መስመር መስራት ስትጀምር ወዲህና ወዲያን ትፈጥራለህ… አጥር መገንባት ስትጀምር ውስጥና ውጭ ትፈጥራለህ… ፍርድ መስጠት ስትጀምር ክፉና ደግ ትፈጥራለህ… በመስመር – አጥርና ፍርድህ ምክንያት የልዩነት ዜማ ሰርክ ይቀነቀናል… እንዲህ ‘የሆኑ’ እና እንዲያ ‘ያልሆኑ’ ክልል ይበጃል… ‘የኛ’ እና ‘የእነርሱ’ ምድብ ይሰራል።
ሕይወት ውብ ናት… የማሰብ መንገድ ግን ውበቷን ከልሎታል… ማሰብ ሁነትን ከአልቦ ላይ ይሰራል… ሁነቱ እኮ ሕላዌ የለውም… ማሰብ ግን ሕልውና ችሮታል… አማናዊዉ ሕልውና የሕይወት ብቻ ቢሆንም አዕምሮ በራሱ ቅዠት በፈጠረው ፎርጅድ ህላዌ ሰላሙን ያጣል።
‘ምንም አለመሆን’ እንዴት ጥሩ መሰለህ… አንድ ጊዜ በሕይወት መሆንታ ውስጥ መሆንን ሆነሃል… ከመሆን በኋላ አለመሆን የለም… ከመሆን በኋላ ሌላ መሆንም እንዲሁ… አዎን.. የሆንከውን መሆንታ የሚስተካከል መሆን የለም… ከሕይወት በላይ ምን ልትሆን ትችላለህ?… ምንም!!
አዕምሮህ ግን ሺህ ምንተሺህ መሆኖች አሉት… ስለዚህ ሰላም የለውም… ፍቅርን አያውቃትም… ሕይወት አትገባውም… የመሆን አሃዱን ፈጽሞ አልተረዳምና ከሆነው እውነት ይልቅ የሌለው ቅዠት ይመስጠዋል… ከራሱ ምናባዊ መሆኖች ጋር በፍቅር ስለወደቀ ከመሆንህ ተፋታ ብትለው እንኳ አይሰማህም… ቅኝቱን ፈጽሞ መለወጥ አይፈልግም… ‘የዘሬን ብተው…’
እስኪ አስበው ከመሆን እውነት በኋላ ስንት ባዶ ሁነት ፈጠርክ?… በዜግነት ‘እንትን’ ነህ… በብሔር ‘እንትን’ ነህ… በሐይማኖት ‘እንትን’ ነህ… በመደብ ‘እንትን’ ነህ… እንትን – እንትን – እንትን… ሁሌም ጥግ ማሻተት ትወዳለህ… እንዲሁ መቆም ያስፈራሃል… እርቃን የቀረህ ይመስልሃል… በሕይወት እውነት ላይ እምነት የለህም… ከማይንድ ቅዠት ጋር የሙጥኝ እንዳልክ ሰርክ ፍስሐ ይርብሃል።
የግጭት ሰበቦችን አጥና… የጦርነት መንስኤዎችን መርምር… የልዩነት ተረኮችን አስተውል… ከመሆን በኋላ ከሆነ ነኝነት የመነጩ ናቸው… ነኝ ላልከው ነኝነት ዘብ የቆምክ’ለት ነኝ ከሚሉ ቡድኖች ጋር ጸብ ውስጥ ትገባለህ… ‘ትክክል ነኝ’ ትላለህ – ‘ልክ አይደሉም’ ብለህ ትፈርዳለህ… ‘ጻድቅ ነኝ’ ትላለህ – ‘ኅጥዕ ናቸው’ ብለህ ትኮንናለህ… ምንም ካልሆንክ ግን ምንም ልዩነት አትፈጥርም።
ምንማዊነት ነው ምልዓት!! … ምንማዊነት ነው ሁሉን መሆን!! .. ምንማዊነት ነው ሕይወት!! … ምንማዊነት ወደ ቤትህ የሚወስድህ መንገድ ነው… ወደ ምንጭህ የሚያደርስህ መሪ ነው… ወደ ከፍታህ የሚመልስህ እርከን ነው… “Nothingness is the womb.” ~ Allan Watts
ያልሆንከው ስለሌለ ምንም መሆን አያስፈልግህም… ከሆኑ በኋላ ምንም መሆን የለም… ከሕይወት በላይ ምን ልትሆን ትችላለህ?
ምንም ካልሆንክ ምንም ላይ አትፈርድም… ምንም ካልሆንክ ከማንም ትሆናለህ… ምንም ካልሆንክ ጽድቅና ኩነኔ የለብህም… ምንም ካልሆንክ ጠላት አታውቅም… ምንም ካልሆንክ በቃ ምንም አትሆንም!!…
የተቃውሞ በትርህን ባነሳህ ጊዜ ሁሉ ይህን አስብ… ‘ምን ስለሆንኩ ነው ምንንታን የምወጋው?’ … ከመልስህ ‘የሆንከውን’ ስታውቀው ከቅዠትህ ትነቃለህ… “When I think I am, I find myself worthless. When I think I am not, I find my value.” ~ Rumi
ምንምነቴን ምንም አትበሉት… ምንምነታችሁን ምንም አይልምና!!
አቤቱ ምንምነቴን ባርክልኝ!!
ፍቅርን ከመስጠት በላይ ዕዳ አይኑርባችሁ!!
3 Comments
ድንቅ ገለፃ ነው ተባረክ
https://dildiy.wordpress.com
ሀሳቡ ደስ ይላል እውነታም አለው ግን ምንም መሆን እኮ ከባድ ነው ።
ምክንያቱም እኔነት በጣም ጠንካራ ግንብ ነው ።
ምን አልባት ትልቅ እኔነትን የ እሚገድል የ ህይወት አጋጣሚ ከ አልተገኘ ።