Tidarfelagi.com

…ምስክሬ ነው

ወላጅ አባቴ በእናቴ አሳቦም ይሁን አስመርራው ሸሽቶኝ ቢሄድም ይሄ ዓላዛር የተባለ የሽሮሜዳ ሸንኮራ እግሮቼን ተከትሎ ወደምሄድበት ሄደ፥ አረፍኩበት አረፈ፥ ሳቄን ሳቀ። አባቴ ወደ ቆላ ቢኮበልልም ዓላዛር እጄን ያዘኝ። ዘመናይ ለዘመናይ። እዚህች ደጋና ወይና ደጋ ሰላሜን አገኘኋት፥ አዚዬ በቁጭት የተጨበጠች ግራ እጄን ከፍቶ ግራ መዳፌ መሃል ትር ትር የምትል በፍጥነት የምትመታ ልቡን፥ ቀኝ መዳፌ መሃልም ማር ማር የምትል መሳሙን አስቀመጠ…..
ይሄን ይሄንን ፍቅር ስንጀምር ብዙ እንደ ደመራ የሚንቦገቦጉ ለአለምና ለሕዋው የተገለጡ ምስክሮች አሉ …..
ምስክሬ ነው፥
የከንፈሮቼን ንቅናቄ መሐላዬን ያነበበ ዕርግብ ይሁን ንስር ሽሮሜዳን ከተወለደ ጀምሮ ገና ከዕንቁላልነቱ ያነበበ። ዕውነቴን እንደነበር። ምስክሬ ነው ያ በራሪ…..
ምስክሬ ነው፥
የነፈሰብኝ የተነፈስኩት የነካኝ የነካሁት የዘፈንኩበት (ከቶ ሳላውቅ ይዞኛል ፍቅር ከእሷ ጠምዶኛል የተባለ ጊዜ) አደግሁ ብዬ አፍሮዬን ስከመክም….. እዚህ እዚያ የትም ያወረደችው የእናቴ ቀጭን ሁሉን ያስመረረ የንጭንጯ ዶፍ (አንቺ ከዛ ልጅ ምን አለሽ?) ….. እሱም ምስክሬ ነው …..
ምስክሬ ነው፥
ምስክሬ ነው፡ የእንጦጦ ወጣ ገባ ተሰነካክዬ የወደቅሁበት፥ እየሳቅሁ የተነሳሁበት፥ ብሳና ዛፍ ጥላ ስር አቅፎ የጣለኝ …. በእቅፉ መግቢያ መውጫ ያጣሁበት …. ምስክሬ ነው ወጣ ገባው …. ብሳናውም
ምስክሬ ነው፥
እንጨት በአጋሰስ የጫነ ገበሬ ፊቱን ወደ ማርያም አዙሮ ለእኛ የፅለየበት …..ወይ የረገመበት ….. ወፍራም ድምፁ እንደ ነፋስ በየቅጠሉ ሳንባ የገባው ….. ቃሉ ምስክሬ ነው ….
ምስክሬ ነው፥
የረጠበ ሳር ላይ ተቀምጠን ….. ደሞ ደረቱ ላይ ሆኜ ልቡ ስትመታ …. ለዘላለም ለመሰለ ጊዜ የሰማኋቸው ድም ድም ድም ….. ምስክሬ ናቸው አስር ሆኑ ሃያ …..
ምስክሬ ናቸው በልጅነታችን እሳት እንደ ኮሬብ ቅጠል የነደዱት የእንጦጦ ቁጥቋጦዎች ….
ምስክሬ ነው፥
ሲኒማ አምፒር ክብር ትሪቡን በሲጋራ ጢስ መሃል ተቃቅፈን አሚትባህና ራጅ ካፑር (አቤት የሕንድ ፊልም ስወድ የነበረው!) ፅጌረዳዎች መሃል ቆንጆ ሲያባረሩ ጭኖቼ መሃል እጁን ሰዶ ቄጤማ ሲፈትል ….. በማርያም ተወኝ እያልኩት …. ምስክሬ ነው ሳሩ …..
ምስክሬ ነው፥
የማርገዝ ፍርሃትና የሚከተለው ውርደቱ ጠዋት ማታ እንደ ፍልስፍና ሃሳብ ሲዘነትረኝ፥ ሴት ነኝና፥ በዚህ ህብረተሰብ ሂሳብ፡ (በየትኛውስ ቢሆን) ገላዬ የራሴም ቢሆን ከፍርድ መቅረቡ እያስፈራኝ፥ ቡና ማጣጫ ፖለቲካ መሆኔ እያሰጋኝ …. ከ ‘የምትረባ’ ወደ ‘የማትረባ’ ስሜ በቅፅበት ሲደራጅብኝ እያሰብኩ መብሰልሰሌ …. ይሄ ይሄ …. ፍርሃቴ ምስክሬ ነው።

መረቅ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *