖራ ገጥሞኝ አያውቅም፤ ኩበት እሚናፍቅ ከሆነ ደግሞ ኢትዮጵያ ድረስ መሄድ አይጠበቅትም፥ አሁን እዚህ አሜሪካ አምሽ እሚባል እልም ያለ ገጠሬ ማህበረሰብ ይገኛል፤ ዲያስፖራው ከፈለገ ወደ Amish ነድቶ፤ እበት በኪሎ ሸምቶ በማይክሮዌብ ሞቅ አድርጎ ማሽተት ይችላል፤ አንዳንዶች ደግሞ ዲያስፖራውን ጭንጫ ሰገጤ አድርጎ መሳል የሚሄዱበት ርቀት ያስመንናል፥ በበኩሌ በየዞርኩበት ከተማ ሁሉ ከብሩህ አእምሮ እስከ ምርጥ ምግባር አስተባብረው የያዙ ዲያስፖራዎች ገጥመውኛል፤ በርግጥ አለፎ አልፎ ከስንዴ መሀል ቦለቄ አይጠፋም፤ በቀደም ለምሳሌ አንዱ ሀበሻ ዩቲዩብ ላይ “የጎሬላ ውጊያ” የሚል ርእስ አንብቦ ምናለኝ” ጎሬላ ካላማጣ ምን ያህል ትርቃለች?”
አስተውላችሁ ከሆነ የነቆራው ባለቤቶች በሴት ዲያስፖራዎች ላይ አይጨክኑም!
ከላይ ከላይ ሲታይ፥ በዲያስፖራና ባልደሰፖረ መካከል ይመስላል እንጂ ውስጥ ውስጡን በዲታ ወንድና በቺስታ ወንድ መካከል የነበረ እና የሚኖር ፉክክር ነው ፤ ዲያስፖራው ዶላር አለው፥ በሀያል አገር የመኖርያ ፈቃድ አለው፥ እኒህን አስማቶች ተጠቅሞ ሴቶቻችንን ያስኮበልልብናል እሚል ስጋት የወረራቸው ሰዎች አሉ፤ እኒህ ሰዎች ዲያስፖራውን ጭንጫ ሰገጤ አድርጎ በመሳል የመታጨት አቅሙን ለማውረድ ይታገላሉ።
በዲያስፖራና በአገር- በቀል መሀል ያለውን ይህንን ስውር ውድድር ስመለከት አንድ ነገር ትዝ ይለኛል፤ ልጅ እያለን ደብረማርቆስ ውስጥ ትልቅ ደመወዝ ተከፋዮች የግብርና ድርጅት ሰራተኞች ነበሩ፤ እና ቅዳሜ ምሽት ወደ አንድ ዝነኛ ባር ጎራ ብለው ሌላውን እንቁልልጭ እያሉ በሰፊው ይዝናናሉ። አልፎ አልፎ ደግሞ ለቡና ቤት ወይዛዝርት ዳጎስ ያለ ክፍያ በማቅረብ ይጠቀማሉ። ጥቂት ቆይቶ የፊላንድ ተራድኦ ድርጀት ተከፈተ፥ ፊኒዳ ይባል ነበር፥ የፊኒዳ ሰራተኞች የደሞዙን ሪከርድ ሰበሩት፤ ለቡናቤት ወይዛዝርት የሚቀርበውን ክፍያ በእጥፍ አሻቀቡት፥ አንዳንድ የግብርና ሰራተኞች ወድድሩን ለማሸነፍ ኪሳቸውን ባዶ አድርገው እስከመግባት ደረሱ ፤
ይህንን ሁሉ ድራማ ጥግ ተቀምጦ ይህንን ይታዘብ የነበረው አየለ ጀንብ እግር የተባለው
የከተማው አውቆ አበድ እንዲህ አለ፤
“ፊኒዳ
በተመን …ዳ
አንተን አክል ብሎ ግብርና ፈነዳ፥”
ጃንሜዳ ላይ ያገናኘን!
One Comment
በጣም ገራሚ ስራ ነው