ቅዳሜ ቅዳሜ ማታ በዙረቴ የማልደርስበት የከተማችን ክፍል የለም። ሳምንት ወይ አስራ አምስት ቀን በሙሉ ከቤት ሳልወጣ እቆይና፣ እመሽግና አንድ ቅዳሜ መርጬ ከወጣሁ ግን የምመለሰው ተበለሻሽቼ ነው። በደንቤ ሳምንት፣ ሁለት ሳምንት ሙሉ ከቤት አልወጣም…… ከእሁድ እስከ ዓርብ። ብዙ ጊዜ ቅዳሜ ግን ከምሽቱ አስራ አንድ ሰዓት ጀምሮ እግሮቼ የማያርፉበት የከተማዋ ክፍል የለም። ከፒያሳ በሜክሲኮ አደባባይ አድርጎ ቄራ። በፒያሳሳ በሐብተጊዮርጊስ ድልድይ አድርጎ በመርካቶ በሰባተኛ እስከ ልደታ። እንደ አውሬ ነው የሚያደርገኝ። በዚያን ዕለት የማውቀውን ማንንም ሰው መገናኘት አልፈልግም። በሕይወቴ ወጥ ውስጥ ትንንሽ የእብደት ቅርንፉድ የልክስክስነት ኮረሪማ የባለጌነት ነጭ ሽንኩርት የደደብነት ጥቁር አዝሙድ…… የመሳሰለ ልጨምርባት እፈልጋለሁ። እነዚህ ቅመሞች ያሉባትን ሐጢያታዊ ማታና ምሽት ከሰዎች ጋር ልኖራት ግን አልፈልግም። ይኽቸን ዓይነት እብደት ከሚያውቁት ሰው ጋር ሆነው ሲሰሯት ትቀጥናለች። ትዕዝብት፣ ትችት፣ ’ይቅርብህ’ ’ጥሩ አይደለም’ ’ይደብራል’ የተሰኙ ቃላቶችና የሚከስቷቸው ስሜቶቶች ይወረውሩብኛል። በቂ ነፃነት የለውም። ያቺ የእብደት ቀኔ የፍፁም ነፃነት ቀኔ ናት። አዲስአባ…… የቅዳሜ አዲሳባ የእኔ ጦር ሜዳ ናት። ፊታውራሪ እኔ፣ ተራ ወታደሩ እኔ። አዛዥ እኔ ነኝ ታዛዥ እኔ።
የግሌም ካርኒቫል ነው።
በግል ባሕሌ ሶስት ወይም አራት የሴት ጓደኞች ያስፈልጉኛል። ቢመቸኝና ቢቻል በየወሩ ይቀያየራሉ። ማግኘቱ አስቸጋሪ ቢሆንም መጣለቱ ግን ቀላል ነው። ስልክ ካለመደወል አንስቶ በማኩረፍ አድርጎ እስከተራ መናጀስ ድረስ ከሴት መለያያ ይጠቅማሉ። ወይም ከመሐል አጉል ፀባይ ማሳየት…… ገብጋባ መሆን፣ የቆሸሸ መልበስ፣ ሰውነት ሳይታጠቡ መሔድ፣ ጥፍርን አለመቆረጥ……. እነዚህ ደ’ሞ ካላዋጡ ከሌላ ሴት ጋር መታየት። ከልጃገረዶች መዋል ግን አሰልቺነት አለው። የሚያሰለቸኝ በቂ ሐጢያት ስለሌለው ይሆናል…… በቂ ሰይጣናዊነት።
ቅዳሜ ታዲያ ሐጢያቴን የምኖርባት ቀን ናት። ሰይጣንነቴን የምፈትሽባት ቀን ናት። ወይም ማን ያውቃል የባሕርዬ ሌላው ጎን ትሆናለች። ያቺ ዕለት ግን በደንቡ ወጣቶች ጎን ለጎን እየተራመዱ የሚሳሳቁባት፣ ወዳጆች ጠረጴዛ ከበው የሚጫወቱባት፣ ጨዋ በየቤቱ ተጋድሞ፣ ተቀምጦ ቡና የሚጠጣባት ነት። ጓደኞቼ ፒያሳ እቴጌ ሆቴል ናቸው። ወግ ቀደዳ፣ ሐሜትና ቢራ ጭለጣ። የሚጠበቅ። የተለመደ ቦታ።
ፐቲ ሲለቃለቅ……
እሁድ ብቻ ነው እኔ እሱን ቦታ የማየው። ቅዳሜ ዕለት አልፌው ነው የምሔድ። ሰው ያለበትም አይመስለኝ። ነፍሳችን ወጥ ውስጥ አንዳንዴ ሚጥሚጣ ጠብ ካለደረግንበት ተቃጥለን የምናልቅ አይመስላችሁም? ሃሃሃ። ትንሽ ብልግና። ትንሽ ስድነት። ትንሽ አፍራሽነት። የመጨረሻው ቅዱስ ሰውም ስድነት አያጣም። ንፁሕ ብለን በሰየምነው ነገር ውስጥ እንኳን ጉድፍ አይጠፋም…… የአስተያየት ጉዳይ ነው።
……ዛሬ ቅዳሜ ከየትኛዋም ጓደኛዬ ጋር ቀጠሮ የለኝም። የፈለጋቸው ሊሔዱ ይችላሉ፣ ሊጠበሱ ይችላሉ። እንደ ፈለጋቸው ከፈለጋቸው ጋር ሊወድቁ ይችላሉ። የመረጥኳቸው ለሥጋ ነው……እነሱም መምረጥ መቻል አለባቸው። ለዚህም አይተናነሱኝም።
አንዳንዴ ግን በዚህ ቅዳሜ ዕለት ደስ የማሰኘው ነፍሴን ይሆን ሥጋዬን የትኛውን እንደሆነ ይምታታብኛል። ምናልባት እንዲመቸኝ ልግለፀውና…… በሥጋ፣ በስድነት ጉዳይ በኩል አድርጎ ነፍስን በአበባ ወንዝ ማጠብ……. ብለው። (ተፈላስፌ ሞቼአለሁ…… ሃሃሃ!)
