ወገን ይቅር በለኝ!! እርሱን የመረጥኩት ስለ ስነፅሁፍ ግድ የማይሰጣቸውን ፊስቡከኞች ትኩረት ለመሳብ ብየ ነው። ርእሱ ሲተረጎም may I have your attention ? እንደ ማለት ነው። ከታች ያለው ወግ ስለ አዲሳበባ አይደለም። ስለ አዲሱ የግጥም መፃፌ ነው።
እስቲ በስምአብ ብየ ማካበድ ልጀምር
“የማለዳ ድባብ ” ጣፋጭ እንደተምር
የምር🤓
ከቀጣዩ ማስታወቂያ በሁዋላ መልሰን በሌላ ማስታወቂያ እንገናኛለን።
የማለዳ ድባብ የተባለችው መጣፌ እሁድ ጁላይ2- 2pm ላይ በሲልቨር ስፕሪንግ 1 veteran pi ትመረቃለች። ጁላይ 4 ሲያትል ገብቼ እፈርማለሁ።
እንዲሁም ባዲሳበባ
ማስመረቄ አይቀርም መስከረም ሳይጠባ😊😉
ዲያስፖራ እህቶቸና ወንድሞቸ! ወዳገሬ እስክመለስ ላንድ ወር የሚቆይ ስራ ፈልጉልኝ። ሁለት የፈረንጅ ዶሮ እንቁላል ባንድ ያበሻ ዶሮ እንቁላል እለውጣለሁ። የኢትዮጵያን እንጀራ ካሜሪካ እንጀራ የመለየት አገልግሎት እሰጣለሁ። ህፃን ልጅ እጠብቃለሁ። በየቪድዮ ጌሙ አሰማራለሁ። አቡጊዳና አባጫዳ አስተምራለሁ። ቤት የዋለች አሮጊት ጋሪ እነዳለሁ። አንድ ሀሙስ ለቀረው አሮጌ ፈረንጅ: ሞት አለማምዳለሁ።
አንድ ሁለት ሶስት ወደ ቁምነገሩ!
“የማለዳ ድባብ” ሽፋን ላይ የሚታየው ምስል የተገኘው በንጉስ ሳህላሴ ዘመን ሸዋን ከግር እስከራሱ የመረመረው ጀርመናዊ ሰአሊ መዝገብ ውስጥ ነው።
ከስእሉ ውስጥ እኔን በቀጥታ የሚመለከቱኝ የ”ፅና”እና “የድባብ “ምስሎች ናቸው።
“ፅና “
ማጠኛ ማለት ነው። የገዛ ግጥሞቼን ሳነባቸው ባፍንጫየ አስቤ የፃፍኩዋቸው ግጥሞች ጥቂት አለመሆናቸውን ተረዳሁ።ሳስበው ባገራችን ባህል ላፍንጫ የሚሰጠው ቦታ ከፍተኛ ነው። ሌላው ቢቀር ቡናን አስቡት! በዘመናይ አሜሪካና አውሮፓ ቡና ይጠጣል እንጂ አይሸተትም። ይምጣብኝ አገርቤት!!ከህዋሶቻችን ማሃል: የቡና በረከት አስቀድሞ የሚደርሰው ለአፍንጫችን ነው። ቡና አፍይዋ እየዞረች ለታዳሚው የቡና ማእዛ ታድላለች። ከዚያ ደሞ እጣን አለ። ባገር ቤት እጣን ሲጨስ ቆሌ ይቀርባል።በጎ መንፈስ ከተፍ ይላል ይባላል። አሜሪካ ቤትህ ውስጥ እጣን ብታጨስ ከተፍ የሚለው ፖሊስና የእሳት አደጋ መኪና ነው። ወትሮስ ውቃቤ ከራቀው አገር ተዚህ በላይ ምን ይጠበቃል?
ባገሬ መቅደስ ይታጠናል። ጋን ይታጠናል። አስከሬን ይታጠናል። አልፎ አልፎ ብልትም ይታጠናል። ባንዳንዱ የገጠር መንደር በሴቶች እግር ማሃል የምትቀመጥ ቦለቂያ የምትባል ማጠኛ እንዳለች አውቃለሁ። ወይዛዝርቱ እየተዋዋሱ ይቀመጡባታል። “የስንቱን አየን! አለች ቦለቂያ”ይል ነበር ገጣሚው ሙሉጌታ ተስፋየ ።
ስለውበት ሽታ -ስለ ሞት ሽታ -ስለ ናፍቆት ሽታ -ስለ አዲሳባ ሽታ የፃፍኩት ሁሉ በስእሉ ውስጥ በሚታየው ማጠኛ ይወከልልኝ ።
“ድባብ”
ያማርኛ መዝገበቃላት ድባብን”ጃንጥላ የሚደበብ የሚዘረጋ የሚጠቀለል ጌጥና ሽልማት ያለው” ብሎ ይተረጉመዋል።
በዘመናይ ኑሩዋችን ጃንጥላ የሚያገለግለው ከዝናብና ከፀሃይ ራስን ለመከላከል ነው። በቀድሞ አገልግሎቱ ግን የጃንጥላ የክብርና የስነውበት ምልክት ነበር።
የመፅሃፌ አጠቃላይ መንፈስ በሚከተሉት ስንኞች ሊጠቃለል ይችላል።
ጎህ ገስግሶ
ደርሶ
ፅልመት ቢያባርርም
የማለዳ ድባብ: ህብሩ ገፁ ቢያምርም
ሰው ፀሃይን አምኖ: ፋኖሱን አይሰብርም።
4 Comments
Interesting review. [Link deleted]
[Link deleted]
Thanks. [Link deleted]
Interesting link to review.
[Link deleted]