Tidarfelagi.com

አይ ቅዳሜ!

በማርና በወተት እንደ ጨዋ ያሳደጉኝ ወላጆቼ…ቢሉኝ ቢሉኝ አልሰማ ያልኩበትን የዚህ እድሜዬን <የግሮሰሪ አመል> አሜን ብለው ከተቀበሉ እነሆ ጥቂት ሰነባበቱ…ከሰፈራችን አንደበተ ርቱዕ ቄስ ባባቴ በኩል እስከምዛመደው ስመጥር የከተማችን መሃዲንስ ድረስ በብዙዎች ተመከርኩ…እኔ እቴ!…MD!…/መስሚያዬ ድፍን!/…እንዴት ችዬ በመለኪያ ልጨክን?…<ከሷ ጋር አድሬ ሲነጋ ልሙት> አልኩ!

ከቀናት ሁሉ በላይ ቅዳሜ ትመቸኛለች…የጧቱ ጮራ-ነፋሻማው አየር-የስድስት ሰኣቱ ቀትር-የምሽቱ ቀውጢ-የቺኮቹ ነገር ሁሉም እሚምርባት ሸሌ ቀን! ቅ.ዳ.ሜ!!!

ባለፈው ቅዳሜም ያው እንደልማዴ…ቅዳ-አዳሜ እያልኩ ስነጥር…ዘመናዊነት ሽምግልናዋን ካልነጠቃት አንድ ፀዴ የካዛንቺስ አራዳ ጋር ቴብል የመጋራትና በጋራ የመዝናናት እድሉ ገጥሞኝ ነበር…አብረን ለግማሽ ሌሊት ያክል ከተዝናናን በኋላ ሂሳብ ትዘጋልኛለች ብዬ ስጠብቅ ምሽቱን በምክር ዘጋችው!

<ስማ አንተ ሸበላ…ፎቃቃ ድሃ ጠብሰህ እከክ ሆነህ እንዳትቀር በናትህ…የጃምቦ ሂሳብ ይቀንሳል ብለህ መንደር ለመንደር አትዙር…ጢቅ ዝንጥ ሽቅርቅር ብለህ ፀዳ ያሉ ሰዎች አካባቢ አትጥፋ…ይሄው ኮንቲነንታል ቅርብህ ነው…ራዲሰንም ሰፈርህ ነው…ወደ ቦሌም ጎራ በል…ፍቅር የራባቸው ስንት ዲታዎች አሉ መሰለህ…እወቅበት…አንዷን ጥለፍና ፏ በል…አንተም ጀልሶችህም ፋሚሊዎችህም ይለፍላችሁ>

እነሆ ለሳምንት ምሳዬን ዘልዬ እራቴን ክጄ ያገትኳትን ፈራንካ ይዤ፤ባለፈው ሳምንት ባ’ንድ የከተማችን ትልቅ የባህል ምሽት ከመሰየሜ እውነታ ጀርባ የዚች አራዳ ሼባ ምክር አለ…በ’ውነቱ ከሆነ ምሽቱ በቦሌ ይፀዳ ነበረ!…እኔም ወጉ ደረሰኝና ፀሐይ ካልዞረባቸው ኑሮ ከሆነላቸው የስኬት ዛር እና ቦዲ ጋርድ በግራና በቀኝ ከቆመላቸው ጋር አመሸሁ..ጨዌው በላይቭ ኦኬስትራ ነው ጀለሶቼ…የገባለት ቆሞ ያስነካዋል…ግማሹ በሸክላ ጥብስ ጭስ ታውዶ ያውካካል…ደብል ብላክ ጎልድ ሌብል….ኦኦኦ….ለካ እስከዛሬ አልተዝናናሁም…ቲሽ!

እኔም እንዳቅሜ ሺ አመት አይኖር ብዬ…አስተናጋጁን ጠርቼ ቢራ አዘዝኩ…ከጎኔ ከተቀመጡ ነጮች ትንባሆ ውስጥ አልባብ አልባብ እያለ በሚወጣ የትንባሆ ጭስ ታጅቤ አንድ ሁለት አልኩ…ሞቅ እያለኝ ሄደ…ከላይቭ ኦኬስትራው ውስጥ የብሄሮች ጭፈራ ተራውን እየጠበቀ ይጨሳል…ባንዱ የትግርኛን ጭፈራ ሲጀምር ፈዞ ደንግዞ የነበረው ሁሉ ተነስቶ ያዙኝ ልቀቁኝ አለ…እኔም የቻልኩትን እየያዝኩ ለቀቅኩ…ቤቱ ተነቅሎ እሚሄድ መሰለ…ጉራጌውን የቤቱን ባለቤትማ ማን ይቻለው…ጭራሽ ማይኩን ነጥቆ ካልዘፈንኩ ሁሉ አለ…ግራ ገብቶኝ ምነው ብል?…<ይሄ የገዥው ፓሪቲ ሙዚቃ ነው…አገራዊ ግዴታ ነው> አሉኝ…ማንን ለማስበላት ነው? ብዬ እኔም ተነሳሁ…ሙዚቃው እስኪያልቅ እንደ አቅሜ ተውረገረግኩ…ሲያልቅ ከመሃል አካባቢ <ድሮም ስትጨፍሩ እንጂ ስትገዙ አያምርባችሁም> እሚል ድምፅ ተሰማ…ቤቱ እንደገና በጥል ቀውጢ ሆነ…ባለ ማካሮዎች ባለምላሱን ይዘውት ወጡ…እሚሆነውን ልይ ብዬ እኔም አብሬ ወጣሁ…ሰዎቹ ልጁን በሸሚዙ ኳሌታ አንቀው < <ስትገዙ አያምርባችሁም> ያልከው ሎሙን አቧትኩን ነው?> አሉት…ልጁ መለሰ…<ምን ምን የመሰሉ ባለሞያ ሴቶች እያሏችሁ ጥህሎ እና እልበት ሱቅ ድረስ ሄዳችሁ ስትገዙ አያምርባችሁም ለማለት ነው> አለ…ወዲያው አቅፈው ሳሙት…ምሽቱም እንደነበረ ቀጠለ!…የኣራዳ ልጅ በመሆኔ ኮራሁ!
በ’ውነት ኣራዳ ይችላል!

ወዲያው ባንዱ ወደ አፋርኛ ውዝዋዜ ተከረበተ…ተወዛዋዦቹ ከመድረክ ወርደው ተቀላቀሉን…ከጎኔ ካለው ዲያስፖራ ጋር የቅርጫት ኳስ እሚያካክል ጡት ያስቀደመች ተወዛዋዥ ጭፈራውን ታስነካዋለች…ሰውየውም የዋዛ አይደለም…ጡቷ መሃል መቶ ብር ወሽቆ የመቶ ዶላር ዳበሳ አካሄደ…እኔማ ዝርዝር ብር እየፈለገ ሁሉ መስሎኝ ነበር…ወዲያው ጥላዬ ከብዶኝ እኔም ዞር ብል ግማሽ ሜትር እሚረዝም ሜንጫ ያነገተ ጎረምሳ እየዞረኝ ነው…ለዚ ጎረምሳ እምሸልመው ድቃቂ እንደሌለኝ እማውቀው እኔ ነኝ…ነገሩ አላምር አለኝ…በህይወቴና ሞቴ መካከል ያንድ ተወዛዋዥን ጤንነት አምኖ መቀመጡ አልነፋኝም…ቢያየኝ ቢያየኝ ዴች እንኳን አልሸጉጥ ስለው የታጠቀውን ስለት አውጥቶ ሸጎጥ አርጎልኝ ቢያልፍስ?…በመዝናናት አለም ውስጥ አምርሬ ወደምጠላው ጉዳይ ብሄድ ይሻለኛል ብዬ አስተናጋጁን ጠርቼ ሂሳብ አልኩት…ሂሳቡን ሳየው ወዲያው ሰከርኩ…ወረቀቱ የሶስት ቢራ ሂሳብን ሶስት መቶ ስልሳ ብር እንደሆነ ሲያውጅ ትንሽ እንኳን አልቀፈፈውም…ቤቱ ራሱ 360° ዞረብኝ…ሂሳቡን ሳስቀምጥ የዘወትር የጃምቦ አጣጭ ጀለሴ የታዴ ቃላት ታወሱኝ…ታዴ ማኛ < ብዙ ጠዋቶች ላይ ከባድ ሃንጎበር እሚይዘኝ በጠጣሁት ቢራ ሳይሆን በከፈልኩት ሂሳብ ነው> ይል ነበር…ታዴ እኮ ዋሽቶ አያውቅም!

በመጨረሻ…በሶስት ጠርሙስ የሶስት ሳምንት ባጀቴን የቀማኝ ቤት ላይ ሽንቴን ሸንቼበት መሄድ አማረኝ…ወደ ቶይሌት አመራሁ…ስወጣ ካንድ ኬቲ ፔሪን ከመሰለች የነጭ ቆንጆ ጋር አይን ለኣይን!…<ዋው ፈረንጅ!>…በመጀመርያ ፈገግታ ቀጥለን ሰላምታ ተለዋወጥን…<ናይስ ቱ ሚት ዩ> ነሽ…<ሄሎ ዲር> ነሽ…<ዌር ዩ ካም ፍሮም?> ነሽ…ብቻ ምን አለፋችሁ ወዳጆቼ እንግሊዝኛን ፈነጨሁባት…ለምን እንደሆን ባላውቅም ሞቅ ሲለኝ እንግሊዝኛ ይቀለኛል…ከእኩለ ሌት በኋላ የሆነውን ግን አላውቅም…ብቻ እንደ ህልም ያክል ዛሬ ላይ ትዝ እንደሚለኝ ከሆነ እንደ መልኣክ ያለች ባለ ነጭ ፀጉር ፍጥረት ስታነሳ ስትጥለኝ ነበር…የወጉ ደርሶኝ ይሆን?…ጀሊሉ ነው እሚያውቀው…ጧት ስነቃ ያየሁት ሽሮ ፍትፍት በቀዝቃዛ ውሃ የተሸከመ የማዘርን ምስኪን ፊት ብቻ ነው!
አይ ቅዳሜ!

በሉ ይመቻችሁ

One Comment

  • መለሰ commented on May 5, 2018 Reply

    አገሬን እወዳለሁ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *