Tidarfelagi.com

መጠናናት

አንድ በድሜና በምጣኔ ሀብት የሚበልጠኝ ወዳጅ ነበረኝ ፤ አንዳንዴ በግድግዳ ስልክ ደውየ “ ለጥብቅ ጉዳይ ስለምፈልግህ እንገናኝ” ስለው ” ጋብዘኝ፥ ሊፍት ስጠኝ፥ ገንዘብ አበድረኝ፥ ዋስ ሁነኝ፥ ሽማግሌ ሆነኝ አትበለኝ እንጂ ለጥብቅም ሆነ ለላላ ጉዳይ ልታገኘኝ ትችላለህ ” ብሎ ይመልስልኝ ነበር ፤ እና እኔንም ፖለቲካ ጻፍ አትበሉኝ እንጂ ፌስቡክ ላይ ለማንዣበብ ቃል እገባለሁ።

“እስቲ አንዴ እንደማመጥ !” አለ የዳምጠው ሹፌር፤
ድሮ ከትዳር በፊት መጠናናት የሚባል ነገር ነበር፤ አባቶቻችን ውሃ አጣጫቸውን ሲያጠኑ “ሙሽራዋ የማን ልጅ ናት? ዶሮ መበለት ትችላለች? ቤተእግዚሀር ትስማለች ?” በሚሉ ጉዳዮች ላይ ብቻ ይወሰኑ ነበር፤ የሙሽራዋ መልክ ራሱ በጫጉላው ቀን ብቻ የሚገለጥ “Top secret ነበር ። ዛሬ ከትዳር ቀርቶ ከድርያ በፊት ያለው መጠናናት እጅግ በጣም ተራቋል፤

ባለፈው ባለቀ ሰአት ትዳር ውል ብሎብኝ እዚህ ጎረቤት አገር ካለች ቀንበጥ ጋራ እንዴት ነሽ እንዴት ነህ ስንባባል ባጀን። ባንድ ምሽት ድንገት “ከወገብህ በታች አወላልቀህ ፎቶ ተነስተህ ላክልኝ አለችኝ” ፤ ተገረምሁ፤ ብሎም ደነገጥሁ፤ ግን ስሜቴን ዋጥ አድርጌ ”ከወገቤ በታች ያለው ጓዝ ባንድ የሞባይል ፎቶ የሚወሰን አይደለም፤ ራሱን የቻለ የናሺናል ጆግራፊ ዶከመንተሪ የሚፈልግ ፕሮጀክት ነው፤ ባይሆን ከወገቤ በላይ አወላልቄ ልላካልሽና ገምግሚኝ” አልኳት።
በስንት ልምምጥ ተስማማች ።
አምሳ ፎቶ ተነስቼ፤ አርባ ዘጠኙን ደምስሼ አንዱን ሰደድኩላት።
“ሲክስ ፓክ አለኝ ብለኸኝ ነበርኮ”
“ ከራት በፊት ሲክስ ፓክ ነበረኝ፤ ከራት በሁዋላ ሲክስ ባግ ሆኗል “ አልኳት።
“No way! ሆድህ ትልቅ ያፈር ገንፎ ነው እሚመስለው “
“ደረቴ ላይ ብታተኩሪ ደስ ይለኛል ”
“ደሞ ሁለት እምብርት ነው ያለህ እንዴ ? ”
‘አንደኛው ትርፍ አንጀት ያስወጣሁበት ጠባሳ ነው ! ምናለ ደረቴ ላይ ብናተኩር”
“ኦኬ! ደረትህ ከየት ነው እሚጀምረው?”

ይሄንን አሳዛኝ ጭውውት ለቀጣዩ ላሳድርና ሌላ ገጠመኝ ላውጋችሁ።
በቀደም ዲሲ ኡበር ታክሲ እየነዳሁ አለምአቀፉን ማህበረሰብ ሳገለግል አንዱ አበሻ ተሳፈረ፤ ሰውየውን የት ነው የማውቀው እያልሁ እያሰበኩ ፊቱን ለጥቂት ደቂቃ አጠናሁት፤ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የሸግግር መንግስት ለመመስረት ተሰባስበው ፎቶ ከተነሱት አንዱ ወጣት መሆኑን ተገነዘብኩ ፤ ሰውየው ከሁዋላ ወንበር ለጠጥ ብሎ ተቀመጠ፤ አቀማመጡን በማየት ብቻ ለንግስና የተፈጠረ መሆኑን መገመት ይቻላል። ረጅም ሎጋ ከመሆኑ የተነሳ በቂጡ የቆመ ነው እሚመስለው፤ ጭራሽ በwhite house በዋይታ-ውስ በኩል ስናልፍ እጁን በመስኮት አውጥቶ አውለበለበ ። ለአሜሪካ አቻው ሰላምታ ማቅረቡ መሰለኝ። ሰፈሩ ሲደርስ ቀልጠፍ ብየ ወረድሁና በሩን እንደ ጋሻጃግሬ ከፍቼ “ እንግዲህ በመንግስትህ አትርሳኝ “ ብየ አሰናበትኩት። ቤቴ ደርሼ መኪናየን ስፈትሽ ሰውየው ሳምሶናይቱን ጥሎ መሄዱን ተረዳሁ ፤ ቦርሳውን ከፍቶ የማየት አሳብ መጥቶብኝ ትንሽ ከራሴ ጋራ ታገልኩ፤ ኢትዮጵያን እጣ ፈንታ የሚወስን ነገር በጄ ገብቶ ቢሆንስ ? የመጣው ይምጣ! ሳምሶናይቱን ስከፍተው ያገኘሁት ገረመኝ- አንድ ፌስታል ድርቆሸ፥ ስድስት ብልቃት ሚጥሚጣ; አንድ ፌስታል ኤልሳ ቆሎ፤ፌርሙስ የሚያክል የብብት ፊሊት… ከስር አንድ ወረቀት አየሁ፤ አሃ! ይሄ የሽግግር መንግስቱ ሰነድ ፥ አለዚያም የአዲሱ ህገ -መንግስት ረቂቅ መሆን አለበት ብየ ገለጥ አደረኩት፤ የኪራይ ቤት ውል መሆኑን ሳውቅ ግን እጢየ ዱብ አለ፤ እጢየን ወደ ነበረበት ሰቅየ ውሉን በጥሞና ማንበብ ጀመርኩ ፤ No shoe inside the house ይላል የመጀመርያው አንቀጽ፤
ከጥቂት ሰአታት በሁዋላ ሰውየው ሳምሶናይቱን ሊቀበለኝ ሲመጣ “ዠለስ! የሽግግር መንግስት ነው ፤ወይስ የችግር መንግስት ያሰብክልን? እስቲ ኢትዮጵያን ከመግዛትህ በፊት መጀመርያ ቤት ግዛ“ ብየ ገሰጽኩት !
ፖለቲካ አልጽፍም ያልኩትን ከምኔው ዘነጋሁት በሞቴ!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *