Tidarfelagi.com

ስለ ፎቶ (ክፍል አንድ)

ልጅ እያለሁ ፎቶ ብርቅ ነበር ፤ ከእናቴ ጋራ የሆነ ግብዣ እሄዳለሁ፤ የቤት እመቤቲቱ ቡናው እስኪፈላ ከግድግዳው ላይ መስኮት የሚያህል ባለፍሬም ፎቶ መስቀያ አውርዳ በዳንቴል ወልወል አድርጋ ትጋብዘናለች። በፎቶው ውስጥ ሚስት ጥበብ ቀሚስ ለብሳ ፤ገብረክርስቶስ ጫማ አድርጋ ቁጢጥ ብላ ትታያለች ፤ ባል ሱፉን ግጥም አድርጎ አጠገቧ ቆሞ ይታያል ፤ በሰሌዳው ውስጥ ያለውን ብዙ ቦታ የሚቆጣጠረው የባልና ሚስቱ ፎቶ ነው ፤ ቴምብር የሚያካክሉ የልጆች ፎቶዎች ፍሬሙን ተጠግተው ጣል ጣል ይደረጋሉ።

አንዳንዴ እናቴና ጋባዧ ሳያዩኝ መስታውቱን ከፍቼ እበረብራለሁ ፤ ያልተዋጣላቸው ፎቶዎች ከጀርባ ተደብቀው አገኛለሁ፤ በጊዜው ዴሊት ማድረግ እሚባል ነገር ስላልነበረ ያለሽ አማራጭ የከሸፉ ፎቶዎችሽን ሰብስቦ መደበቅ ነው።

አስራሁለተኛ ክፍል ስደርስ የፎቶ አልበም መጣ፤ ግን በጊዜው የነበሩት አልበሞች ከአምሳ ገፆች በላይ አልነበራቸውም ፤ ከዚያ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሆነው ቦታ፤ ያገለገለ የሰርግ ጥሪ ካርድ ፤ የከሸፈ ሎተሪ እና የመፅሄት ቅዳጅ ይቀመጥበታል።

የፎቶ አልበም ሲቀርብልን የምናየው በታላቅ ተመስጦ እንደነበር ትዝ ይለኛል ፤ ያኔ የጎረቤት ፎቶ በምናይበት ጥሞና ዛሬ ፊልም የምናይ አይመስለኝም ፤ እያንዳንዱ ፎቶ ደግሞ የራሱ ታሪክ ነበረው።
በከተማችን የነበረው ብቸኛ ፎቶ ቤት እነማይ ፎቶ ቤት ይባላል ፤ የስቱዲዮዋ ባክግራውንድ ሁሌም የዘንባባ ዛፍ ነው፤ ካሜራው የቅየሳ መሳርያ ይመስላል፤ ከጎኑና ከጎኑ ሁለት ትልልቅ ባለ ባርኔጣ አምፕሎች ያጅቡታል፤ አንዱ አምፖል ብቻ የሚለቀው ጨረር ድፍን ጎጃምን ራት ሊያበላ ይችላል፤ ሲመስለኝ ከተማው መብራት ሃይል የለህዝቡ የሚያከፋፍለው ከነማይ ፎቶ ቤት የተረፈውን መብራት ሳይሆን አይቀርም ፤
በጊዜው “ ፊትዎትን በሳሙና በመታጠብ አይንዎን ከትራኮማ ይጠብቁ” የሚል መፈክር በሬድዮ ይነገር ነበር፤ የእነማይ ፎቶ ቤት አምፖል ባጨናበሰው አይን፤ ትራኮማ ተጠያቂ መሆኑ ያሳዝነኛል፤
ብዙ ጊዜ የተነሳነው ፎቶ ለመድረስ በትንሹ አምስት ቀን ይፈጃል፤ ጉጉታችን አይጣል ነበር። በተለይ ሴቶች የቀጠሮ ቀናቸው እስኪደርስ ድረስ እየተቁነጠነጡ ፎቱዋቸውን ቢያንስ ሁለቴ በህልማቸው ያዩታል፤
ሲኒማ ወደ ከተማው ከመግባቱ በፊት ቅዳሜ ከሰአትን የምናሳልፈው እነማይ ፎቶ ቤት በር ላይ የተለጠፉትን የሳምንቱን ፎቶዎች በማየት ነበር ፤ አልፎሂያጁ የከተማዋ ቆንጆ ሴት የተነሳችውን ፎቶ ከብቦ እያየ “ እዩዋትማ!! እመብርሃንንኮ ነው እምትመስል ” እያለ ያደንቃል ”፤ አንዳንዱ ጎረምሳ በማየትና በማድነቅ ብቻ አይወሰንም፤ ፤ ለፎቶ አንሽው ጉርሻ ሰጥቶ የቆንጆይቱን ፎቶ አጥቦ እንዲሸጥላት ያግባባዋል፤ ከዚያ ፎቶዋን በኪሱ ይዞ በከተማው በመዞር ‘ገርሌኮ ‘ ናት እያለ ጉራውን ይነሰንሳል ፤ ማርክ ዙከርበርግ የሰው ፎቶን Share የማድረግ ሀሳብ የወሰደው ከነማይ ፎቶ ቤት ይሆን

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *