በልጅነቴ ትዝ ከሚሉኝ መፈክሮች አንዱ “ያልሰራ አይብላ” የሚል ነው። ስራ ብሄራዊ ሀይማኖት ሆኖ ነበር። ይሄ ደግሞ በጊዜው ፎቶ አነሳስ ላይ ሳይቀር ይንፀባረቃል ፤ አንድ ሰው ፎቶ ሲነሳ የሆነ ሰርቶ ማሳያ ነገር ፎቶው ውስጥ ማካተት ነበረበት፤ የቤት እመቤት ከሆነች ጥጥ እየፈተለች ወይም ምስር እየለቀመች ትነሳለች፤ ገበሬ ከሆነ የማሽላ እሸት አንጠልጥሎ ፤ የእንጨት መሰንጠቂያ ያለው ወጣት ደግሞ የሰራውን ቁምሳጥን ተሸክሞ ይነሳል።
አንድ ቀን ከአባቴ ጋር ፖሊስ ጎረቤታችን ቤት ሄድን። በቤቱ ግድግዳ ላይ አራት ሰዎች ጎን ለጎን ቆመው የሚታዩበት ትልቅ ባለፍሬም የፎቶ መስታወት ተሰቅሏል።
“ሽጉጥ ታጥቀህ የቆምከው አንተ ነህ ፤ቀሪዎች ወንድሞችህ ናቸው ልበል ?” ሲል ጠየቀ አባየ፤
“ አይደሉም! “ አለ ሰውየው” ይሄኛው ለመጀመርያ ጊዜ እጄ ላይ የወደቀው ሌባ ሲሆን እኒህ ደሞ ምስክሮች ናቸው ”
በጊዜው ሰርቶ ማሳያም ሆነ ሰሮ ማሳያ የሌለን ልጆች ግን እጃችንን አንከፍርረን እንነሳለን፤ ከፎቶ መነሳት ውስጥ በጣም ከባዱ የእጅ ማስቀመጫ ማግኘት ነበር ፤ በተለይ ትምርት ቤት ውስጥ በቡድን በቡድን ስንነሳ- የነበረብን አበሳ- አይነሳ ! እጅህን ብድግ አድርገህ አጠገብህ የቆመቺው ልጅ ተከሻ ላይ ስታስቀምጠው አመናጭቃ ትወረውርብሃለች ፤ እጆችህን በወገብህ ላይ ብታስቀምጥ” ምነው ጠላ የቀጠነባት ኮማሪት መሰልህ” ይልሀል ፎቶ አንሺው፤ አሳርፍ በሚባለው ፈሊጥ ቆመህ ብትዘጋጅ “ እጅህ ቁርጭምጭሚትህ ላይ ደረሰኮ ፤ የጭላዳ ዝርያ አለብህ? ብሎ ያሸማቅቅሀል፤ እጅህን አገጭህ ስር ብታስደግፈው “ አቡሽ! አለሎውን እስክትወረውረው በጉጉት እየጠበቅንህ ነው” ብሎ ያላግጥብሀል፤ ያለህ አማራጭ እጅህን ኪስህ ውስጥ መክተት ነው፤
ችግሩ እኛ የደሃ ልጆች የምንለብሰው ሱሪ ኪስ አልነበረውም፤ “ ሽልንግና ፀባይ ካለህ ከኮሌታህ ላይ ቀንሼ ኪስ ልስፋልህ እችላለሁ” ብሎኝ ነበር የመንደራችን መኪና ሰፊ፤ እኔ ደግሞ ከሁለቱ አንዱ አልነበረኝም፤
አንዳንዴ ከስማርት ስልክ በፊት የነበረውን ህይወት ስታስቡት ይገርማል፤ እንደዛሬ ካሜራ በኪሳችን ይዘን ከመዞራችን በፊት ከምናደንቃቸው ዝነኞች ጋር ፎቶ የምንነሳው እንዴት ነበር? ፤ ሙሉቀን መለሰ ዝንጥ ብሎ ስታዲየም አካባቢ ሲናፈስ ታገኝዋለሽ እንበል ፤
“ ወይኔ ሙሌ እንዴት እኮ እንደማደንቅህ”
“ አመሰግናለሁ የኔ ቆንጆ”
“ ካላስቸገርኩህ ፒያሳ ፎቶ ቤት ሄደን ለማስታወሻ የሚሆን ፎቶ እንነሳ?”
ሙሉቀን መለሰ ዘፈኑን ትቶ ዘማሪ የሆነው እንዲህ አይነት ውጣ ውረድ አጋጥሞት ይመስለኛል፤
በነገራችን ላይ ፤በአዲሳባ ከተማ ውስጥ የመጀመርያውን ፎቶ ቤት የከፈተው የማንኩሳ ሰው ነው ፤ መቼም አታምኑኝም፤ ግን አንዴ ጀምሬዋለሁና ልቀጥል ፤ ጎሹ ይባላል፤ ማንኩሴው ከመላው ምስራቅ አፍሪካ የመጀመርያው የካሜራ ጥበብ ባለቤት እንዴት ሆነ እሚለውን አንድ ቀን እተርከዋለሁ።
አዲስአበባ ውስጥ አንድ አርመን የቡልዶዘርና የአውቶብስ ቅልቅል የሚመስል ባቡር ሰርቶ ነበር። በምርቃቱ ላይ ተገኝቶ ባቡሩን አምስት ፎቶ እንዲያነሳው ለጎሹ ጥሪ ቀረበለት! ጎሹነት ጥሪውን ተቀብሎ አዲሳባ ሲገባ በጊዜው የነበሩት ከንቲባ ሃያ ጊዜ መድፍ አስተኩሰው ተቀበሉት፤ብቻ ስራውን ለመስራት ቀላል ሆኖ አላገኘውም፤ የከተማው ህዝብ በካሜራው ውስጥ ለመግባት ካለው ጉጉት የተነሳ ግልብጥ ብሎ ባቡሩ ጀርባ ላይ ወጣ ፤
ከዚያስ? ትሉኝ ይሆናል
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አካባቢው “ሰባራ ባቡር “ተብሎ ይጠራል።