የኑሮ ውድነት የማያሳስባቸው ነዋሪዎች ፥ ደላላ፥ የመሬት ሽያጭ ሰራተኛ ፥ ሰባኪ ፥ ታዋቂ ዘፋኝ እና አነቃቂ ንግግር አቅራቢ ናቸው፥ ባለፈው አንድ የታወቀ አነቃቂ ነኝ እሚል ሰውየ ላስር ደቂቃ አፉን ያለገደብ ወለል አድርጎ ከፍቶ ሲያዛጋ አየሁት፥ ጠጋ አልሁና ”በውኑ ከዚህ አፍ መነቃቃት ሊወጣ ይችላልን?“ ስለው በስንግ ቃርያ ጥፊ ወለወለኝ! ብታምኑም ባታምኑም የሌለ ነቃሁ! እውነት ለመናገር በንግግር መነቃቃት የሚባል ነገር የለም፥ በንግግር የሚነቃቃ ንግግሩ ሲጠናቀቅ ይተኛል። እውነተኛ አነቃቂዎች የሚከተሉት ናቸው፥ የደመወዝ ጭማሪ፥ የኢኮኖሚ እድገት፥ ፍትሀዊ አስተዳደር እና የቶሞካ ቡና።
ባለፈው እኔና ምኡዝ በረንዳ ላይ ቁጭ ብለን ቡና ስንጠጣ፥
“ስማ፤ ዘመኑ ክፍቷል፥ ተጠንቀቅ፡ አለኝ
“እሞክራለሁ”
“ በጊዜ እየገባህ ነው?”
“ አዎ ! ለምሳ ቤቴ ከገባሁ አልወጣም”
“ ይህም በዛ! ተጠንቀቅ እንጂ ተንቦቅቦቅ አልተባልክም”
ድንገት አንድ ጎረምሳ በረንዳው ላይ ዱብ አለና ጠረጴዛው ላይ የነበረውን የምኡዝን ስልክ አፈስ አድርጎ ዘለለ ፤ ምእዝ ተከትሎት ሊሮጥ ሲቃጣ ክንዱን ያዝ አደረኩትና “ ቆይ ! ትንሽ አቫንስ እንስጠው “ አልሁት፥ ካሜሪካ ከመጣሁ ወዲህ ጂም ስላልሰራሁ ሌባው ሮጦ ያሯሩጠኛል ፥ፍሪምባየ አካባቢ ያለውን ስብ እንዳቀልጥ ያግዘኛል ብየ ተስፋ አድርጌ ነበር፥ ሌባው ግን ያልተጠበቀ ነገር አደረገ። ባቅራቢያው አቁሞት የነበረው ሞተር ሳይክል ላይ ጉብ ብሎ ኮለኮለው፥ እኔና ምኡዝ ስንከተለው አስፖልቱ ዳር ትራፊክ መብራት የያዘው ሌላ ኮስማና ሞተረኛ አየን፥
“አንተም የሱ ግብረአብር ሳትሆን አትቀርም “ አልሁና ኮሌታውን ጨምድጀ ያዝኩት
“እረ ፖስተኛ ነኝ “ አለ ሰውየው፥
“ጭራሽ ፖስታም መስረቅ ጀምራችሁዋል” አልሁና ከነሞተሩ በጠረባ ጣልሁት፥ ከጥቂት ደቂቃ በሁዋላ በማረክሁት ሞተር ጉዋደኛየን አፈናጥጨ ሌባውን ማሳደድ ቀጠልሁ። ሌባው ሞተሩን አግለበለበው ! ጭራሽ የሆነ ጊዜማ እንደ አገው ፈረስ አቆመው፥ አንዱን ሲኖትራክ ዘለለው፤ ቀጥሎ ውሀ ልማትን የሚገምሰውን የባቡሩን ድልድይ እመመመር ብሎ አለፈው፥
በመጨረሻ ምኡዝ እንዲህ ሲል ሰማሁት፥
“ይሄ ልጅ ቀን ጎድሎበት ነው እንጂ ሆሊውድ ወይም ቦሊውድ ውስጥ የአክሽን ፊልም አክተር መሆን እሚችል ሰው ነበር ፥ በል አባርረን እንድረስበት እና ላፕቶፕ እንሸልመው”