ውድ አንባብያን! <ያልተቀበልናቸው>የተሰኘው አዲሱ መጽሐፌን በየመጻሕፍት መደብሩና በየአዙዋሪዎቹ እጅ ታገኙታላችሁ።መጽሐፉ በእጃችሁ እስኪገባ፣አሁንም አንድ ቁንጽል ጻሪክ ከመሐፉ ልጋብዛችሁ።
በውበት ሳሎኑ ውስጥ – 3
——-
የተቀመጥኩት መግቢያው በር አጠገብ ነበር። የሆነ ሰው፣ እጀርባዬ እንደቆመ ትከሻዬ ነግሮኝ ቀና አልኩ። ቀና ስል፣ ከዚህ ቀደም ዐይቻቸው የማላውቃቸው አንድ አረጋዊ፣ ጥቁር እንደለበሱ፣ የረዘመ ፂማቸውን እያፍተለተሉ ዐየኋቸው።
ሳሚ አላያቸውም ነበር፣ ቀና ሲል፣ አንድ የሆነ ሰው መግቢያውን ጋርደውታል። የተለየ ትኩረት አላሳያቸውም ነበር። ከቆሙበት ቦታ አንዳችም የሆነ እንቅስቃሴ አለማሳየታቸው ግን ትኩረቱን ሳበውና ዐይኑን በድጋሚ እሳቸው ላይ ጣለ። እንደመጠራጠር ብሎ፣ ዐይኑ ላይ ፀጉር የበነነበት ይመስል፣ በአይበሉባው እየጠራረገ አተኮረባቸው። የመጀመሪያ አተያዩ የት ነበር የማውቃቸው ዓይነት ነበር። አሁን ግን ተለወጠ። ተጠራጥሮ ተጠጋቸው። የተጠራጠረውን ነገር እርግጠኛ ሆነ። ሰውየውን ለይቷቸዋል። ማን መሆናቸውን መለየቱ ግን ደስታን አላመጣለትም።
ድገተኛ ድንጋጤ፣ ዐይኑ ላይ፣ ፊቱ ላይ፣ እጁ ላይ፣ እንዲሁም በመላ አካላቱ ላይ ሁሉ ተዘርቶ በፍጥነት ሲበቅል ዐየሁ።
“ምነው ጋሼ?” አላቸው፣ መቀሱን ዕቃ መደርደርያው ላይ፣ ቀኝ እጁን አገጩ ላይ አሳርፎ። ‹ምነው ጋሼ?› አባባሉና አደነጋገጡ፣ እኛንም ጭምር አስደንግጦናል። ክው ብሎ ቀርቷል። ፀጉር እየተሠራለት የነበረው ደንበኛም፣ የሙያተኛውን ፊት፣ ፊት ለፊቱ ባለው መስታወት መከታተል ብቻውን አልበቃ ብሎት፣ ፊቱን ወደ ሁለቱ አዙሮ- ልክ እንደ እኛ- እነሱን ይከታተል ገባ።
“ምነው ጋሼ?” በጥያቄው ውስጥ መስማት የማይፈልገው ምላሽ እንዳለ ገብቶኛል። ገብቶናል። ሰውየው ሀዘን አጥልቶባቸዋል። ተሰብረዋል። አንዳች የተነጠቁት ነገር እንዳለ ያስታውቅባቸዋል።
“ምነው፣ምን ደረሰብዎ?” እንዲቀመጡ ወንበር አመቻቸላቸው። አጠገባቸውም ሆነ። የሚያደርገው ነገር የቸገረው መሰለ። አዘነ፤ ተከዘ።
እሳቸውም፣ አንገታቸውን ዘለስ አድርገው፣ “ተወኝ ልጄ። ተወኝ። የእኔ ነገር አያልቅም።” አሉ።
“ምን አጋጠመዎ?!”
