ወይንሸት የመጀመርያ ልጅ ነች። ዕድሜዋ አስር ሆኗል። እኩዮቿ ከክፍል ወደ ክፍል በተዘዋወሩ ቁጥር እሷ ግን ታናናሾቿን በመሸከም ነው ከዓመት ወደ ዓመት የምትሸጋገረው!
ወላጆቿ ሞግዚት የመቅጠር አቅም የላቸውም፤ ለዚህም ነው ወይንሸትን ወደ ፊደል ገበታ ያልሰደዷት።
አባቷ ‘ሰርቶ በይ!’ የሚል ድምፅ ወደሰማበት የሚሮጥ. . . ቤተሰቡን ፆም ላለማሳደር የሚተጋ አባወራ ነው።
እናቷ የምትሸጠውን እንጀራ በመጋገር የምታሳልፍ፤ ነፍሰጡር አለመሆን የሚከፋው ሆዷን እየገፋች፤ ለአራት ልጆቿ ሆድ ስትኳትን የምታድር ናት!
እና፤ ወይንሸት ቀርቶባት ታናሿ ነው ተማሪ ቤት የተላከው። በዓመቱ የታናሽዋ ታናሽ!
ዘንድሮም…‘እሹሩሩ ማሙሽ ውረድ ከጀርባዬ’ ነው ቅኝቷ።
ዛሬ ደግሞ ከጥዋት ጀምሮ ከፍቷታል።
እናቷ ምጥ ይዟት ወደ ከፍተኛ ክሊኒክ ከወሰድዋት በኋላ መረጋጋት ርቋታል። ‘ስድስተኛ ወር አልፎኛል’ ስትል እንጂ ‘ዘጠነኛ ወሬን ሞልቻለሁ!’ ስትል አልሰማቻትም ነበር፤እናቷን።
ፈርታለች እናቷ! ‘እንጃልኝ ዘንድሮ’ ባይ ሆናለች – የሐኪም ቤት ደጅ ረግጣ በተመለሰች ቁጥር። ድንገት አንድ ሐሳብ መጣላትና ፈገግ አለች…ፈገግ…
የጥዋት ፈረቃ ተማሪዎች ከትምህርት ቤት የሚመለሱበት ሰዓት ነው።
ወይንሸት “የማደርገውን አውቃለሁ!” በሚል ስሜት ውስጥ ሆና፤ የምታዝላትን ህጻን ‘እሹሩሩ’ ብላ አስተኝታ፤ “ሽንት ቤት ሄጄ ልምጣ” የሚል ምክንያት ፈጥራ…
ወደ ማርያም ቤተክርስቲያን ሄደች። ከነፈች። ተሳልማ ገባች። ከዚህ በፊት ፀልያ አታውቅም። እንዴት ነበር የሚፀለየው? እንዴት ነበር?…እንዴት እንደሚፀለይ ትዝ አልልሽ አላት።
ተንበረከከች።
ተንበርክካ ስለደረሰባት በደል ታሰላስል ያዘች። ጓደኞቿ ዛሬ ባለ ብዙ እውቀት ሆነዋል። የሚያማምሩ ስዕሎች የበዙባቸው መጻሕፍት አሏቸው። ሊገቧት ባልቻሉ ርዕሰ ጉዳዮች ዙርያ እንኪያ ስላንቲያ ይገጥማሉ። ይጽፋሉ፤ ያነብባሉ።
አራተኛ ክፍል ደርሰዋል።
አራተኛ!
እያንዳንዱ ቀን ለነሱ ንጋት ነው። አዳዲስ ተረት… አዳዲስ ሃሳብ….አዳዲስ ሰው!
ተረስታለች፤ ወይንሸት። በ‘ሀ’ ና በ‘በ’፤ በ‘ሠ’ ና በ‘ጠ’ ፊደል መሃከል ስላለው ልዩነት የማወቅ ዕድል ተነፍጓታል። ጨዋታ ጎድሏታል። ሳታድግ አሳዳጊ ሆናለች።
በህጻን ልቧ ውስጥ ፊደል አልተዘራም፤ ቁጥር አልበቀለም፤ ቀለም አልፀደቀም። እንደጓደኞቿ እያበበች አይደለም። አረም ተብላ ከእኩዮቿ ተነጥላ፤ ተነቅላ እንዳትጣል ነው ስጋቷ!
ዕንባ ዕንባ ሲላት ቆየና “ማርያም!” አለች በሹክሹክታ፤ “ዛሬ እናቴን ሐኪም ቤት ወስደዋታል፤ ልትወልድ ነው ብለው እናቶች ወስደዋታል!” አለች ወይንሸት፤ ግራ ቀኝዋን ገልመጥ አድርጋ። “ማርያም በናትሽ እናቴ እንዳትወልድ አድርጊ!.እናቴ ከወለደች ክረምቱ ሲያልቅ ትምህርት ቤት ላያስመዘግቡኝ እኮ ነው። በናትሽ! እናቴን አታስወልጂያት! ምንም ሳልማር ትልቅ ሰው ልሆን እኮ ነው፤ አላሳዝንሽም?”
ዕንባዋ…
“ሠራተኛ እስኪቀጠርልን ድረስ አታስወልጂያት። ማርያምዬ….ጓደኞቼ አራተኛ ክፍል ናቸው። እኔ ግን ዜሮ ክፍል የሚያስገባኝ አጣሁ፤ አላሳዝንሽም? በናትሽ….እ?…”
ፀሎቷን ጨርሳ፤ ቤተክርስቲያኗን ተሳልማ ወደ ቤቷ ተመለሰች። የምታዝለው ህጻንም ከእንቅልፉ አልነቃም ነበር፤ ጡጦ እንደጐረሰ አገኘችው።
ሳሎን ውስጥ ያገኘቻቸው ሰዎች ግን ቀደም ሲል የነበሩ ጎረቤትና ዘመዶች ብቻ አይደሉም። እናቷም ከሐኪም ቤት መጥተዋል። ፀጥ፤ ረጭ ብሏል – ቤቱ! ዕንባ ዘንቦበት፤ ልቅሶ ተሰምቶበት የቆዘመ ጎጆ!
ቀዝቅዟል። ፊታቸው ደምኗል። በተለይ እናቷ! እናም ደነገጠች። ወዲያው አንድ የጎረቤት እናት “ነይ! ነይ ሚጡ! አይዞሽ እሺ? ዋናው እናትሽ በሰላም መትረፏ ነው!” አሏት በሚያፅናና ዜማ፤ ድምፃቸውን ቀንሰው።
አልገባትም። ከዚህ በፊት ‘ወንድም ቢወለድልሽ ይሻላል ወይስ እህት ቢወለድልሽ?’ እያሉ ያስጨንቋት የነበሩ አሮጊት ናቸው።
አሁን ግን…
“እናትሽ መትረፏ ነው ዋናው ነገር! ጊዜው ሳይደርስ ነበር ምጡ ያጣደፋት!” አሉ ዕንባ ባጀበው ሻከራ ድምፅ “ለዚያ ነው ህፃኑ ያረፈው!”
የወይንሸት ፊት ላይ ሀዘን አልነበረም፤ ልቅሶ አልነበረም፤ ድንጋጤም፤ መታወክም አልነበረውም….
ፈገግ ብላለች።
የትምህርቷ ነገር….
“ምን እያሰብሽ ነው ልጄ?” ብለው ጠየቋት አሮጊቷ።
“ቤተክርስቲያን ነበርኩ”
“ምን ልትሠሪ ሄደሽ?” ቀጠሉ ጥያቄያቸውን።
“ልፀልይ!”
“የምን ፀሎት?”
“እናቴን እንዳታሳምሚብኝ ብዬ ለማርያም ነግሬያት ቶሎ መጣሁ” አለች ወይንሸት።
“ሰምታሻለቻ!” አሉ አሮጊቷ ደስ ብሏቸው፤ “ማርያም! የነገሯትን የማትረሳ፤ የለመኗትን የማትነሳ!”
ወይንሸት፤ ጎረቤት ወዳሉት እኩዮቿ ሄዳ በጥያቄ ታጣድፋቸው ጀመር።
– የአንደኛ ክፍል ምዝገባ መቼ ነው?
– ተፅፎበት ያላለቀ ደብተር ሲኖራችሁ አትሰጡኝም?
– እስኪቢርቶ ካቆራረጠባችሁ አትጣሉት፤ እኔ አስፅፌ እጠቀምበታለሁ። በናታችሁ! እሺ?
የማትለው ነገር አልነበራትም። እጅግ ብዙ ነገር!
“አንቺ የምትማሪ ከሆነ እናትሽ ብትወልድስ? ብቻዋን አትሆንም?ልጅ ማን ይይዝላታል?” ይሏታል ጓደኞቿ።
“ዘንድሮ አትወልድም” ይሆናል መልሷ።
“ለምን ወይንሸት?” ሲሏት ደግሞ –
“ለማርያም እናቴን አታስወልጂያት ብዬ ነግሬያት የለ!” – ትላቸውና ስንጥር ቢጤ ፈላልጋ ትቀመጣለች። ቀሚሷን በትንሹ ገለብ አድርጋ እግሮቿ ላይ ትፅፋለች።
ስም ያልወጣላቸው ‘ፊደሎች’…የተንሻፈፉ መስመሮች… የተወለጋገዱ ክቦች!
ፊቷን ማየት ነው በዚህ ጊዜ።
በብርሃን የተሞላ ፊቷን፤ ፊደልና ቁጥር መለየት የናፈቀው ዓይኗን…
/እንዳለጌታ ከበደ፣ከ “የመኝታ ቤት ምስጢሮች” የአጫጭር ትረካዎች መድበል፤ እንደ ባለታሪኳ ያሉ ብዙ ሕጻናት በየቦታው አሉና ችላ ልንላቸው እንደማይገባ ለማሳሰብ የተለጠፈ።/