Tidarfelagi.com

ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያዊነት፣ ሀገር ግንባታ

የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ‘ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በአማርኛ ሥነ ፅሁፍ’ በሚል ርዕስ ባዘጋጀው መድረክ ላይ ተባባሪ ፕሮፌሰር ቴዎድሮስ ገብሬ፤ የጸጋዬ ገብረመድህንና የአዳም ረታን ስራዎች ዋቢ በማድረግ ስለ ብሔርተኝነትና ሀገር ግንባታ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል።
የጥናታዊ ፅሑፉ ጨመቅ (Summary) ለንባብ እንዲመች ተደርጎ እንደሚከተለው ቀርቧል።
***
#ብሔርተኝነት_Nationalism_እና_ውክልና
ብሔርተኝነት፤ የሀሳብ፣ የእምነትና የመርህ ጣጣ ነው። እነዚህ ሶስት ጉዳዮች ረቂቅ ናቸው። ሜታፊዚካል ናቸው። ስለዚህ ውክልና (Representation) ይፈልጋሉ።

ውክልና በኪነት ወይንም በስነ ጽሁፍ ውስጥ ሁለት መልክ አለው። አንደኛው መወከል ነው። የተጠራ አለ፣ ያልተጠራ አለ። ሁልጊዜም የሀገር ግንባታ (Nation Building) የሚያከራክረውና ብሔራዊ ሚት (National Myth) የሚያስፈልገው፤ ያልተወከለ ወገን ወይንም ሰብዓዊ እሴት ስለሚኖር ነው። ጠንቅቀን አደረግን ብንል እንኳን አዲስ ትውልድ ሲመጣ አዲስ እሴትና አዲስ ፍላጎት ይዞ ስለሚመጣ ማደስ ያስፈልጋል። ይሄን ለመስራት ስነ ጽሁፍ ጥሩ አውድ ይሰጣል። ለምሳሌ የስንብት ቀለማት ላይ አዳም ነባሩን የሳባ-ሰለሞን ሚት ያፈርሳል። ገፀ ባህሪው ስንዝሮ ጊዜን ይገፋል። አምስት ሺህ አመት ስለኖረ ከማክዳ ከሳባ የሚቀድም ታሪክ አለው። በታሪክ ውስጥ የምታውቃቸውን ጉልሃን ሰዎች፤ ለምሳሌ ቅዱስ ያሬድን ይወስድና ሃይማኖታዊ ቀለሙን ቀይሮ ስንዝሮ ያስተማረው አንድ ጎበዝ ሙዚቀኛ ያደርገዋል። ፀጋዬና አዳም የ ውክልና (Representation) ጥያቄ የሚያስነሱ ጉዳዮችን አፍርሰው ሌላውን በሙሉ ሊወክል በሚችል መልኩ ይሰሩታል።

ሁለተኛው የውክልና ፈርጅ፤ አስተማስሎ የሚባለው ነው። አስተማስሎ ማለት፤ ረቂቅና ውስብስብ የሆኑ ሃሳቦችን በምስል ማቅረብ ማለት ነው።
#የኢትዮጵያ_ብሔርተኝነትና_የከያኒያን_ሚና
ከሃምሳዎቹና ስድሳዎቹ ጀምሮ የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ታውኳል። እስካሁንም እንደታወከ ነው። ብዙ ጥያቄዎች ተነስተውበታል። ብዙ እሴቶች አጥፍቷል። ባጠፋቸው እሴቶች ምትክ አዲስ እሴት አልገነባም። ትውልድ ተለዋውጧል። ነባሩ ትውልድ በነቀለው እሴት ምትክ አዲስ ስላልገነባ፤ አዲሱ ትውልድ ያለ እሴት ነው የተቀመጠው።

ነባር እሴቶች ይወደዳሉ (Romanticize) ይደረጋሉ። እነዛ እሴቶች ላይ ነው ብሔርተኝነቱ የተመሰረተው። በሃምሳዎቹና ስድሳዎቹ ሮማንሱ ሲፈርስ፤ አብሮ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነቱም ፈርሷል። አዲሱ ትውልድ አዲስ ብሔርተኝነት (Nationalism) ያስፈልገዋል። ይሄን የሚሰሩለት ደግሞ ከያንያን ናቸው። የሌላ ሀገራት ልምድ ብናይ ከያንያን በዚህ ረገድ ስኬታማ ናቸው። እኛ ጋር ግን አይደሉም።
ለምን?
የቋንቋ መብዛት እርግማን ሆኖብን ይሆን?
እንደዛም እንዳይባል፤ ፓፑዋ ኒው ጊኒ የምትባል ሃገር 3 ሚሊየን ሕዝብና 700 ገደማ ቋንቋ አላት። ነገር ግን በሕብረት (In Harmony) ነው የምትኖረው።

ሕንድ፤ ከአንድ ሺህ በላይ ቋንቋና ከአራት በላይ እዛው የበቀሉ ሃይማኖቶች አሏት። እምነት ላይ የተመሰረት የካስት ስርዓት (Caste system) አላት። ሕንድም በግጭትና በመከፋፈል የታወቀችበት ጊዜ ነበር። ታጎር (Tagore) የሚባል ሰው ነው የዋጃት። የህንድን መንፈስ (Indian Soul) የሚባለውን የሰራው ታጎር ነው። ታጎር በስነ ጽሁፉ አማካይነት ከሰውና ከታሪክ በላይ (Transpersonal & Transhistorical) ሆኗል። ስኬታማ ነው። እነሱ ጋር የተፈወሰው የቋንቋ በሽታ እኛ ጋር ለምን አልተፈወሰም?
የዛሬ 80 አመት ሕንድ በግጭት የታወቀች ነበረች። አሁን ሕንድ የአለምን ኢኮኖሚ እና አውሮፓ ተኮር (Euro Centric) የሚባለው የሚጫነውንና “Global South South” የሚባለውን ንቅናቄ የምትመራ ሀገር ነች። እዚህ ውስጥ የ ታጎር እጅ ትልቅ ነው።

እኛ ሀገር የ ታጎር አይነት ሰው ጠፋ ወይ?
#የአማርኛ_ስነ_ፅሑፍ/ #የኢትዮጵያ_ስነ_ፅሑፍ_
የኢትዮጵያ የስነ ጽሁፍ ቀኖና (Literary Canon) ብንሰራ ከላይ ከሚቀመጡት ሰዎች ውስጥ እንደ ስብሃት፣ ጸጋዬ፣ በዓሉና ሰለሞን አፋቸውን የፈቱት በአማርኛ አይደለም። ግን ለምን በአማርኛ መጻፍ መረጡ?
የባህል ጭቆና (Cultural Dominance) ጣጣ ሆኖባቸው አይደለም። ወይንም ሰፊ የሆነ አንባቢ ፍለጋ አይደለም። እነዚህ ከያኒያን በእንግሊዝኛ እና በፈረንሳይኛ ጥሩ አድርገው ይጽፋሉ። በነዚያ ቋንቋዎች ቢጽፉ ሰፊ የሆነ አንባቢ ማግኘት ይችሉ ነበር። ግን አላደረጉትም። በነዚህ ሰዎች አማካኝነት የአማርኛ ስነ ፅሁፍ የ ኢትዮጵያ ስነ ፅሁፍ መሆን አይችልም ወይ?

የብሔርተኝነት ጉዳይ የቋንቋ ጉዳይ ነው ካልን፤ እዛ ውስጥ የሀገር ግንባታ ፕሮጀክት የለም ወይ? እሱን ሳናነብ ሀገር መገንባት እንችላለን?
ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት (Ethiopian Nationalism)ን ለመገንባት pop culture, literary art እና ሌላውም የጥበብ ስራ መስራት አለበት።
በፖለቲካ ዲስኩር መስራት አይቻልም። ፖለቲካ ሊሰራ የሚችለው ሀሳብን በሃሳብ ማስረዳት ነው። ጥበብ ግን ሃሳብን ፈርክሶ፣ ቀለም እና ቅርጽ ኖሮት ሰው እንዲኖርበት አድርጎ ነው የሚሰራው።