ከሁሉ ነገር (ብዙ ጉዳይ የምፈፅም አይመስልም?) በመጀመሪያ የማደርገው ነገር ያለገደብ መጠጣት ነው። ቢራ ሳይሆን ጂንና ብራንዲ። ቢራ ሽንት ነው። እኔ ደ’ሞ ፊኛዬን የመለጠጥ ስፖርት የማሠራበት ምክንያት የለኝም። አራት ኪሎ ፓርላማ ጎን ካለው የሉካንዳ ሱቆች ሰፈር በመጀመሪያ ኪሎ ቁርጤን እበላለሁ። ቁርጥ እንደምበላ የሚያውቅ የለም። ቅዳሜ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ግን ቁርጥ በሚጥሚጣ፣ ቁርጥ በአዋዜ እበላለሁ። መብላት ነው። ከዚያ እያላበኝ እወጣና ግሮሰሪ ገብቼ አንድ ሁለት ጂን እወረውራለሁ። ቁርጥ። ጂን። ይሔዳሉ። ሲፈጠሩም ለሽርክና ነው። እውስጥ ሲገናኙ አይራበሹ፣ አይታገሉ ተቃቅፈው ቁጭ ነው። ጆክ እያደረጉ። እሳት የመሰለ ቁርጥ ሥጋ። ውሐ የመሰለ ጂን።
የምዞረው ደ’ሞ በእግሬና በታክሲ ነው። የተጠጋጉ ምግብ ቤቶችና መጠጥ ቤቶች ባሉበት በእግሬ፣ ከተራራቁ በታክሲ። አንዳንድ የማውቀው ሰው ያጋጥመኛል ’ቀጠሮ አለብኝ’ እላለሁ። ሌላ ምክንያት አይጠፋም ’የምሔድበት አለ’ የምትገርም መልስ ናት’። ትደመጣለች። ሰው የሚሔድበት ሳይኖር ’የምሔድበት አለ’ ሊል ይችላል። ግን ይደመጣል። ይታመናል…… እንደ አጥጋቢ መልስ። ፀሐይ ስታዘቀዝቅ በየቡና ቤቱ እየገባሁ የምታምር ሴት እፈልጋለሁ። መበላሸት ምኞቴ ነው። መበላሸት ምኞቴ ነው። የጥፋት ፍላጎትም ይሆናል። በቁርጡና በጂኑ እያላበኝ ሴት ለመኝታ እጠይቃለሁ።
……ዛሬ ግን አልተዋጣም። ደክሞኛል። አርብ ዕለት ከሰዓት በኋላ ከሥራ ቀርቼ ያወጣኋት ባለትዳር አድክማኛለች። እኚህ ባለትዳር ባሎች ሚስቶቻቸውን ምን ያበሏቸዋል…… ወይስ ያለመጥገብ ነው። ሌላ ጊዜ አይመቻትም ስለዚህ ለዓርብ ተስማማን። ከሥራ ቀርቼ ከከተማ ወጣ ያለ ቦታ ሔድን። ማታ ሦስት ሰዓት ቤቴ ስገባ…… ኮቴ ከላዬ ተንሸራቶ ሊወድቅ ምንም አልቀረው።
ቢሆንም የሰንበት የሰንበት ሽፍትነቴን ማንም አሮጊት ባለትዳር እንድታበላሽብኝ አልፈለግሁም። የሴት ፍላጎቴ ቢደክምም እንኳን…… እየጠጣሁ መብላቴን አላቆምኩም። ከአራት ኪሎ ጀምሬ በፒያሳ አድርጌ ልደታ ገባሁ። ልደታ ግር የሚያደርገኝ ቦታ ነው። ግር ይልብኛል። ከአብነት እስከ ደሴ ሆቴል….. ከደሴ ሆቴል እስከ ባልቻ ሆስፒታል…… የዳርማርን ፋብሪካ ቀንሰን፣ የፍርድ ቤቱን የግቢ ዛፍ ላጭተን የሚቀረው ሠፈር…… አርጅቶ የተቀዳደደ መታደስ የሚጠብቅ የወደቀ ፍራሽ ይመስላል…… ሺህ ዘመን የተተኛበት። ስልት የለውም ዝብርቅ ነው። መኖሪያውና መስከሪያው ተባውዞ ነው። የነዋሪው አእምሮ ይሆናል። ጠቅላላ የአዲሳባ አእምሮ ይሆናል። የተዘባረቀ። ወይም ያገሪቷ…… የተቃወሰ ነው።
ከሰማይ የወረደ ፍርፍር
One Comment
አዳም በጣም የምወደዉ ደራሲነዉ።