Tidarfelagi.com

ስጦ-ታ

 የሆነ ነገር የሚሸጥበት ቤት አለ፤ የሆነ ነገር ገዝቼ ከከፈልኩ በሁዋላ ፤
“እዚህ ቀረህ እንዴ? “ አለቺኝ፤
“ አይ! ልደቴን ለማክበር ወጣ ብየ ነው እንጂ ኢትዮጵያ ነው እምኖረው”
ያብማይቱ! ይህን ያህል የመጎረር ብቃት አለኝ!?
“ ስንት አመት ሆነህ?”
እጇን ሳብ አርጌ መዳፏ ላይ ጻፍኩላት።
“ብዙ አይደለም”
አገጨን ዳርዳሩን የከበቡትን ሽበቶች እየጠቆምኳት “ አታይም እንዴ! ስጦ ቃሚ ፍየል መስየ ” አልኳት፤
ትስቃለች ብየ አስቤ ነበር ፤ አልተሳካም ፤
ሳስበው ልጂቱ ስጦ እሚባል ነገር አታወቅም ፤ የተከካ አተር በሩ ላይ ለኢግዚብሽን በማቅረብ የሚታወቀው የመጨረሻው ትውልድ አባል መሆኔ ትዝ አለኝ ፤ አገጬ ላይ ከተዘመዘሙት የሽበት ቡቃያዎች በላይ ይህ ግኝት ልቤ ውስጥ የአምስት ደቂቃ ከሁለት ሰከንድ ትካዜ ቀሰቀሰበኝ ።
አይኔ የተራቆቱ ክንዶቿ ላይ ሲያርፉ፤ ትካዜዎቼም እንደ ዘመኔ አለፉ፤ የቆዳዋ ቀለም የተጣራ ኔክታር ይመስላል !!!
ትንሸ ካወራን በሁዋላ
“ እስቲ የልጅነት ፎቶህን አሳየኝ “ አለችኝ፤
“በልጀነቴ ፎቶ ወደ ኢትዮጵያ አልገባም ፤ ከፈለግሽ የተሳልኩትን ላሳይሸ ”
በጉጉት ሲጠበቅ የቆየው ሳቅ ተሳቀልኝ ! ወንድ ልጅ ከሳቁለት ውሻ ከሮጡለት፤ ጀብ ካነጠፉለት ፤ የሜዳ አህያ ከተዝጎረጎሩለት አይመለስም ፡:
“ እዚህ አንድ ካንተሪ ክለብ አለ፤ ማታ ናይን ላይ ይከፈታል ፤ ብዙ አላቆይሽም ፤ አንድ ሁለት ብለን ወደ ቤቴ እሸኝሻለሁ “
መዳፏን በፊቷ ልክ ከፍ አድርጋ ቀለበቷን አሳየችኝ።
“የት (አባቱ ) ነው ሚኖረው ? “
“አገር ቤት ”
“ እሺ ሲኒማ ቤት እንግባ ፤ ከዛ ወደ ቤትሽ እሸኝሻለሁ”
“አበሻ እሚበዛበት ሰፈር ነው ፤ ሰው ካየን ሌላ ነገር ይመስላል ! ”
“ሲኒማ ቤት?”
“ አዎ! አታቅም እንዴ ! አበሻ ሲኒማ የሚገባው ፊልም ሳይሆን የፊልም ተመልካቾችን ለመመልከት ነው “
“ማስክ እንለብሳለን”
“በል ቻው ብሮ “
“ በይ ቻው ሲስትሮ “
በሩ ላይ ደርሼ እጀታውን ለመሳብ ስሞክር ከሁዋላየ ” How about a hug? “ ስትለኝ ሰማሁ፤
“ በኒህ ክንዶችሸ አይደለም ሀግ “ሃንግ” ብትሰሪኝ አልጠላም”🙂
የልደት ቀመስ መልክት የሰደዳችሁልኝ ባለንጀሮቼ እጀግ ከልብ አመሰግናለሁ፤

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *