Tidarfelagi.com

አልወዳትም እንጂ አልጠላትም (ክፍል 6-7)

(በተጋባዥነት)

ክፍል 6

ከለቅሶው ድንኳን ባሻገር ቁጭ ብዬ በግድ የምታለቅሰዋን ትንሿን እህቴን አያታለሁ። “ኤዱዬ አይዞሽ!” ብለው በደጋገፏት ሰዎች መሀል ሆና ፊቷ ላይ የማየው ህይወት አልባነት እናታችንን አስታወሰኝ። ለመጨረሻ ግዜ እናቴን ያየኋት የሞተች እለት ነበር።የአስራ አራት አመት ጎረምሳ ሆኜ። የመጀመሪያም የመጨረሻም የገደልኳት እናቴን ነው። ወልዳ ራሷን ስታ ስትንፈራገጥ ነርሶቹን ቀድሜ ገብቼ በትራስ አፍኜ ጨረስኳት። ማንም አላየኝም። የዛኑ እለት ምሽት ከጉዲፈቻ አሳዳጊዎቼ ጋር ወደማድሪድ በረርኩ። ጉዋፓ!!! ላቭሊ ማለት ነው በስፓኒሽ። ይኸው ከሰላሳ አመት በኋላ የሙት ልጅ ያደረግኳትን እህቴን አፈላልጌ ብመጣ የእንጀራ እህቷ ቀብር ላይ ደረስኩ። አሁንም ፊቷን አየሁት። በድን ሆናለች። በድን ሆና እንዳደገች የሚያውቀው ግን እንደኔ የናታችንን በድን ገፅ ያየ ብቻ ነው። ውስጧ የለም በመሀል ብቻ “እህቴ!” የሚል ማጓራት ይፈነቅላታል። የተወለደች እለት ገድያታለሁ ማለት ነው።

አስከሬኑ ወደቀብር ቦታ ሲንቀሳቀስ የእናቴ አከራዮች ወይም የሟቿ ወላጆች እየተንዘፈዘፉ በሰው ተደግፈው በአጠገቤ አለፉ። ያኔውኑ የእናቴና የነሱ ንግግር ጆሮዬ ላይ አንቃጨለ። የዛኔ አስራ ሶስት አመቴ ነበር። ከአያቶቼ ጠፍቼ ከደሴ አዲስአበባ በመከራ ደርሼ እናቴን ፍለጋ ለቀናት ተርቤ በራቸውን አንኳኳሁ። እናቴ መጥታ በሩን ከፈተችልኝ።ፎቶዋን ዘወትር አይ ስለነበር ከመወፈሯና ከመኳኳሏ ውጪ መልኳ አላደናገረኝም። እንዳየኋት ተዝለፍልፌ ወደቅኩ።ለደስታ እንኳን የሚሆን እንጥፍጣፊ ጉልበት አልነበረኝም።በሰመመን እናቴ ከአከራዮቿ ጋር የተባባለችው እንደህልም ትዝ ይለኛል። “ሊለምን ነው መሰለኝ….ውሀ አምጡ ውሀ” ውሀ ሲደፉብኝ ሲግቱኝ እየተንቀጠቀጥኩ ነቃሁ። እናቴ አይኔን እያየች”አቡሽዬ እንጀራ ልስጥህ?” አለችኝ።”እ…ሺ” አልኳት።አከራዩዋ ” በረንዳ ላይ ሁን ለንፋሱ ጥሩ ነው” አለችኝ ያደፈ ልብሴን በጭንቀት እያየች። አሁንም ከሰላሳ አንድ አመት በኋላ ልማድ ሆኖብኝ ከደጃፋቸው ቆሜያለሁ። ሁሉም ከድንኳኑ ተነቅሎ ሲንቀሳቀስ መኪናዬን አስነስቼ ተከተልኳቸው። መካነ መቃብሩ ጋር ደርሰን ሀተታ ምናምኑን ጨራርሰው ሳጥኑ ጉድጓድ ሲገባ ኤዱ ተዝለፍልፋ ወደቀች። ተስፈንጥሬ “sorry CPR!CPR!” እያልኩ ከመቅፅበት ከወደቀችበት አቅፌ ተሸክሜ ወደዳር አወጣኋት። ከጓደኞቿ ሁለቱንና ኤዱን ጭኜ ወደሆስፒታል በረርኩ። እነሱን አድርሼና የህክምና ከፍዬ ወደሆቴሌ ተመለስኩ።እንደገባሁ ሻወር ወስጄ ተጋደምኩ። እንባዬ ያለማቋረጥ ይፈስሳል። አራሷ ኤዱ…ሳታድግ የቀጠፍኳት አበባዬ…ያኔ ተሳስቼ የገደልኳት እሷን ነው እንዴ? ለምንድነው ከሷ ፊት የእህቷ ሬሳ ሳጥን የወዛው? ለምን?

