ቀኑ እንዴት ይመሻል ያንን ሳናነሳ

አዝማሪ ወርቄ (ሻምበል ወረቀት) እንዲህ ይል ነበር፤

“ቢናገሩ አፈኛ፤

ዝም ቢሉ ሞኝ

ቢወፍሩ ዝሆን፥ ቢቀጥኑ ትንኝ ‘

አወይ ሰው! አወይ ሰው! ሰው አስቸገረኝ”

ካዝማሪው የተረፈውን እነዲህ መዘርዘር ይቻላል-

ብትጋብዝ “ አባካኝ “ ትባላለህ- ብትቆጥብ “ ቁዋጣሪ” – ብታሞግስ “ አሽቃባጭ፥- ብትተች” አቃቂረኛ- ብትቀመቅም “ሰካራም” ባትቀመቅም “ አብሿም”- ሴቶች ቢቀርቡህ “አተራማሽ -የሴት ድሮን” ‘ – ሌጣህን ብትሆን “ስልብ “ ወይም “ ጌ”

ሸሸግ ብትይ “ ምነው ጠፋሽ “ – ብቅብቅ ብትይ” ምነው እዩኝ እዩኝ አበዛሽ “ – ባያምርብሽ “አመዳም “ -ቢያምርብሽ “ፊልተራም” ወይም “ዱቄታም” -ብትጨምቺ “ አንገት ደፊ አገር አጥፊ፤ “ ነጻ ብትሆኝ ‘ ሸሌ”

እንደ መካሪ ሲቃጣኝ እንዲህ እላለሁ-

በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ብትገኝ ከሰዎች ምዘና እና ካስተያየት አታመልጥም፤ የሚመዝን ማጉደሉ አይቀርም፤ ዠለስ! እንዳመጣጡ ኑር፤ ዠለሲት እንደፍጥርጥሩ ኑሪ፤ ልብሽን ተከተይ፤ ህግ እስካልጣስህ ድረስ ፥ ሰዎችን እስካልጎዳህ ድረስ ማድረግ የሚገባህን ከማድረግ አትቆጠብ፤

የሆነ ዘመን ላይ አንድ ባላባት ካድዋ ዘመቻ ተመልሰው በህዝብ ፊት ሲፎክሩ ደመቅ ያለ ፈስ አመለጣቸው ፤ ነዋሪውም በታላቁ ዘመቻ ላይ፥ አራት ጣልያን መግደላቸውን ቸል ብሎ ለአራት ሰኮንዶች ያክል አየር ላይ በቆየው ፈሳቸው ዙርያ በማውራት ተጠመደ ፤ ባላባትየው ለህዝቡ ጥሩ ነገር በመስራት ገጽታቸውን ለመገንባት ወሰኑ ፤ አስር በሬ አርደው የአገሩን ሰው ጠርተው አበሉት፤ “እኒያ አስር በሬ ያበሉት ጌታ” እየተባሉ እንዲነሱ ተመኝተዋል፤

ከተበላ ከተጠጣ በሁዋላ አንዱ አዝማሪ ብድግ አለና እንዲህ አቀነቀነ፥

“እንኩዋን አስር በሬ ቢታረድ ሰላሳ

ቀኑ እንዴት ይመሻል ያንን ሳናነሳ🙂

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *