የወሎ መንፈስ አድናቂ ነኝ፤ ስለወሎ ሲነሳ ይቺ ወግ ትዝ ትለኛለች፤
አንድ ሼህ እና አንድ ቄስ ወደ መስጊድ እየሄዱ ነው፤ ምንም አገሩ ወሎ ቢሆን ቄስና ሼህ ባንድ ላይ ወደ መስጊድ ሊሄዱ አይችሉም ልትሉኝ ትችላላችሁ፤ እሺ በቃ ፥ ቄሱ ሼሁን ወደ መስጊድ እየሸኘው ነው፤ እንዲያውም ምን አጨቃጨቀኝ፤ ቄሱና ሼኩ ወደ ገበያ እየሄዱ ነው፥
“ቄሱ” አይዋ! እንዲያው በሰማይ ቤት ከክርስትያን እና ከእስላም ማን የሚኮነን ይመስልሀል?” ብሎ ጠየቀ
ሼሁ ፥ትንሽ ካሰበ በሁዋላ፥
“እንጃ ! ብቻ ተሁለት አንዱ አሩን የሚበላ ይመስለኛል” ብሎ መለሰ።
በተወሳሰበው ማህበራዊ ህይወታችን ውስጥ “የኔ መንገድ ብቻ ነው መዳኛ ብለው የሚያምኑ ሰዎችን ያህል አደገኛ የለም፤ “እንጃ ፤ ይመስለኛል፤..” የሚሉና ለሌላው እድል የሚሰጡ በእውቀታቸው ላይ ትንሽ ጥርጣሬ ነስነስ የሚያደርጉ ሰዎች ይስማሙኛል፤ አሁን መፈላሰፉን ትቸ ልዝብ ልዝቡን ላውጋ።
ስሙኝማ! የድሮ ሰው ብዙ ጊዜ ሀቀኛ ነው፤ ልቀደድ ካለ ግን ቀደዳውን የልብስ ሰፊዎች ማህበር ራሱ ተባብሮ አይሰፋውም ፤ ባለፈው ካንድ ያባቴ እኩያ የሆነ ሰውየ በኑሮ ውድነት ዙርያ በሚድያ ምን ሲል ሰማሁት ፡ “በኛ ጊዜ በግ ባምስት ብር ገዝተን ጮማው ቅርጥፍ አድርገን በልተን ቆዳውን ባምሳ ብር እንሸጠው ነበር።”
ተው ባክህ! በናንተ ጊዜ በጎች የነብር ቆዳ ለብሰው ነበር እሚወለዱት!?
በቀደም አንዱ ዝንጥ ያለ ሬስቶራንት ውስጥ ሽሮ ይበላል፤ ሽሮ የቀረበለት እጀታ ባላት ድስት ነው፤ ድስቲቱ የሸክላ ጭልፋ ትመስላለች፤
“ እንብላ” አለኝ
ሌላ ጊዜ “የተማረከ ይሁን” ብየ አልፍ ነበር ፤ ያንቀን ግን ፤
“ እሺ” ብየ የሸሚዜን እጅጌ ሰብሰብ ሳረግ፥
“ መጀመርያ እጅህን ብትታጠብ አይሻልም?”አለኝ ንዴት እና ተማጽኖ በተቀላቀለበት ድምጽ ፤
“ መታጠቢያው የትጋ ነው?” አልኩት፥
“ ከሬስቶራንቱ ትወጣና አስፓልቱን በዝግታና በትግስት ታቋርጣለህ፥ ከፊትለፊት ካለው ህንጻ አራተኛ ፎቅ ላይ አሪፍ መታጠቢያ ቤት ታገኛለህ”
” ከስፋልቱ ፊትለፊት ያለው ህንጻኮ ተሰርቶ አልተጠናቀቀም” አልሁት
“ ግዴለህም! አስፋልቱን እስክታቋርጥ ያጠናቅቁታል”
“ እሺ እዛ ገብቸ ታጥቤስ?”
“ ታጥበህ ወደ ቤትህ ሄድ”
የኑሮ ውድነት ሰውን ስስት ብቻ ሳይሆን ብስጭትም ለቆበታል፥ ሰልስትና (ከሶስት ቀን በፊት) የሆነ ክለብ ውስጥ አንዱ ጎጃምኛ ሲዘፈን ታዳሚው ጸጥ ብሎ ያዳምጣል፤ እኔ ነሸጥ አድርጎኝ ከወንበሬ ተነስቼ ክንዶቼን ፈርከክ አድርጌ መንቀጥቀጥ ጀመርሁ፤ ዘፋኙ ያበረታታኛል ብየ ሳስብ ዘፈኑን ገታ አድርጎ ፥የሚከተለውን ጣለብኝ ፤
“ወንድም ፤ በኔ ዘፈን ብብትህን እያናፈስህ ነው ?”