ስሙኝማ ! በቲቪ የኮመዲ ሾው እሚያቀርቡ ባለ መዋያዎች አሉ ፤ የአንጀራ ጉዳይ ሆኖባቸው ነው አንጂ በርግጥ አንዳንዶቹ መክሊታቸው ሌላ ነው፤ ወይ ጭራሽ መክሊት የላቸውም፤ እንደኔ እንደኔ፤ ልጆቻውን መክሊት ብለው ስም እንዲያወጡ ሊፈቀድላቸው አይገባም፤ እና ትንሽ የቸከ ጨዋታ ተረረር ያደርጉልንና በየሰክነዱ የብድር ሳቅ (laugh track ) ይለቁብናል።
ዠለሶች! የእናንተ ድርሻኮ እንደምንም ተጣጥሮ መቀለድ ነው፤ መሳቁን ማለቴ አለመሳቁን ለምን ለኛ አትተውልንም? ታዳሚ ነን ስንል ታማሚ አረጋችሁንኮ ! እስቲ አስቡት ! የሆነ ቁርስ ቤት ገብታችሁ እዚህ ግባ እማይባል ዱለት ቀርቦላችሁ እየበላችሁ ፤ ሼፉ አጠገባችሁ ቆሞ “ አቤት ዱለት! ልብ እሚያጠፋ ጣእም ! “ እያለ ቢያዳንቅ አይደብራችሁም? እንደዚያ አድርጋችሁ አስቡት እንጂ ! ( አይ በውቄ ! ገና ለገና ህዝብ በትብብር ሳቀልኝ ብለህ በወጣት ኮመድያን ላይ በድሮን ትዝምታለህ )
እኔ እምለው ! ዓውደ ዓመት በመጣ ቁጥር አንዳንድ የቲቪ ሰዎች፥ ስቱድዮአቸውን በግብዳ እጣን እንደ ጋን የሚያጥኑት ለምንድነው? አለሞቸ! የእጣን ዋና አገልግሎትኮ ለአፍንጫ እንጂ ለዓይን አይደለም፤ አንዳንዴ ስቱዲዮው የተቃጠለ መንደር መስሎ ፤ በጭሱ ውስጥ የሚርመሰመሱ ጋዜጠኞች ፥እየደነሱ ይሁን እየተደባደቡ መለየት ይከብዳል።
ሰሞኑን የገረመኝ የባህርማዶ ዜና አለ፤ የሆነ የፈረንጅ ጎረምሳ ጠመንጃውን ጥይት አጉርሶ ፥ መነጽር አልብሶ ፥ ዲብ ተንተርሶ ቢተኩስ ቻርሊ ከርክ የተባለውን ወግአጥባቂ ሰይፎ ጣለው፤ ከዚያ አንዳንድ ያገሬ ልጆች ‘ ነፍስህን ከሰማእታት ጋር ባጸደ ገነት ያኑርልን “ አይነት ነገር ሲጽፉ አየሁ፤ እንዴ ወለላው! ለመሆኑ እዚህ ተመዲናው ብዙ ሳይርቅ፥ በእገታ፤ በጥይት ፥ በጠኔ የሚተላለቀው ዜጋህ ሕይወት አሳስቦህ” ነፍስ ይማር” ብለህ ታውቃለህ ? ምን ልሁን ብለህ ነው ፤ ጥቁርን ከመጤፍ የማይቆጥር ፥ስደተኛን አጥብቆ የሚጠላ ወመኔ ተቀነሰ ብለህ ምሾውን የምታቀልጠው?
ይልቅ፥ አንዱ ወዳጄ ያደረገው የተሻለ ነው፤
አሜሪካን ኢምባሲ ቀጥሮው ደርሶ ለቃለመጠይቅ ቀረበ፤
“ለምን ጉዳይ ነው ወደ አሜሪካ የምትሄደው?” አሉት፤
“ለቻርለስ ከርክ ጉዳይ ነው”
“ማለት ?“
ዠለስ እንባውን ባይበሉባው እየጠረገ፥
“የቀብሩና ለሰልስቱ እንኩዋ ባልደርስ ለአርባው ልድረስ ብየ ነው”
“ የቤት ካርታ አለህ?”
“የለኝም ! ግን ደንኳኑ ውስጥ ከእዝንተኞች ጋራ የምጫወትበት ካርታ ይዣለሁ “
የኢምባሲው ሰውየ ምን አለ?”
“ ኮንግራጁለሽን ! የአምስት አመት ቪዛ እና ነጻ የአውሮፕላን ትኬት አግኝተሀል “