“ልጄ ሙት ዓመቴን እያከበርኩ ነው። መቼም እግዜር አንዳንዱን አንድ ጊዜ ብቻ አይገድለውም። እየሞተ እንዲነሳ፣ እየተነሳ እንዲሞት ያደርገዋል። እኔም እንዲያ ነው የሆንኩት። እኔ ብቻ ሳልሆን መሰሎቼም እንዲያ ነው የሆኑት ልጄ።…”
ግራ ገባን። የሆነ የተምታታ ነገር እያወሩ እንደሆነ ተረዳሁ።
“የቅርብ ቤተሰብ…” አለ፣ ፀጉር ተስተካካዩ።
“እንዲህ መጠየቅህ፣ፂሜን ማሳደጌን፣ በአካል መጎዳቴንና ጥቁር መልበሴን ዐይተህ ነው አይደል?!… አየህ ልጄ! እኔ አንድ አይደለሁም፤ ብዙ ነኝ፤ ብዙ ሟቾች፣ ብዙ እስረኞች በውስጤ አሉ። እኔ የሚሰማኝ ስሜት ሁሉ የእነሱ ነው። የእነሱን ሀዘን ለማስታመም የሚችል ጫንቃ እግዜሩ የፈጠረልኝ ያለምክንያት አይደለም…”
ፀጉር አስተካካዩ፣ እያዩት እንዳልሆነ ርግጠኛ ሲሆን፣ በምልክት አንድ ነገር ነገረን። “እየለቀቁ ነው፤ አዕምሯቸው ጤናማ አይደለም!” እያለን እንደሆነ ተረጎምነው።
ተነሳና፣ ሼቨሩን በቄንጥ ይዞ፣ የተለመደ ሥራውን ቀጠለ።
“ጎበዝ ስንት ጊዜ እንሙት? ስንት ጊዜ፣ በስንቶቹ እንገደል?! እናንተ፣ የአንደኛ ደረጃ ትምሕርታችሁን በምትከታተሉበት ጊዜ፣ እኔ የት የነበርኩ ይመስላችኋል?! ምን የተደረግሁ ይመስላችኋል? 1976 ዓ.ም. ማለት የሰቀቀን ዘመን ነበር። የኡኡታ፣ የድንጋጤ፣ የስጋት ዓመታት። ደርግ የአብዮቱ ጠላቶች ናችሁ ብሎ፣ ከየተሰማራንበት ስፍራ እየለቀመ ለእስር ሲዳርገን፣ ማን ከጎናችን ቆመ?! በራሱ በደርግ ጽሕፈት ቤት፣ በራሱ ሕዝባዊ ድርጅት ውስጥ፣ አብዮቱን እያገለገልን ነው ብለን በምናምንበት ዘመን፣ ሕወሓትና ሻዕቢያ የገንጣይነትና የአስገንጣይነት ሚና ለመጫወት የሚያደርጉትን ጥረት በምናወግዝበት ዘመን ተያዝናታ- በደርግ መዳፍ። ተለቀምን። ደርሰንባችኋል ተባልን። ተወገዝነው፤ ተቀፈደድነው፤ ተደበደብነው፤ ምን ያልሆንነው አለ ልጆቼ?! ከላይ እሳት፣ ከታች እሳት። በስንቱ ቢላዋ እንታረድ? በስንቱ የፖለቲካ መስቀል እንቸንከር?! ማን ይቀበለን? ተቀባይ ያጣን ደብዳቤዎች!!”
መጽሔቶቹን በሥርዓት ደርድሬ ወደነበሩበት መለስኳቸው። ሽማግሌውን ማዳመጥ ፈለግሁ። በሙሉ ልቤ!
“ምን ብዬ ልንገራችሁ?! ይሄ ትውልድ አያውቀንም። አላወቀልንም። ደርግና ሕወሓት በእኛ ላይ የተጫወቱትና እየተጫወቱ ያለውን የፖለቲካ ቁማር አያውቅልንም። ለነገሩ እኛስ ብንሆን ጠልቀንና ጠንቅቀን መች አወቅነው?!… በኛ ላይ የሚደረገውን ሽኩቻ፣ በእኛ ላይ የሚፈፀመውን ጨዋታ መቼ አወቅነው?! ድራማው መቼ አለቀ?! አዎ! እንዲህም እንዲያም ሆኗል። ደርግ በቤርሙዳ፣ በማዕከላዊና ሌላ ሌላ ቦታ በታጎርን እስረኞች ላይ፣ የተለየ ስም ነበር ያተመብን። ‹አብዮታዊ መንግስት ሕብረተሰቡን እንዲያገለግል በሰጠው ኃላፊነትና ሥልጣን በመጠቀም ጥቂት መሰል ከሃዲዎችን በማስተባበር አብዮቱን ከማገልገል ይልቅ በጠባብነት ነቀርሳ ተይዞ በእርሱ የሚመሩ ጥቂት ግለሰቦች… የውስጥ የሕወሓት አርበኛ በመሆን አገሩን፣ ወገኑን ወግቷል፤ አብዮቱን በመካድ ያሳደገችውን የእናት አገሩን የኢትዮጵያን ጡት ነክሷል ስንባል፣ ዓለም ደርሶልናል?! አቤቱታችን ተሰምቷል?
“አያችሁ ልጆቼ፣ የሚታተምባችሁን ስም እስክታስፍቁ ድረስ ብዙ መከራ ታያላችሁ። እኔ በታሰርኩበት ዘመን፣ ‹የለም፤ እናንተ የምትሉኝን ዓይነት ሰው አይደለሁም፤ በግ አይደለሁም እንዳሻችሁ ወዳሻችሁ የምትወስዱኝ!› በማለታቸው፣ እነ ኅሩይ አስገዶም ከደርጎቹ ጋር አልተታኮሱም?! ኅሩይ ራሱ በተኩሱ ልውውጥ አንድ ሁለቱን አቁስሎ፣ በመጨረሻም አልተገደለም?! ተገድሏል። እናንተ ይህን አታውቁም። ብታውቁም አትደነቁም። አንድ ሰው መልሶ መላልሶ ሲገደል፣ ለምን ብላችሁ አትጠይቁም።
“ደርግ አለቦታችን አውሎ፣ አለሚዛናችን ሰፍሮ፣ በወጣትነት ዕድሜያችን ላይ ቀልዶበታል። ሸንቶበታል። በጅምላ ነበር የታሰርነው። ከመቀሌ፣ ከአዲስ አበባ፣ ከድሬዳዋ… ከየአቅጣጫው ነበር የተሰበሰብነው።‹አብዮቱን ቦርቡራችኋል፤ ከሕወሓት ጋር አብራችኋል!› ተብለን በየወህኒ ቤቱ ማቀቅን። ማቀቀን አልኩ?! አለምክንያት መታሰር፣ መገረፍ፣ መማቀቅ ብቻ ነው የሚባለው?! ‹ሕወሓት በተባለ የወንበዴ ድርጅት ውስጥ የነበረህ ሚና ምንድነው? ካንተ ጋር እነማን ነበሩ? እመን!› እየተባላችሁ ስትገደዱ፣ ‹ከምኑም ከምናምኑም የለንበትም!› በማለታችሁ፣ በአካልም በመንፈስም የምትጎዱበት ሁኔታ ሲመቻች… ፀረ ሕዝቦች ተብላችሁ፣ ጠመንጃ የያዘ ሁሉ ሲዘባበትባችሁ … ኧረ ምኑ ቅጡ!”
ዝም ብዬ ማዳመጤን ቀጠልኩ። ፀጉር ተስተካካዩ እሳቸውን መስማት አቁሟል። ሳይሰለቸው አልቀረም።
—–
“ዛሬ እንዴት እንደ አዲስ ሊያስታውሱት ቻሉ?!” አለ፣ ሳሚ።
“ሳላስታውሰው ቀርቼ የማውቅ ይመስልሃል?”
“ዛሬ ነገሩን ሁሉ እንዴት ትኩስ አደረጉት ማለቴ ነው!” አለ፣ በገረሜታ።
“እንደምን ትኩስ አላደርገው! ሲያመኝስ? እንደገና፣ አሁንም እየተገደልኩ እንደሆነ ሲሰማኝስ?!… እኔኮ ተስፋ የቆረጥኩት፣ እዚያው ቤርሙዳ፣ የአዲስ አበባ ኢሠፓአኮ የርዕዮተ-ዓለም ጉዳይ ኃላፊና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ከእኛው ጋር እንዲደመር ሲፈረድበት ነው! ጓድ ታደሰ እኮ ለደርግ ታማኝ ሎሌ ነበር። አብዮት ድመት ሆኖ ታደሰ ልጁን ሊበላው ግድ ሆነ። ተመልከቱ – ታደሰ ገብረእግዚአብሔር፣ ኮለኔል ካሳዬ ወልደአብ፣ ኮለኔል ገብረዮሐንስ አስፋው፣ ኧረ ስንቱን ጠቅሼ ልጨርሰው? ለሦስት ዓመታት ከታሰሩ በኋላ ነው የተገደሉት። ማን ተረፈ? ሺህዎች ታጨዱ። ሞት ረከሰ። እነኮሎኔል ተስፋዬ ወልደሥላሴ፣ በጸረ አብዮተኛነትና ሕወሓት አባልነት የፈረጁትን ሰው ሲገድሉና ሲያስገድሉ ቅጠል የመበጠስ ያህል ነበር የሚሰማቸው! ደርግ እንደወደቀ፣ ከሕመሜ እምድን እየመሰለኝ፣ የደርግ ባለስልጣናት ሲከሰሱ ሲወቀሱ መስማት ሥራዬ አድርጌው ነበር። …….
እነዚህን ሰማእታት በየቀኑ ይዣቸው እዞራለሁ። ተፈርዶልኝ ይሁን ተፈርዶብኝ አላውቅም። ትተውት የሄዱት ተስፋ፣ ትተውት የሄዱት አቋም፣ በትነውት የሄዱት ቤተሰብ ጉዳይ ያሳስበኛል።
“አንዳንዶቻችን ደርግ እስኪወድቅ ከቤርሙዳ አልወጣንም። የታማንበት መንግስት፣በደርግ ዘመን ፖለቲካዊ ስልጣን ስለነበረን በሀዘኔታ ያየን ይመስላችኋል? አላደረገውም። ከ1985 ዓ.ም. ጀምሮ ብዙዎቻችን፣ ለሰባት ለስምንት ዓመታት ያህል ዳግም ታሰርን። የተሳከረ ቴአትር መሰላችሁ አይደል? አዎን! የደርግ ሥርዓት አራማጆች ተብለን፣ በደርግ ዘመን ስለነበረን ስልጣን ተጠቅሶልን፣ እናንተ በመራችኋት አገር ነው ኑሯችን መራራ የሆነው ተብለን… ታሰርን። ተፈረደብንም! ርግጥ ነው፣ እኔም እንደ እነ ታደሰ ደርግን ጠቅሜዋለሁ። ለእንጀራ ብዬ አልነበረም። ፍርሃት ይዞኝ አልነበረም። ሳላምንበትም አይደለም። አብዮቱ ለአገር እንደመጣ እምነቱ ነበረኝ።የዘውዱ ስርአት በአገሪቱ ላይ ተኝቶባት ነበር።ሲጀመር የአጼ ኃይለሥላሴ መንግስት አገሪቷን እያንደረደረ አሳድጓት ነበር።ትምሕርት ቤቱ፣ማተሚያ ቤቱ፣የኅትመት ውጤቶቹ ምን ልበላችሁ? አገሪቱ ታደሰች።በኋላ ግን መፍጠኗ ቀርቶ መዳህ መንፏቀቅ ጀመረች።እንደ አንድ ተራማጅ ስርአቱ እንዲቀጥን መፍቀድ ልክ አልነበረም።ለአመጽ የተባርነውም ለዚህ ነው።የደርግ ስርአት ሲመሰረት ከዘር መድልዎ የፀዳ ለመሆኑ ጥርጥር አልነበረኝም። አለመታደል ሆነና ስማችን ከእንክርዳዶች ተርታ ተሰለፈ። ተለቅመን ተወረወርን።ወያኔ ምኒልክ ቤተመንግስት ስትገባ ባትሾመን ባትሸልመን እንኳን፣ ሰብዓዊነት ተሰምቷት ምሕረት ታደርግልናለች የሚል ግምት ነበረን፤ ግን አላደረገችውም! አዎን! ለዚህም ነው ስንት ጊዜ እንገደል ማለቴ!
“ለመሆኑ የገብሩ አስራትን መጽሐፍ አንብባችሁታል?!” አሉን፤ መልስ አልጠበቁም። የጠበቃ ከመሰለ መለስተኛ ሻንጣቸው አንድ መጽሐፍ ይዘው ወጡ። አውቀዋለሁ – መጽሐፉን። ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ ይላል።
“አያችሁት? አነሰች እንጂ የእኛም ታሪክ በዚህች መጽሐፍ ጥቂት ገጾች ተሰፍሮ ተሰጥቶታል። ለደርግም ሆነ ለወያኔ እንደ ከረንቦላ መጫወቻ ድንጋይ እንደነበርን የነገረኝ መጽሐፍ ይሄ ነው። ድንጋዮቻቸው ነበርን። ሁለቱም ወዳሻቸው ጥግ የሚያጎኑን። የሚቀባበሉን።ደርግ ሳያውቅ በስህተት፣ሕውሓት አውቆ በድፍረት፣ በነፍሶቻችን የሚዘባበቱብን ድኩማን ነበርን።…ኧይ! የማይገባ ነገር ተናገርኩ መሰለኝ። እንዴት እንዲገባችሁ ማድረግ እንደምችልም አላውቅም።… እስኪ ይህችን ገጽ አንብቧት ። ቢያንስ አንድ ሁለቷን አንቀጽ።”
መጽሐፉን ተቀበልኳቸው። ገጹን ገልጠው አሳዩኝ። መጽሐፉ ውስጥ በተለየ ሁኔታ በዚህ ገጽ ላይ በሚገኙ አንቀፆች ላይ አስምረውባቸዋል።
<የከተማው የሕወሓት እንቅስቃሴ ከተነሳ ዘንድ አንድ የሚታወስ አስገራሚ ታሪክ አለ። በ1970 ዓ.ም ደርግ ባካሄደው የማጋለጥና የመመንጠር ዘመቻ በኋላ ቁጥራቸው የማይናቅ የትግራይ ተወላጆች ደርግን ማገልገል ጀምረው ነበር። ‹…› ሕዝቡን ያውኩ ስለነበር፣ ሕወሓት እነዚህን ሊያጠፋቸው አንድ ዘዴ ቀየሰ። ሐሳቡን በዋነኛነት ያፈለቀው ዕውቁ የከተማ የሕዝብ ግንኙነት ሠራተኛ ተኽሉ ሃዋዝ ሲሆን፣ የቀየሰውንም ዘዴ ለማስፈፀም ሦስት ታጋዮች እንዲመደቡለት ጠየቀ። ይህ ከተፈቀደለት በኋላ፣ ሦስቱ ታጋዮች ከተማ ገብተው ሕዝቡን የሚያውኩትን ግለሰቦች ደርግ ራሱ እንዲያጠፋቸው የተቀየሰውን የረቀቀ እቅድ እንዲያስፈጽሙ ተልዕኮ ተሰጣቸው። ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ ከተኽሉ ሃዋዝ በወቅቱ የፖለቲካ ሐላፊ ለነበረው ዓባይ ፀሐዬ የተላከ አስመስሎ አንድ ሰፊ ደብዳቤ አዘጋጀ። ‹ጥብቅ ምስጢር› የሚል ተጽፎበት በማጣበቅያ፣ በሙጫና በስቴፕሎች ታሽጎ ነበር። በዚህ ደብዳቤ ውስጥ በኮድ ብቻ የተጻፈ የብዙ ሰዎች የስም ዝርዝር ሰፍሮ ነበር። ስማቸው ብቻ ሳይሆን ማን ከማን ጋራ በሕዋስ እንደተደራጀና የአመራር ኮሚቴ አባላቱ እነማን እንደሆኑ በማመልከት የውሸቱን የከተማ መዋቅር ቁልጭ አድርጎ ያሳይ ነበር። ስሞቹ ሆን ተብሎ በኮድ ይጻፉ እንጂ ኮድ የደርግ ባለሙያዎች በቀላሉ ሊፈቱት እንደሚችሉ ተደርጎ የተዘጋጀ ነበር። በዚህ ደብዳቤ ውስጥ የአብዛኛዎቹ ሕወሓትን ሲያውኩ የነበሩት የደርግ ጋሻ ጃግሬዎች ስም ሰፍሮ እጅግ ታማኝ የሕወሓት አባላት እንደሆኑ ተገልጾ ነበር።>
እያለ ይቀጥላል – መጽሐፉ።
ማንበቤን ያቋረጥኩት አረጋዊው መጽሐፉን ነጥቀው የተቀረውን ሃሳብ ራሳቸው አንብበውልኝ ነው።
“ሦስቱ ታጋዮች ይህን ደብዳቤ ይዘው አክሱም ለሚገኘው አስተዳደር እጃቸውን ሰጡ። ወዶ ገብ ተባሉ። በያዙት ደብዳቤ ላይ የተጠቀሰው የላኪና የተቀባይ ስም ደግሞ ደርግ የሚያውቃቸው ናቸውና የወዶ ገቦቹ ጉዳይ ክብደት አገኘ። ወያኔዎቹንና ደብዳቤያቸውን ተቀባበሉዋቸው። ደርግ፣ ግዳይ እንደጣለ አዳኝ፣ በዚህ ዜና እጅጉን ተደሰተ። ኮዱ ተፈታ። ሲፈታ የራሱ ሰዎች ስም ዝርዝር አለበት። እኔ ራሴ አልቀረሁም። በኤርትራ መገንጠል አላምንም የምለው እኔ፣ እንደ ቀንደኛ የድርጊታቸው ተባባሪ ተብዬ ስሜ ተጠቅሷል። የደህንነት ሰዎች፣ እነ ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደሥላሴ ይህን ዐይተው እንዴት እንቅልፍ ይውሰዳቸው? እንደ አረም መነጠሩን፤ እንደቅቤም አነጠሩን፤ ሸለሉብን! ፎከሩብን፤ይኸው ተጽፏል!”
በጣታቸው ወደ አመለከቱኝ ቦታ ዐይኔን ላክሁት።
<ሕወሓት በዚሁ ዘዴ በክልሉ ቀንደኛ ተዋንያን የነበሩትን የደርግ ካድሬዎችና ታጣቂዎችን በቁጥጥር ስር እንዲውሉ አደረገ። በዚህ ሰበብ የኢሠፓአኮ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የፖለቲካ ትምሕርት ቤት ከፍተኛ ባለስልጣን የነበረው ታደሰ ገብረእግዚአብሔር ሳይቀር በቁጥጥር ሥር ውሎ መጨረሻ ላይ ከወህኒ ቤት ተወስዶ በደርግ አፋኞች ተገድሏል። የክፍለ ሀገሩ ቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር የነበረው ኅሩይ አስገዶምም የውስጥ አርበኛ ነው ተብሎ በቁጥጥር ስር እንዲውል ሲጠየቅ በተደረገው የተኩስ ልውውጥ ሕይወቱ አልፏል። ሕወሓት ውስጥ በደህንነት ሥራ ተመድቦ ሲሰራ የነበረውና እጁን ለደርግ ሰጥቶ በጸጥታ ሠራተኛነት ተመድቦ ሲያገለግል የነበረው ዓለማየሁ በቀለም እንዲሁ በሠርጎ ገብነት ተጠርጥሮ እጁን እንዲሰጥ ሲጠየቅ ሊያስሩት ከተላኩት ጋራ በተደረገው የተኩስ ልውውጥ ሕይወቱን አጥቷል…>
አቋረጡኝ።“ይኸው ነው! መናደዴ ለዚህ ነው! እንዲህ መሆኔ ለዚህ ነው! ወዳጆቼ እነታደሰ፣ እነኅሩይ ለምን እንደተገደሉ የገባኝ አሁን ነው! ደርግ ለምን እንድታሰርና እንድንገላታ እንደፈረደብኝ የገባኝ አሁን ነው! አያሳዝንም?! ገብቷችኋል ግን?…” ተጠራጥረው ጠየቁን።
እኔና ፀጉር አስተካካዩ ሳሚ በአዎንታ ጭንቅላታችንን ነቀነቅን። ተስተካካዩ ግን፣ በመስታወት ውስጥ፣ጸጉሩን እየገመገመ ነበር። ጨርሷል። ጆሮው ውስጥ የተወተፈው ጥጥ ወጥቶለታል። ለብ ባለ ውኃ በተነከረ ፎጣ፣ ጉንጩና አናቱ ተዳብሶለታል። አምሮበታል። እስኪወጣ ቸኩሏል እንጂ፣ የአረጋዊው ጉዳይ ቦታም አልሰጠው። እሳቸውም ገብቷቸዋል!
“የገባችሁ አይመስለኝም። ዓመታቴን ያለአግባብ ተነጠቅሁኮ ነው የምላችሁ! በምን ምክንያት እንደተገደሉ በቅጡ ያላወቁ ሰዎች ጓደኛ ነበርኩ እኮ ነው የምላችሁ! እኔም፣ወያኔ ምን ያህል እንደተጫወተችብን፣ ደርግም እንዴት እንደተጃጃለብን የገባኝ ይሄ መጽሐፍ ሲወጣ ነው።የከረንቦላ ድንጋዮች ነበርን! ድንጋዩ ምን አቅም አለው-ወደተወረወረበት መወርወር፣መወሸቅ፣መሽቀንጥር እንጂ!”
በሃሳብ ሰመጡ።
አረጋዊው ድምጻቸው እየሻከረ ወደ በሩ አመሩ።
“ደርግ ሰባት ዓመት፣ ኢሕአዴግ ሦስት ዓመት አሰሩኝ። አሰሩን።” አሉና ዝም አሉ። ልናገረው ወይስ ይቅርብኝ የሚል ሃሳብ ተከትሎ የመጣባቸው ይመስላል።
አመነቱና ቀጠሉ።
“ደርግ እኔን ሊይዝ አንድ ቀን ሲቀረው፣ በእነታደሰ ገብረእግዚአብሔር መታሰር በጣም ነድዶኝ ጂን ስጠጣ አመሸሁ። ወደ ቤቴ እንዳልገባ የገዛ ቤቴ ቀፈፈኝ። ሰዓቱ ሄዶ ነበር። ሰዓት እላፊም ታውጆ ነበር።ልቤ እንደ ጨለማው ጠቁሮ ነበር።አልጋ ፍለጋ ዞር ዞር አልኩ።ብቻዬን መሆን ስላልፈለግሁ፣የበታችነት ስሜት እንዲሰማኝም ስለፈለግሁ፣ከንቱነቴን ለራሴ ላሳየው፣ያልለመደብኝን፣ ከአንዲት መንገድ ዳር ቆማ ወንድ ከምትጠባበቅና ገላዋን ሽጣ ከምታድር ሴት ጋር አደርኩ።አየኋት።ልጅ እግር ነበረች።ይዣት ወደሆቴል ወሰድኳት።ሌሊት ራሴን ያገኘሁት፣ አንድ ደከም ባለ ክፍል ውስጥ፣ ክንዴን ተንተርሳው ነበር። የገረመኝ ግን፣ ልጅቱ መስማትና መናገር የተሳናት መሆኑን ያወቅሁት ሲነጋ ነው። ወይስ ማታውኑ አውቅ ነበር? ትዝ አይለኝም። መስማትና መናገር የተሳናት መሆኗን ባወቅሁ ጊዜ ፣ደንግጬ እንደነበር ትዝ ይለኛል። በምን ቋንቋ አውርቼ ተግባባኋት? እንዴት ወደ መኝታ ወሰድኳት? እንዴትስ መስማትና መናገር የተሳናት ሴት በዚህ ሙያ ራሷን ለማኖር ቆርጣ ተነሳች? አገሪቱን ወዴት እየወሰድናት ነው? እያልኩ ስገረም ነበር። ማዕከላዊ እያለሁ ለብዙ ጊዜ አስባት ነበር። ያ ቀን ጠዋት ከእንቅልፌ ስነቃ፣ ያወለቅሁት ቀበቶዬ ላይ፣ አንድ ጽሑፍ አገኘሁ። ጽሑፉ የእሷ እንደሆነ በምልክት ነገረችኝ።ልጆቼ እየሰማችሁኝ ነው? ጽሑፉን ሳነበው፣ ‹እኔኮ መስማትም መናገርም የማልችል ሸርሙጣ ነኝ› ይላል። እንዲህ ያለችኝ ምን ብያት ነው? እንደምገምተው፣ ሌሊቱን ሙሉ ስለ እስረኛ ወዳጆቼ፣ ወይም አብዮቱ እዚያ ደረጃ ለማድረስ ስለከፈልነው መስዋዕትነት፣ወይም የኮሚኒስት ስርአት በአለማችን ሲሰፍን፣እያንዳንዱ እንደ ሁሉም፣ሁሉም እያንዳንዱ የሚለው አመለካከት በአለማችን ሲንሰራፋ፣የእሷም ሕይወት እንደሚለወጥ እያለቀስኩ ተርኬላት ይሆናል።የደረሰብኝ በደል ዘርዝሬ አሳዝኛት፣ አስለቅሻትም ይሆናል። ታዲያ ለምንድነው- ልክ እንደ እናት- እንደዚያ ተንሰፍስፋ የተሰናበተችኝ?
ሳሚ ፀጉር አስተካክሎ ጨረሰ። ተስተካካዩ ሂሳብ ከፈለ። የጨፈገገ ፊቱ ፈካ። አመስግኖም ወጣ።
ሳሚ ተስተካካዩ የተነሳበትን ቦታ አጽድቶ፣ ለብሶት የነበረውን ዩኒፎርም አጣጥፎ፣ ፀጉር በበነነባቸው ቦታዎች ላይ ያረፉ ብናኞችን አጽድቶ ሲጨርስ፣ አረጋዊውን ወደ ወንበሩ ጋበዛቸው።
እሳቸው ግን ለመሄድ ብድግ አሉ እንጂ በወንበሩ አልተቀመጡም።
“ምነው?” አላቸው።
“ፀጉሬን ልስተካከል የመጣሁ መስሎህ ነው? አይደለም! ዐየህ በውስጤ ሀዘን፣ ቁጭት፣ መበደል አለ። ተገፍቻለሁ! ተተፍቻለሁ! ራሴን እንዲህ የጣልኩት፣ የሀዘን ማቅ ያጠለቀ የመሰልኩት፣ ፂሜን ያጎፈርኩትና ፀጉሬን አለቅጥ ያሳደግሁት ሙታመቴን በማስመልከት ነው አላልኳችሁም? አዎ! ደርግና ሕወሓት ተኩሰው ቢስቱኝም ገድለውኛል። ጠላቴ ደርግ ብቻ እንዳልሆነ ያወቅሁት ይኼ መጽሐፍ ሲወጣ ነው።…እናም፣ እናንተ እንደጠየቃችሁኝ፣‹ምነው አባባ፣ምን ሆነዋል?›እንዳላችሁኝ ሌላውም እንዲጠይቀኝ እፈልጋለሁ። ለሌላውም ለእናንተ የሰጠሁትን ዓይነት መረጃ መስጠት እፈልጋለሁ። ምን ላድርግ? ልብ የሚለን አጣሁ፤ ሕመማችን የሚገባው አጣሁ… ስንት ጊዜ እንሙት ልጆቼ?”
‹አዎን! ብዙ ነገር ሆኛለሁ፤ ብዙ ነገር ሆነናል።የሚያሳዝነኝ ሳንስማማ፣ ሳንሰማማ፣ ሳንተዋወቅ፣ ሳንናበብ፣ በጠላትነት ዓይነት እንደተያየን መሞታችን ነው!›