#በሀገር_ግንባታ_ውስጥ_ፀጋዬና_አዳም_በንጽጽር
ሁለቱም ጥልቅ የሆነ ጊዜና ሚታዊ እሳቤ (Mythical Thinking) አላቸው።
ሁለቱም የተቃራኒዎች መቃለጥ (Fusion of Opposites) ላይ ይመሰረታሉ።
ልዩነታቸው

#1
ጸጋዬ ተሰርቶ ያለቀ ትዕምርት (Symbol) ይፈልጋል። የጸጋዬ ተረክ ወይንም ብሔራዊ ሚት ሙከራ በግዙፋን እሴቶች ላይ፤ ለምሳሌ በአባይ፣ በአዋሽ፣ በምኒልክ፣ በዓድዋ፣ በቴዎድሮስና በዘርዓይ ታሪክ ላይ ይመሰረታል። እዛ ላይ ተመስርቶ የሚፈልገውን ይሰራል።
ጸጋዬ ሕሩያንን እና ጉልሃንን ነው የሚፈልገው። አዳም ያን ይሽርና በጥቃቅን ነገሮች ላይ ይመሰረታል። ወደ ምድር ይመጣል።
ጥቃቅን ሲባል በማሕበራዊ ሕይወታችን ውስጥ ስፍራ የማንሰጣቸውን ባህሪያት (Values) ነው ወደ ማዕከል የሚያመጣው። ለምሳሌ ጀግና (Hero) መፍጠር ሲሞክር ጀግናውን ቴዎድሮስ ወይንም ምኒልክ ሳይሆን ሁሌ ከምንሰማው ተረት ወይንም ተንኮለኛ ከሆነ ገፀባህሪ ስንዝሮን ይመለምላል። እና ተንኮለኛ ባህሪውን ያራግፋል። ስም ይቀይርለትና ሚታዊ አካል (Mythic Figure) ያደርገዋል። ከማይረባ የተረት figure ወደ mythic figure ይቀይረዋል።

ስንዝሮ ረዥም ታሪክ አለው። ወደኋላ አምስት ሺህ አመት አለው ወደፊትም ብዙ ዘመን ይገፋል። የነባሩ የሰለሞን-ሳባ ሚት ፅንፍ የለሽ የኋላ ተረክ (Immemorial Past) እንጂ የወደፊት ትልም አልነበረውም። ጸጋዬም አዳምም ሲሰሩ ይሄንን የወደፊት መንገድ (Future) ያስባሉ። የተረጋገጠም (Guaranteed) ነው።
ጸጋዬን ጨምሮ ነባር ከያኒያን ጀግና (Hero) ሲሰሩ የሚመርጧት እናት በተለመደው የእንስታዊነት ባህሪ (Feminine Value) የተሟላች መሆን አለባት። ንጹህ ቦታ የተገኘች፣ ከማሕጸን ጀምሮ የተጠበቀች መሆን አለባት። የአዳም ገፀ ባህሪ ግን ጉልት ላይ የምትውል፣ እግሯ ንቃቃት የተሞላ፣ ከነባሮቹ ባሮች የከፋ ድህነት ያላት ይሆንና እሷም ግን እንደነባሮቹ በድንግልና ትወልዳለች።
ጸጋዬ አባይን ይጠልፍና ከአባይ የኢትዮጵያዊ ማንነትን ያሰግራል። አባይ ትልቅ ነው፣ አባይ ጠንካራ ነው። አዳም ደግሞ ጤፍን ይወስዳል። ጤፍ ማለት ከሰብሎች ሁሉ ትንሿ ነች። ከዚህች አንድ ፍሬ ጤፍ አብራክ (ልብ በሉ ጤፍ አብራክ ሲኖረው) እንጀራ እንደሚከፈለው ሁሉ፤ አዳም ኢትዮጵያዊነትን ከዛ ሊከፍል ይሞክራል።

#2
ጸጋዬ በአቋሙ ወጥ (consistent) ነው። በሃምሳዎቹና ስድሳዎቹ ሃገር በታመሰ ጊዜ ጸጋዬ ከሮማንሱ አልወጣም። የጸጋዬ ኢትዮጵያ ከምድር በላይ ነች። አትለወጥም።

አዳም እስከ 1983 ድረስ በ አለም አቀፋዊ ሰብዓዊነት (Universal Humanism) የሚያምን ሰው ነው። የሰው ልጅነትና የሰው ልጅ ዕጣ ፈንታ ነው የሚያሳስበው። ነገረ ሰብ (Human Condition) ነው ጉዳዩ።
ከ 83-85 ለውጥ በኋላ፤ ቻርተር ሲጸድቅ፣ ሌሎች የምናውቃቸው ነገሮች ሲፈጠሩ በአስተሳሰብና በአካሄድ ለውጥ አደረገ። በፊት ሲሰራ ሚት ይሰራል። የሚገለገልበት ሚት ግን አለምዓቀፋዊ ስብዓዊነት (Universal Humanism) ሊወክል የሚችል ሚት ነው። ለምሳሌ፤ እንቁላል። Cosmic Egg ከሚባለው ሚት የሰው ልጅን ዕጣ ፈንታ ይነድፋል። እሱን ነው ትቶ የመጣው።
ይሄን ትዕምርት (Symbol) መተዉ መዓት ነገር ይለውጣል።

አንደኛ፤ ለትችት ይዳረጋል። አፍሪካውያን የምዕራባውያኑን ሃሳብ መተው ሲፈልጉ የዚያን ነገር አቻ እዚህ ማግኘት አለባቸው። እዚህ ካላገኙት ያንሳሉ። እና በባዶ አርበኝነት (Superficial Nativism) ይተቻሉ። አዳም እዚያ ውስጥ ላለመውደቅ ማጥናት ነበረበት።
አዳም ታዋቂ ከመሆኑ በፊት ሰላሳ ምናምን አመት ሰርቷል። ሲያጠና ያገኘው በእንቁላል ፈንታ ጤፍን ነው። ጤፍ በብዙ መንገድ ለ ኢትዮያጵያዊ ብሔርተኝነት ጥሩ የሆነ ትዕምርት ነው።
አንደኛ፤ ጤፍ ውስብስብ (Racially Complex) ነው።

ሁለተኛ፤ ጤፍ ፍናፍንታዊ (Sexually Hermaphrodite) ነው።

ሶስተኛ፤ ጤፍ በዕድሜ ሩቅ ነው።

አራተኛ፤ ጤፍ ስሙ የመጣው ‘ጠፋ’ ከሚለው ነው። ነገሯ ራሷ ትንሽ ነች። ጠፋ ማለት (Absence) ነው። በፍልስፍና አይን ቢታይ ጤፍ የምትባለው ነገር ራሷ የምትወክለው አለመኖርን (Absence) ነው። ያለመኖር መኖር (The Presence of Absence)
አለመኖር ሚታፊዚካላዊ ነው። በኛ አውድ ግን፤ ጤፍ የምትወክለው መኖርን ሳይሆን አለመኖርን ነው። ገበሬው አለመኖርን ይዘራል፣ ያጭዳል። ሴቶች ደግሞ ከዚህ ያለመኖር እንጀራን ያህል ነገር ይጋግራሉ።

እና እኛም ስንመጣ ካለመኖር ነው። ይሄ ሚታዊ መሰረት አለው። ምክኒያቱም ሁሉም ሚቶች የመጀመርያዎች ሁሉ መጀመርያ (The beginning of all beginnings) መሆን ይፈልጋል። መነሻ መሆን ካለበት ደግሞ ከእመ አልቦ (Ex Nihilo) መምጣት አለበት።
አዳም እመ አልቦን በጤፍ አማካይነት ሰራ።
ጤፍ ብዙ ነገር ነው። 70% ኢትዮጵያዊ ጤፍ እንደሚበላ ጥናቶች ያሳያሉ። በስፍራም፣ በጊዜም፣ በውክልናም አስቡት። በየትኛውም መንገድ ጤፍ ጥሩ ትዕምርት ነው።

#3
ጸጋዬ ብሔራዊ ሚት ሊሰራ ሲፈልግ የጋራ ጠላት (Common Enemy) ይመለምላል። የጋራ ጠላት በብዙ ብሔራዊ ሚቶች እና ብሔራዊ ስነ ፅሁፎች ውስጥ መሰረታዊ ጉዳይ ነው። ምክኒያቱም የውጪ ጠላት ሲመጣ ወደ አንድ ይሰበስበናል። ስለዚህ ለ ሀገራዊ ማንነት ጥሩ ነገር ነው። ‘ቴዎድሮስ’፣ ‘ምኒልክ’፣ ‘ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት’ ወዘተ በዚያ መንፈስ ነው የተሰሩት።
አዳም ከዚህ ተቃራኒ ነው። የኛ ጠላት ራሳችን ነን። እንደ ማሕበረሰብም እንደ ግለሰብ አንድ አካል የሁለቱም ማደሪያ ነው። ስለዚህ ራሳችንን እንድናሸንፍ ነው የሚያደርገው።
***
የብሔርተኝነት ጉዳይ የጊዜ ጥልቀት (Time Depth) ይፈልጋል። ጸጋዬና አዳም የጊዜ ጥልቀት ሰርተዋል። ፀጋዬ ‘አባይ’ በሚለው ግጥሙ የጥንታዊ ግብፅ ቃላትን ወደ አማርኛና ኦሮሚኛ እየቀየረ ይፅፋል። ለምሳሌ ‘ፒያንኬ’ የሚለውን የግብፆች ቃል “ቢያ ሃንኬ” ወደሚል የኦሮሚኛ ቃል ይለውጣል። ‘አበሲምበል’ የሚለውን የጥንታዊ ግብፆች የመቃብር ቦታ ስያሜ “አበ ሲምቦል” (የሲምቦሎች ሁሉ አባት) በማድረግ አባይን የ ትዕምርቶች ሁሉ ትዕምርት ያደርገዋል።

አዳምም ‘በለስ’ በሚለው አንድ ታሪኩ ውስጥ ተመሳሳይ የጊዜ ጥልቀት ይሰራል። ለምሳሌ ምዕራባዊያን የእውቀት ፍሬዋን Apple ነች ይላሉ። Apple ሴክሹዋል ነው። እነ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ይህችን የተከለከለች ፍሬ ‘በለስ’ ያደርጓታል። በለስ ይሉና ‘በለሶም፣ ወተታም ፍሬ’ እያሉ ይፈቱታል። ‘እናታዊ’ (Motherly) ይሆናል። መፅሀፍ ቅዱስ ውስጥ የተከለከለ ፍሬ የሚለውን በአካባቢህ material ትሞላዋለህ። እኛ ያለን በለስ ነው። አዳም ረታ በለስን ይወስድና ውሥጡ ጤፍ ይከትበታል። እዛ ታሪክ ውሥጥ አዳም ከጤፍ የተሰራውን የበለሷን ፍሬ ከበላ በኋላ መገለጥን (Discovery) ያገኛል። ከባቢውን መረዳት (Cosmic Consciousness) ይጀምራል።
አዳም ረታ ይሄን የሚያደርገው Time Depth ፍለጋ ነው።

የጊዜ ጥልቀት (Time Depth) ካለው እዛ ላይ የሚተከል ብሔርተኝነት የሚነቃነቅ አይደለም። ብሔራዊ ማንነቱም ጽኑ ነው። የሰሩበት ግብዓት ደግሞ ከየትም ቦታ የመጣ ሳይሆን ሀገር በቀል ነው።

ለአዳም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በጊዜ ውስጥ አይደለም የተፈጠሩት። ከጊዜ ጋር አብረው ነው የተፈጠሩት።
ከጊዜ ጋር ከተፈጠሩ አንደኛ በAnderson ቋንቋ በጣም ሩቅ የሆነ (Immemorial Past) አላቸው። ሁለተኛ፤ የማይገመት (Unpredictable Future) አላቸው። የጊዜውን ጽንፍ በሚገባ ይዘውታል።

ይሄ ለሀገር ግንባታ ለም የሆነ አፈር ነው።
***

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *