፩
“… ማሕሌት ሕይወትን ከልጅነቷ ጀምራ እንደ ፈቀደችው ያልኖረች፣ ዕጣ ፈንታዋ በጉልበተኛ ወንዶች ጫማ ሥር ያዋላት ልብ ሰባሪ ገፀ – ባሕሪ ናት።
በልጅነቷ ተገዳ የተዳረች፣
ከገጠር ሸሽታ ወደ አዲስ አበባ ስትመጣ በአጎቷ ጓደኛ የምትደፈር፣
ይህን ለማምለጥ ሥራ ብትቀጠር እንደ ቀደሙት ሁሉ በገዛ አሰሪዋ የምትደፈር
የተዋለባትን ግፍ ለማንም ሳታጋራ አምቃ የያዘች ሴት።
ከሦስቱ ሰይጣናውያን ወንዶች የተለየና እንደ ሰው ቆጥሮ ፍቅር ሰጥቶ የሚቀበላትን አፍቃሪ የምታልም ሴት –
ማሕሌት …
የከንፈሯ ውበት አድናቂ እና የአሰሪዋ ጓደኛ የሆነ ሠዓሊ እየተሳመች ሊሥላት በመሻት መቶ ብር ከፍሎ ሞዴል እንድትሆነው ሲጠይቃት ገንዘቡን ስለፈለገችው ትስማማለች።
ሰዓሊው ሥዕሉን ሸራው ላይ ሲያሰፍር ሶስቱ ደፋሪ ወንዶች የፈፀሙባትን ጥቃት እያሰበች፤ ሥዕሉ ላይ ያለው ወንድ ከእነርሱ የተለየና የምታልመው ንፁህና አፍቃሪ ወንድ ይሆን ዘንድ ትመኛለች።
እነርሱን የሚመስል እንዳይሆንም ሥዕሉ ላይ ያለው ወንድ ምን እንደሚመስል ደጋግማ ትጠይቃለች – ሠዓሊውን። ሂደቱ የተዋለባትን ግፍ አስታወሷት እንድታለቅስ እስኪያደርጋት ድረስ። ሠዓሊው እንዳታለቅስ ሲጠይቃት፤
“አይ የለም ላልቅስ። ሥዕሉ ላይ እንኳን ላልቅስ” ትለዋለች።
“ሸራው ፊት ለፊት ሔዳ ቆመች። እንዳ’ለች ሥሏታል።
(ካሰበችው በተቃራኒ) ሰውዬው እንደ ባሏ ጡንቻማ፣ እንደ ደፈራት ወንድ ነጭ ካኔቴራ የለበሰ እንደ አሰሪዋ ትንንሽ አይኖች አሉት።”
ማሕሌት …
በእውኗ ያጣቸውን በወጉ የሚስማት አፍቃሪና ዕንባ በሥዕል ላይ እንኳ ማጣቷ ከፈጠረባት ህመም ባሻገር፤ የበዳዮቿ እዚህም መከሰት በነዲድ ቁጣና የአመፃ መንፈስ ሞልቷት ሥዕሉን ሸረካክታው አንዲትም ቃል ሳትናገር ልብሷን ለባብሳ ትወጣለች።
ማሕሌት …
ታሳዝነኛለች”
*
ጀሚል ይርጋ
***
፪
ማሕሌት ሌላው ቀርቶ በገዛ ገላዋ ላይ እንኳ ፈቃድና ፍላጎቷን የመፈፀም መብት የሌላት እስረኛ ናት። ምን አይነት ወንድ ነው የምትስልልኝ የሚለው ጥያቄ የተደጋገመበት እስጢፋኖስ ፈቃዷን የመፈፀም ፍላጎት ባይኖረውም የይስሙላ ይጠይቃታል።
“ምን አይነት ወንድ ደስ ይልሻል?”
“ቀጭን ረዥም ለስላሳ ፀጉር ሴታ ሴት መልክ”
“አይሄድም። ላንቺ ለስላሳ ሰውነት፣ ላንቺ ውብ የሴት ሰውነት፣ ሴት የመሰለ ወንድ አይሆንም” (ገፅ፣ 39)
ከእስጢፋኖስ መልስ ይልቅ የማሕሌት ጥያቄ ገራገርም እንግዳም ይምሰል እንጂ እውነታው የዛ ተቃራኒ ነው።
ማሕሌትእድሜ ልኳን ከፍ አድርጌ በዘረዘርኳቸው የተባዕት እሴቶች በተገነባ ያልተገራ የአለም ጭብጥ ውስጥ ነው የኖረችው። የዚህን ዓለም ሸካራነትና ጨካኝነት የሷን ያህል የሚያውቅ የለም።
የማሕሌት ጥያቄ የዕሴት ለውጥ ነው። ተጫኝ የሆነውን የተባዕት እሴት (Hegemonic Masculinity) በለስላሳና ሚዛናዊ በሆነ የእንስት እሴት የመቀየር ጥያቄ።
ይህ ለስላሳ ዓለም እስካሁን ያየነው ተጫኝና ተጋፊ ዓለም ግልብጥ ነፀብራቅ (inverted reflection) ነው።
ተባዕቱ መለስለስ ሲሳነው ፈቃድና ፍላጎቷ የተገፋባት ማሕሌት ትሻክራለች። በዚህ እንግዳ ባህሪ የአቋመ ማህበሩ የሃይል አሰላለፍ ፍፁም ይፈተናል። ከመጠየቅ፣ ከመሟገት፣ እምቢኝ ከማለት አልፋ ተባዕት የገነነበትን ዓለም በገቢር ትጋፈጣለች። በሙሉ ሃይልና ስልጣን የተባዕቱን ዓለም አፍርሳ “እንግዳ ዓለም” እስከማበጀት ትደርሳለች።
“ሸራው ፊት ለፊት ሄዳ ቆመች። እንዳ’ለች ስሏታል። ሰውየው እንደባሏ ጡንቻም፣ እንደደፈራት ወንድ ነጭ ካናቴራ፣ እንደ ጌታዋ ትንንሽ አይኖች አሉት።
ስዕሉን ከተደገፈበት ጣለችው።
“ምን ነካሽ?!”
ሊይዛት እየሮጠ ወጣ። ብርድ ልብስ እላዩ ላይ ወረወረችበት። የስዕሉን ሸራ በምስማር ከተያያዘበት የጣውላ ጠርዝ እስከ መሃሉ ድረስ በአንድ ስንዘራ ሸረከተችው።
ሌላም ቀዳዳ – ሌላም ቀዳዳ – ሌላም።
ብርድ ልብሱን ከላዩ ላይ ጥሎ ቆሞ አያት። ሳይነጋገሩ ለባብሳ ወጣች።” (ገፅ 48)
የማሕሌት ምርጫና ውሳኔ የአንድ ነጠላ ድርጊት ሁነት ውጤት አይደለም። ይልቅም ‘አንድም’ ተብለው የሚፈከሩ ድርብርብ ፍቺዎች አሉት።
አንድም
ይህ ሶስት ቀን የፈጀ ጉዞ ነባሩን ምንትነትና ገድሎና ቀብሮ በአዲስ ምንትነት የመነሳት ነው። ጉዞው “ኤጀንሲ” የማበጀት ሂደት ነው። ከ ፍዝ ተሳቢነት (passive objectivity) ወደንቁ (አ)ሳቢነት (Active subjectivity) የተካሄደ ሽግግር ነው።
አንድም
በተለይ የነገረ ፍካሬያችንን ስልት አሌጎሪያዊ ካደረግነው ጉዞውን ውስጣዊ (Journey into imagination) አድርገን ማሰብ እንችላለን።
በሌላ ቋንቋ አዳም በፈጠረው ዓለም ውስጥ የሚኖር ገፀ ባህሪይ እስጢፋኖስ ብቻ ነው። ማሕሌት በክየና ሒደት በሰዓሊው እስጢፋኖስ ምናባዊ ዓለም ድንገት የተጣለችና ከምናቡ ጋር አብራ የተጨለፈች ምስል ብቻ ናት።
በክየናው ሂደት ውስጥ ሰዕሊው ሐሳቡንና ስሜቱን ለመቅረፅ ከቀለም ጋር ይታገላል። ከዚህ ሁሉ የሚልቀው ግን በሰዓሊው (እስጢፋኖስ) እና በራዕዩ (በማሕሌት አካል) መካከል የሚደረግ የ ልምራሽ-አልመራም፤ ከነጭራሹ እኔ ካልመራሁህ ዓይነት ዓይነ ሕሊናዊ-ዕዝነ ልቡናዊ (illusionary hallucinatory) ትንቅንቅ ነው።
በማሕሌት አሸናፊነት የተጠናቀቀው ትግል የልማዳዊና ዘመናዊው የኪነ ጥበብ ርዕዮተ ዓለም ፉክክርም ይመስላል።
ሁለቱ የትርጓሜ ቅጦች ተጋግዘው የሚጓዙ እንጂ ለብቻ የሚቆሙ አይደሉም። በዓለም የነገረ ኪን ልማድ ውድጥ ዛሬም ድረስ ከሚያከራክሩ ጉዳዮች አንደኛው በከያኒውና በተከያኒው መካከል ያለው የፈጣሪነትና የፍጡርነት፣ የአድራጊነትና የተደራጊነት፣ የሰጪነትና የተቀባይነት ነገረ ፆታዎ ሚና ነው።
ታዋቂዋ የስነ ፅሑፍ ሐያሲና የእንስታዊነት አቀንቃኝ ሱዛን ጎባር (Susan Gobar) እንደምታስረዳው
ወንድነት በተጫነው በዚህ ልማድ ውስጥ ብሩሽና ብዕር የወንድነት ትዕምርት (phallic symbol) ተደርገው ሲወሰዱ ሸራና ወረቀት ከሴትነት ጋር ይቆራኛሉ። ይህ አይነቱ የሚና አደላደል ሴትነትን ከነባሪነት ወደ ንብረትነት ስለሚያወርድ እጅጉን አድሏዊ ነው።
“This model of pen-penis writing on the virgin page participates in long tradition identifying the author as a male who is primary and the female as his passive creation – a secondary object lacking autonomy endowed with often contradictory meaning but denied intentionality. Clearly this tradition excludes woman from the creation of culture even as it reifies her as an artifact within culture”
ከፍ አድርገን ከልብ ወለዱ በወስድነው አስረጂ እንደተመለከትነው አዳም በማሕሌት አማካይነት ይህን አይነቱን ሚዛን የተዛባበትን ስርዓት ነው የበጠበጠው። ሱዛን ጉባር በምትተቸው ነባር ልማድና አዳም በቀደደው አዲስ ልማድ (ወይም በራዕዩ በማሕሌት) መካከል የሚያስደንቅዝምድናን እንመለከታለን።
ብርድ ልብሱ በደራሲው ‘ደርቢው’ ተብሎ የተሰጣት ነው። የማሕሌትን አዲስ ጉልበት፣ ሃይልና የሚና ለውጥ የምንገነዘበው በብርድ ልብሱ አወራወርና በሸራው አሸነታተር ነው።
በተወረወረበት ብርድ ልብስ ከሩጫው የተናጠበው፣ አቅሙን የተነጠቀው እስጢፋኖስ ቆሞ ከማየት ውጪ ምንም ማድረግ አይችልም። (የማሕሌትን ነባር ሚና ወስዶ ወደ ፍዝ ተሳቢነት ተለወጠ እንደማለት ነው።)
በዚህ ትዕይንት ውስጥ ነባሮቹ ፆታዊ ትዕምርቶች ሚናቸውን ያጣሉ። ማሕሌት ልማድ አፍርሳ ‘የፈጣሪነቱንም የፍጡርነቱን’ ሚና ወስዳለች። በአንድ ጊዜ ‘Subject’ም ‘Object’ም ሆናለች።
***
ተባባሪ ፕሮፌሰር ቴዎድሮስ ገብሬ
“አካል በአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ” የሚለውን ሙሉ ጽሑፋቸውን ለማንበብ ሊንኩን ይከተሉ፡
2 Comments
ሠላም ለሁላችሁ
አንድ ጥያቄ ነበረ ነኝ
የአዳም ረታን የemail አልያም የስልክ አድራሻ
አመሰግናለሁ
text