ክፍል 7

አልጋዬ ላይ እንደተጋደምኩ የኤዱ ሀሳብ እያብሰለሰለኝ ሳለ ስልኬ ላይ ቴክስት ገባልኝ።አንድ የምጠብቀው መልእክት ስለነበር ተንገብግቤ አነሳሁት።እንዲህ ይላል “እንዴት ነህ? አምስት ኪሎ ሮሚና ካፌ ከሰላሳ ደቂቃ በኋላ እንገናኝ” ጊዜ ሳላጠፋ ተነስቼ ወጣሁ።ቦታው ላይ ስደርስ ቀጠን ያለ ወጣት እጁን ለምልክት አነሳልኝ። ከፊቱ ሄጄ ቁጭ አልኩ። “ያዘዝከኝን በሙሉ ሰርቻለሁ። የኤዶም የትምህርት ማስረጃ እዚህ ላይ አለልህ። ከአስረኛ ክፍል በኋላ ግን የለም።” አለኝ አይኑ እየተቅበዘበዘ። ያላቸውን ዶክመንቶች ከፍቼ አየኋቸው። እህቴ በከፍተኛ “ደደብ” ማእረግ የወደቀችባቸው የትምህርት አይነቶች ተደርድረዋል።ለልፋቱ አመስግኜው ሁለት መቶ ዶላር እጁ ላይ ሸጎጥ አድርጌለት ወደቀጣይ ቀጠሮዬ ገሰገስኩ።
ሰባተኛ አካባቢ ጥብቅብቅ ያሉ ቤቶች መሀል በተሰጠኝ አድራሻ መሰረት የእናቴን የስራ ባልደረባ የአሁን ቁርበት አሮጊት ተቀምጣ ስታንቀላፋ አገኘኋት።ስታየኝ መልአከ ሞት የመጣባት ያህል ገረጣች። “አንተ ከይሲ! እዚህ ምን ትሰራለህ?” አለችኝ እየተንቀጠቀጠች።”ተረጋጊ! የኤዶምን ቤት እንደምታውቂ ስለማውቅ እንድትመሪኝ ብቻ ነው የመጣሁት።የኔ እርዳታ ያስፈልጋታል።” በወላለቀው ጥርሷ ትስቅብኝ ጀመር። “እሺ ባክህ አሁንም ወንድሟ እንደሆንክ ነው የምታስበው?” ብላ የቢጃማዋን ቁልፎች መፈታታት ጀመረች።”ምን እየሆንሽ ነው?” አልኳት የተጨራመተ ገላዋ መታየት ሲጀምር።”ያቺ በልጅነትህ ያቀመስኩህ ነገር ከናፈቀችህ ብዬ ነው” አለችኝ በቀነዘረ የአሮጊት አይን እያየችኝ።ብልጭ ብሎብኝ ሽጉጤን ግንባሯ ላይ ደቀንኩባት።ደርቃ ቀረች።”ስሚ አንቺ ቆሻሻ…ያኔ ያባለግሽው ህፃን አይደለሁም ዛሬ! የእህቴን ቤት ብቻ አሳይኝ አሁን ተከራይታ የምትኖርበትን!!!አለዛ አናትሽን እበትንልሻለሁ።” ብዬ አስበረገግኳት።

መኪናዬ ውስጥ ጨምድጄ አስገባኋትና በሷ መሪነት ልደታ ኮንዶሚኒየም ጋር ስንደርስ ቆምን። ኤዱ በሰው ተደግፋ ወደቤቷ እየገባች ነበር። አንድ ትልቅ የቤት ስራ የጨረስኩ ያህል ተሰማኝ። የምትኖርበትን ማወቅ። አሮጊቷን ሰፈሯ የመመለስ ፍላጎት ስላልነበረኝ እዛው ጥያት ወደ ማረፊያዬ ተመለስኩ። ያኔ እሷም እንዲህ ነበር የተጫወተችብኝ። ሳቋ…ያ ቀፋፊ የዘማዊት ሳቋ ትዝ ይለኛል…እናቴ ፊት ስትነሳኝ እሷ የአስራ ሶስት አመት ወንድነቴን እየነካካች”ኧረረ….ይሄማ ይደባልቀኛል” ብላ ላዬ ላይ ስትከመር…የማይሆን ነገር ሆነ። እንባዬ አሁንም ይፈሳል። ወደ ክፍሌ ገብቼ የቀጣይ ቀን እቅዴን አዘጋጀሁ። የቀኑ መጠሪያ”ኤዶም” ይላል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *