(በተጋባዥነት)
ክፍል 8
በቀጣዩ ቀን በጠዋት ተነሳሁ። የERAን ‘Divano’ የተሰኘ ሙዚቃ እየሰማሁ በሞቀ ውሀ ሰውነቴን አስደበደብኩ።ሙዚቃውና የውሀው እንፋሎት ተደማምሮ የሆነ ስርየት የመስጠት ስሜት አለው። እንደከባድ ፀሎት ሁሉ ልቤ ፍርስ ይላል።ከየት እንደመጣ የማላውቀው የእጣን ሽታ አፍንጫዬን ያውደዋል።ልቤ ወደህፃንነቴ ይሸፍትብኛል። ደጓ አክስቴ በህይወት ሳለች ወደሞቀው የአያቶቼ ጎጆ ነፍሴ ትመንናለች። “እሰይ የኔ ድምቡሼ ና ፈንዲሻ ልጨምርልህ! እሰይ የኔ ማር…” አክስቴ ከእጣኑ መሀል እየተፍለቀለች የማሽላ ፈንዲሻ ዘግና ትሰጠኛለች።ይሄ ትውስታዬ ነው ራሴን እንዳላጠፋ በሰራሁት ሀጢያት ወደሲኦል እንዳልነጉድ የሚያስገድደኝ። ዳግም እንዲህ አይነት ፍቅር እስካገኝ መሞት አልፈልግም። እንባዬን የሚያብስ ለስላሳ መዳፍና ውብ ጠረን አግኝቼ ነው መገነዝ የምፈልገው።
ልክ ሁለት ሰአት ሲሆን የኤዶም ሰፈር ደርሼ ራቅ ብዬ ቆምኩኝ። ብዙ ሳታስጠብቀኝ ወጥታ የሆነች ቪትስ ውስጥ ጥልቅ አለች። በቅርብ ርቀት ተከተልኳት። ሜክሲኮን እና እስጢፋኖስን አልፋ መኪናዋ ወደ መገናኛ መስመር ቀጥታ ተሻገረች። ተከተልኳት። ለም ሆቴል ስትደርስ ወደ ሀያ አራት የሚወስደውን መንገድ ይዛ ወደ ቀኝ ታጠፈችና ብዙ ሳትጓዝ ወደ ሰፈር ውስጥ በሚያስገባው ቅያስ ተሰወረች። ቅያሱ ውስጥ ተከትያት ገባሁ። መኪናዋ ቆማ ኤዶም ወረደችና ወደ አንድ ፎቅ ቤት ውስጥ ገባች።ግቢው በር ላይ የስነ ልቦና አማካሪ አድራሻ ተለጥፏል። እሷ እስክትወጣ መኪናዬ ውስጥ ቆየሁ።ከአርባ ደቂቃ በኋላ ተመልሳ ወጣች።ፊቷ ላይ ምንም አይነበብም። ዝም ብላ በአጠገቤ አልፋ ሄደች። ባለፈው ካየኋት በጣም ከስታለች።
እሷን ትቼ ወደ ህክምና መስጫው ጊቢ ገባሁ። ከሪሴፕሽኑ ጀምሮ ለማበድ ያቆበቆበን ነፍስ ገርቶ የሚመልስ መንፈስ ያለበት ቤት ነው። እንግዳ ተቀባዩዋ ስሜንና ቀጠሮ እንዳለኝ ጠየቀችኝ። “ቀጠሮ የለኝም እራሴን ከማጥፋቴ በፊት አንድ እድል ልሞክር ብዬ ነው የመጣሁት” አልኳት በአጭሩ።ተደናግጣ ለባለሙያው ስልክ ደወለች።ይሄ የሰይጣን ተንኮሌ በውስጤ አሳቀኝ። እየመራችኝ ወደአንደኛ ፎቅ ወጣን። እጅግ ንፁህ ቢሮ ውስጥ አንድ ጎልማሳ ቄንጠኛ ሶፋ ላይ ተቀምጧል።ቀና ብሎ አየንና “አመሰግናለሁ መሄድ ትችያለሽ” ብሎ አሰናበታት። ልጅቷም የቢሮውን በር መለስ አድርጋው ወደ ታች ተመለሰች። አማካሪው ብዙም የመደነቅ ፊት ሳያሳየኝ “እ…ሺ ለምንድነው ለመሞት የተጣደፍከው?ወይስ ወረፋ መጠበቅ አልፈለክም?” ነገረ ስራው የነቃብኝ ይመስላል። “የኤዶም ታላቅ ወንድም ነኝ። ከዘገየሁ እሷ የምታመልጥ አይመስልህም?” ጥያቄውን በጥያቄ መለስኩለት። ቀና ብሎ በድንጋጤ አየኝ….
ክፍል 9
አደነጋገጡ የሆነ የጠፋ ቅርስ ያገኘ ነው የሚመስለው። ልክ የሚናገረው የበለአም አህያ ሳልመስለው አልቀርም። “አንድም ነገር ሳትናገር ነው እኮ የወጣችው…ቤት ውስጥ ያላት ፀባይ እንዴት ነው?” አለኝ። “አላውቅም” አልኩት አሳጥሬ። “ከልጅነቷ ጀምሮ ድብቅ ነች ማለት ነው…” በጥያቄ አይን አየኝ። “አይ እኔ አብሬያት አላደግኩም።ይልቅስ አንድ ነገር ላስቸግርህ?” አልኩት ዶክተሩን። “የምችለው ከሆነ” አለኝ አይኔን እያየ…”ኤዶም በህይወት መኖሬን እንኳን ስለማታውቅ አደራህን የኔና አንተ ሚስጥር ይሁን።አደራህን ራሷን የመጉዳት አዝማሚያ ካየህባት በዚህ ስልክ ደውልልኝ” ብዬ ካርዴን አውጥቼ ሰጠሁት። አላመነኝም። “ወንድሟ ባትሆንስ?በዚያ ላይ የታካሚዎቼን ሚስጥር አሳልፌ መስጠት ሙያዬ እንደማይፈቅድ ያጣኸው አይመስለኝም…” አቋረጥኩት “ይቅርታ ዶክተር ወንድሟ ባልሆን እንኳን ህይወቷን ላድን እንጂ ልጉዳት አላልኩህም። በዚያ ላይ የማትናገር የማትጋገር ልጅ ለመጥቀም እንደኔ አይነት ምንጭ ያስፈልግሀል። ከልጅነቷ ጀምሮ ያሉ መረጃዎችን እየሰበሰብኩ ነው። በተቻለ መጠን ተጋግዘን እህቴን ማትረፍ አለብን”እንባዬ አይኔን ሲያቃጥለው ታወቀኝ። ዶክተሩ “እባክህን ተቀመጥ…ሻይ ወይስ ቡና?” አለኝ በሀዘኔታ እያየኝ። “ጥቁር ቡና ይሁንልኝ” አልኩት ለመረጋጋት እየሞከርኩ። “ኢትዮጲያ ውስጥ ነበርክ?” አለኝ። “የለም ከጣሊያን ነው የመጣሁት” አልኩት። ከዛ በኋላ ምንም አልጠየቀኝም። ምናልባት ቀስ እያለ ሊገዘግዘኝ ይሆናል። የጋበዘኝን ቡና ጠጥቼ አመስግኜው ወጣሁ።
ምናልባት የስራ ኢሜይል ካለኝ ብዬ የስልኬን ኢንተርኔት ሳበራው ብዙ መልእክቶች ገቡ። የሊና ግን ከሁሉም በላይ ተደጋግሟል። “ማት እንዴት ነህ! በጣም ናፍቀኸኛል። የራሴ ማድረግ ቢያቅተኝም እንዲሁ ሳይህ እንኳን ደስ ይለኝ ነበር። መች ነው ተመልሰህ የምትመጣው?” የሚል ነበር። ምስኪኗ ሊና ሴትን በፆታዊ ፍቅር ለመቅረብ ድሮ ገና እንደተደፈርኩ አታውቅም። ምናልባትም ግብረሰዶማዊ ያላረገኝ ውስጤ ያለው እንጥፍጣፊ የሟች አክስቴ ፀሎት መሆኑን አትረዳም። ለመጀመሪያም ለመጨረሻም ጊዜ ከሴት ጋር የተኛሁት በአስራ ሶስት አመቴ የእናቴ ጓደኛ አስገድዳኝ መሆኑን ዛሬ እርቃኗን ባያት ምንም የሚቆም ነገር እንደሌለኝ እንዴት ብዬ ላስረዳት?
ከሆቴሌ በር ላይ ስደርስ የቅድሟ ቪትስ የመኪና ማቆሚያ ቦታ ላይ ተገትራ ጠበቀችኝ። ታርጋዋን በደምብ አየሁት። አዎ መኪናዋ ራሷ ነች። ተረጋግቼ መኪና አቆምኩና ወደውስጥ ልገባ ስል”ማቲ ባላየ ልታልፈኝ ባልሆነ” አለችኝ አንዲት የቀይ ዳማ ቆንጅዬ ልጅ። ማን ስሜን ነገራት? ሰላይ ሆንኩ ስል ተሰልዬ አረፍኩት?