Tidarfelagi.com

ላንዲት ማስቲካ ሻጭ ህጻን

በደብተርሽ ምትክ
ትንሽ ሱቅ ታቅፈሽ
ካልፎሂያጅ እግር ስር፤ እንደ ድንቢጥ ከንፈሽ
ጋሼ ግዙኝ ስትይ፤ ኣንጋጠሽ ወደ ላይ
ለጉድ ተጎልቸ፤ ምታረጊውን ሳይ
ራሴስ ይታመም፤ ምላሴን ምን ነካው
ግራዋ ይመስል፤ መረረኝ ማስቲካው::
ኣፈር ጠጠር ለብሶ ፤በዶዘር ተድጦ
መስኩ ከነጎርፉ
ሰማይ ከነዶፉ
ለጌቶች ተሽጦ
ኣተር ነው እያሉ፤ ኣፈር ዘግኖ መፍጨት
ገነት ነው እያሉ፤ መስክ ላይ መፈንጨት
ጠበል ነው እያሉ፤ ተጎርፉ መራጨት
ይህንን ማን ሰጦሽ
ገና በልጅነት፤ ልጅነት ኣምልጦሽ፡፡
በምቢልታ በዋሽንት፤ በከበሮ ታጥሮ
በክራር ተማግሮ
በቆመ ከተማ
እምባሽ ቅኝት የለው ፤ለሰው ኣይሰማ፡
ጠዋት የፎከረ ፤ቀትር ላይ ሲረታ
ዛሬ ዝሎ ሲወድቅ ፤ትናንት የበረታ
ኑሮን ያህል ሸክም፤ ያላንቀልባ ሲያዝል፡፡
ምን ጸጋ ለብሶ ነው፤ ትከሻሽ የማይዝል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *