የዩንቨርስቴ ተማሪዎች ወገን ለይተው በተደባደቡ ቁጥር ምን አደባደባቸው ብሎ የሚጠይቅ የለም። ከዚያ ይልቅ መስደብ መሸርደድ ማዋረድና ሙድ መያዝ ለምደናል።
ባገራችን ከቤተመቅደስ እስከ ስቴድየም ድረስ ጎሰኝነት ያልነካካው ተቁዋም እንደለሌ እናውቃለን። ተማሪዎች ከሌላው የከተማ ነዋሪ የከፋ ጎሰኝነት እንደተሸከሙ የምናረጋግጥበት ሚዛን የለም። ልዩነቱ የኑሮ ሁኔታ ይመስለኛል። የዩንቨርሲቲ ተማሪ የኑሮ ሁኔታ ለግብግብ እንጂ ለግልግል የተመቼ አይደለም።
እንዴት በለኝ!!
ከዩንቨርሲቲ ውጭ ለመኖር የታደልህ ሰው ከሆንህ አለምህ ሰፊ ነው። ለውጥረትህ ብዙ ማተንፈሻ አለህ። የጎረቤትህን አመል ካልቻልከው ሌላ ቤት ትከራያለህ። ሌላው ቢቀር በቤትህ ውስጥ ንጉስ ነህ። ፒያሳ የምትጠጣበት ቤት ውስጥ የሚለክፉህ ዱርየዎች ካሉ ትተህላቸው ረከቦት ጎዳና ትመጣለህ። መንግስትህን መምረጥ ባትችል እንኳ የትና ከማን ጋር እንደምትውል ትመርጣለህ።
ባንፃሩ ዩንቨርሲቲ በፈቃደኝነት የሚታሰሩበት ማጎርያ ቦታ ነው።አብሮህ የሚያድረውን ሰው እንኩዋ መምረጥ አትችልም። የሰደበህን ሰው ቦታ ቀይረህ በቀላሉ አትፋታውም። መመገቢያ አዳራሽ ስትገባ ላንተ ያልደረሰህን ቅልጥም ሲከካ ታየዋለህ። ትንሽ ቆይቶ ላይበራሪ ውስጥ ፈልገህ ያጣከውን መፅሀፍ በወፍራም ምራቅ እያጣቀሰ ሲገልጥ ታገኘዋለህ። ቴሌቢዝን ለማየት አዳራሽ ስትገባ ከፊትህ ተጎልቶ የየካን አቀበት በሚያክል ትከሻው ይጋርድሃል። አንተ ለራስህ : የፈታና ውጥረት የወሲብ ውጥረትና የገንዘብ እጥረት አፍኖሃል። ለጊዜው የምታገኘው ማስተንፈሻ ዱላ ነው። ለዱላው ደግሞ ህጋዊ ሽፋን ትሰጠዋለህ። “በማንነቴ ምክንያት ሲሰድበኝ ራሴን ተከላከልኩ ትላለህ”። ህገመንግስቱም እንደምንም ይደግፍሃል። ፓርቲውም ያቅፍሃል።
ብዙ ተማሪ ዩንቨርሲቲ ከመግባቱ በፊት ከተወለደበትና ከተማረበት ቀበሌ ባሻገር ያለውን አለም አያውቀውም። መምህራኑም ማትሪክን እንዴት እንደሚያልፍ እንጂ ልዩ ልሳንና ባህል ካላቸው ሰዎች ጋር አብሮ የመኖር ፈተናን እንዴት እንደሚያልፍ አላስተማሩትም።
ተው ባክህ!! የተማሪን ጣጣ ከለታት አንድ ቀን ተማሪ የነበርን እናውቀዋለን 🙂
አብን ተውትና ንገሩት ለወልድ
ተገርፏል ተሰቅሏል እሱ ያውቃል ፍርድ
እንዲል ባለበገናው።