ከማውቃቸው ሰዎች መሀል በነውጠኝነቱ ወደር የሌለው አቦሌ ነው፤ ከብዙ ጊዜ በሁዋላ አንድ የጫማ መሸጫ ቤት ውስጥ ሳገኘው ገረመኝ፤ በፊቱ ያለው ውስብስብ ሰንበር የቀለበት መንገድ ይመስላል፤ ግንባሩ ላይ የብረት ቦክስ ጠባሳ አለ፤ ግራ ጉንጩ ላይ የሰንጢ ጭረት ይታያል፤ ማላመጫው ግድም የኮብልስቶን ምልክት ታትሟል።
የባጥ የኮርኒሱን ስናወጋ ከቆየን በሁዋላ፤
“ስማ ፤ ያለፉትን አራት አመታት ብዙ መንፈሳዊ መጻህፍት በማንበብ አሳልፍያለሁ፤ ከራሴ ጋራ ተመካክርያለሁ፤ ሁሉንም አውጥቸ አውርጀ ጌታ ቡድሀን ተቀብያለሁ፤ የድሮው አቦሌ እንደሞተ ቁጠረው” አለና ትካዜ የተቀላቀለበት ፈገግታ አሳየኝ።
ወድያው አንድ ሰውየ ገብቶ ንግግሩን አናጠበው፤
“ካልሲ አለ?” አለ ሰውየው፤
“ይሄ የጫማ መሸጫ ቤት ነው፤ ካልሲ እንዴት ትጠይቃለህ?’ አለ አቦሌ።
“ጫማ ቤት ውስጥ ካልሲ መጠየቅ ምን ነውር አለው? ኬክ ቤት ገብቸ ካልሲ የጠየቅሁ አስመሰልኸውኮ”
አቦሌ ሰውየውን ትክ ብሎ አየው፥ አስተያየቱ የዘጠኝ ቡዳ አስተያየት ድምር ነው፤ ከዚያ ቡጢውን ጨበጠ፤ ከንፈሩን ነከሰ፥ ከገዛ ሀይሉ ጋር ታገለ፤ በመጨረሻ በረጅሙ ተነፈሰና “ እባክህ ለግልና ላካባቢ ሰላም ሲባል ተፋታኝ” አለው፤
ሰውየው መሰስ ብሎ ወጣ።
“ውነትም ተለውጠኻል “ አልኩት፥
“ቀላል ተለውጫለሁ፡ ከሁለት አመት በፊት ቢሆን ይሄን ሰውየ ጎድኑን እንደ አሮጌ ሳጠራ ጠርምሼለት ወህኒ ወርጀ ነበር፤ ወህኒ ወርጀ ሁለት እስረኛና አንድ ዘበኛ መግደሌ አይቀርም ነበር፤ “እባክህ “ ከሚል ቃል ጋራ የተዋወቅሁት በቅርብ ነው! ጌታ ኢየሱስ እንደ ርግብ የዋህ እንደ እባብ ብልህ ሁኑ ይላል ፤ ይቅርታ አድርግልኝና እኔ በዚህ ህዝብ ላይ ብልህ ልሆንበት ምኞት የለኝም፤ እኔ እንደ ርግብ የዋህ እንደ ሰርከስ እባብ ገራም ነኝ”
“እንዲህ ተለውጠህ ማየት ደስ ይላል “ አልኩኝ ልቤ ተነክቶ፥
“ክንዴ ላይ የነበረው ንቅሳት ትዝ ይልሀል?” አለኝ
“ደቁሰው” የሚለውን” አልሁ እየሳቅሁ
“አዎ ! ባለፈው ታቱ የሚሰራው ልጅ በጠባየ አዲስነት ተገርሞ” ቁ” ን ወደ “ ጉ” ቀይሮልኛል”
“ጌታ ቡድሀ የተመሰገነ ይሁን “ አልሁት፤
“ አሜን!”
አቦሌ ጫማ ቤቱን በጊዜ ዘግቶ ወደ አንድ ግሮሰሪ ሄደን ትንሽ ቀማመስን፤
“ ስራ ፈልግልኝ፤ ይሄ ስራ አይመጥነኝም” አለ አቦሌ ፥
ካገባደደ በሁዋላ ሁለተኛውን ቡትሌ፤
“ምንድነው ችግሩ?” ስል ጠየኩት፤
‘ጫማ ሊለኩ ጫማቸውን ሲያወልቁ ከካልሲያቸው የሚያፈልቁት ጨረር አስመረረኝ፤ ሳስበው ያፍንጫ ካንሰር ሳይዘኝ አልቀረም፤ ያፍንጫ ካንሰር የሚባል ነገር ከሌለ በኔ ጀምሯል”
“ይሄን ያህል?”
“ ተወኝ ባክህ! አንዳንዴ ሳስበው ፤ ላለፈው ሀጢያቴ ቅጣት ይሆን እላለሁ? “አለና ተከዘ፤
ትንሽ አሰብኩና ፤
“ በሰኔ ስድስት ብሄራዊ ትያትር የማቀርበው ሾው አለኝ ፤ ደና ዝግ ከዘጋሁ ቦዲጋርድ አድርጌ እቀጥርሀለሁ” አልሁት፤
“ ቦዲጋርድነት አልፈልግም፤ አንተም የኢትዮጵያ ህዝብ ስለሚወደህ ቅጥረኛ ጠባቂ አያስፈልግህም፤ ከፊትህ ያለው ስጋት ርጅና እና በሽታ ነው፤ ደምብዛት እና ጉብጠትን ደሞ በቦዲጋርድ አትመክታቸውም” አለና ተፈላሰፈ፤
“ ሌላ ምን ስራ ልሰጥህ እችላለሁ?”
“ ለምን መኪና ገዝተህ ሾፌር አታረገኝም፤ ቀለል ያለ ቴስላ ግዛ ! እኔ እሱን እሾፍርልለሀለሁ’፤ “
“ መንጃ ፍቃድ አለህ?”
“ መንጃ ፈቃድ ባይኖረኝም ማሸከርከር እችላለሁ”
“ እንሱማ አይሆንም፤’ ገገምሁ፤
አቦሌ ዘጠነኛውን ቢራ ጨለጠና እንዲህ አለ፤
“ የመንጃ ፍቃድ ትምህርት ቤት ያለው ጎረቤት አለኝ፤ መንጃ ፈቃዱን ዱቅ እንዲያረገው እለማመጠዋለሁ፤ እምቢ ካለ ሰላሳ አምስት ጥርሱን አራግፍለታለሁ”