ዲያስፖራ አይደለሁም፤ተመላላሽ ነኝ፤ “ ሲራራ “ የሚለው መጠርያ ይገልፀኛል::
እኔ እንደታዘብኩት ፤ዲያስፖራ ሁሉ አንድ አይነት አይደለም፤ መአት አይነት ዲያስፖራ አለ! ለዛሬ ዋና ዋናዎቹን ላስታዋውቃችሁ !
የመጀመርያው ክፍል አድፋጭ ዲያስፖራ ነው፤ አሳምሮ የተማረ፤ ዘናጭ ስራ ያለው፤ ፖለቲካን የሚያውቅ ግን በፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ ውቃቤው የማይፈቅድለት ! ወይ በእምየ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ተስፋ የቆረጠ ! የራሱን እና ያገር ቤት ዘመዶቹን ኑሮ ከማቃናት የዘለለ አላማ የለውም ፤ ሰልፍ ላይ ብትጠሪው አይመጣልሽም ! አበሻ ሬስቶራንት ብዙ አይታይም! እንጀራ ሲያምረው ተራርቆ ያዝዛል ! ደፋሮች መድረክ ላይ አንፈራጥጠው ፤ ማይክ አንቀው ሲቀደዱ ጥግ ይዞ እያየ ይስቃል፤ወይም ያሽሟጥጣል ! ለትምርት ቤት ፤ ለላይብራሪ ወይም ለመጠጥ ውሃ ማሰርያ ካልሆነ በቀር መዋጮ አይሳተፍም ! ቁጥሩ ብዙ ነው፤ግን በቀላሉ አይታይም!
ሁለተኛው መደብ የቱግ ቱግ መደብ ልንለው እንችላለን ! አልተማረም ! ወይ ተምሮም ትምርት አልዘለቀውም! ግንባሩ ላይ ነጥሮ ተመልሷል! እድል፤ ከውልደት ወደ ስደት በቀጥታ የገፈተረችው ነው ! አዲሳባን እንኳን በቅጡ አያውቅም! ፤ በቀጥታ ከይፋትና ጥሙጋ ወይም ከጭላሎ አሜሪካ ወይም አውሮፓ የገባ ሊሆን ይችላል ! ከሩቢላ እንደወረደ የሰፈሩ ሰዎች ወይም ዘመዶቹ ይቀበሉታል፤ እዛው ሰፈራቸው ውስጥ ማደርያ ይፈልጉለታል፤ ከዛ እዛው ሰፈሩ ውስጥ ሲጥር ሲግር ኖሮ አርጅቶ ይሞታል! ሰፊውንና ውስብስቡን የኢትዮጵያ ማህበረሰብ የማወቅ እድል አልነበረውም ! ስለዚህ ስለሌላው ህብረተሰብ ያለው እውቀት ካሉባልታና ከሚድያዎች ቀደዳ የተቃረመ ነው !
በኑሮ ቺስታ ሊሆን ይችላል! ቤቱ ገብቶ “ ምን ይዤ ልመለስ ወደ ናቴ ቤት “ የሚለውን በድብቅ ያንጎራጉራል! አገሩ መግባት እንደማይችል ስለሚያውቅ አገር ቤት ያለውን ሰው ሲያስብ ደሙ ይፈላል! አገር ቤት ያለው ሰው ድርሻውን የወሰደበት ይመስለዋል! ፤ከእሱ ቡድን ውጭ ያለውን ከማርስ እንደወረደ እንግዳ ፍጡር ይመለከታል ! የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ስትጠራው ሁለት ሰአት ቀድሞ ይደርሳል፤ ! ባንዲራ በየአይነቱ- በጨርቅ መልክ፤ በፈሳሽ መልክ ሳይቀር ሊኖረው ይችላል! ኑሮው እሮሮ አንደበቱ ተናዳፊ ነው! ዲያስፖራ ከሚባል” ዳሞትራ “ ቢባል በደንብ ይገልፀዋል!
ብዙ ጊዜ ሚድያዎችን የሚያጣብበው በዚህ ምድብ ውስጥ ያለው ነው !
እንግዲህ ሁኔታውን አይተህ፤ ፍረድበት ፤ወረድበት፤ ወይም እዘንለት!
ምራቂ፤
ያገር ቤት ነዋሪ በዲያስፖራ ሲናደድ “ እዛ በርገርህን እየገመጥህ እኛን ታፋጀናለህ ይላል! የማፋጀቱን ምንጭ ከላይ ጠቅሻለሁ:: አሁን የበርገሩን ነገር ልናገር!
ብዙ ተመላልሻለሁ ! በርገር የሚበላ ዲያስፖራ አንድ ቀን አይቸ አላውቅም፤ እንዲያውም ከዲሲ ከቶሮንቶና ከአምስተርዳም በላይ በርገር የምትቀለብ ከተማ ብትኖር አዲሳባ ናት
ኮረና ጭር ሳያደርጋቸው በፊት፤ ውሃ ልማት ፤ ቦሌ መድሀኒያለም እና ገርጂ ውስጥ የተከፈቱ ቀያይ በርገር ቤቶች በደንበኛ ተጨናንቀው ጠጠር መጣያ እንኳን አልነበራቸውም ! ዲያስፖራው ግን እንጀራን በያይነቱ አማርጦ የሚበላበት ገበያ ዘርግቷል ! አበሻ እንደ ልብ በማይገኝበት ከተማ የተቀረቀርን ሰዎች እንኳን ቢያንስ በወር አንዴ አገር አቆራርጠን ሄደን እንቀምሳለን!
ሚኒስቶታ ውስጥ አቶ ገረመውንና ኦቦ ጋሩማ በፖለቲካ ምክንያት ሊደባደቡ ይችላሉ! ዲላ ሬስቶራንት ውስጥ ስታገኛቸው ግን አንድ ናቸው ! ሁለቱም የጤፍ ምርኮኞች ናቸው ! ሁሉን አሰባሳቢ ባንዲራ ካለ እንጀራ መሆን አለበት!