Tidarfelagi.com

እምዬ ያልታደለች

እምዬ ያልታደለች
ተመዘኚ ሲሏት— መዛኝ ነኝ ትላለች
እምዬ ሰከረች
ልትመዘን ወጥታ — መዛኝ ሆና ቀረች!

የቅቤን ስብራት — በቅመም ለማከም
በወቀጣ መዛል — በድለዛ መድከም
የቅቤን ወለምታ — በቅመም ለማሸት
ሲደቁሱ አድረው — ሲቀይጡ ማምሸት
የቅቤን ጉብዝና — በቅመም ለማትጋት
እያመሱ መዋል — እየፈጩ ማንጋት
* * *
ይልቅ ግድ የለሽም !
ለቅቤ ጥፍጥና
ለቅቤ መአዛ
ቅመም ከመደቆስ —ቅመም ከማበጠር
ከቅቤያችን በፊት —ከብቶቹን ነው ማንጠር
እንስራ ወዝውዞ
በጢሳጢስ ናውዞ
ለቅቤ ከማማጥ —ለአይብ ከማማጥ
ከወተቱ በፊት — እስቲ ላሟ ትናጥ
ማለቢያ ከማስፋት —ማለቢያ ከማጥበብ
ከግቷ አስቀድሞ
ከሆዷ አስቀድሞ —ምግቧን ነው ማጠብ
* * *
ለምሽቱ ድምቀት — ቀኑን ሳይበርዙ
እንዲህ ነው ፊተኞች — ‘ሩቅ የሚጓዙ
እንዲህ ነው መስማማት — መግባባት ከዛፉ
ከስር ሳይመትሩ — አይታይም ጫፉ !
* * *
ግራ ነኝ ይለኛል
ቀኝ ነኝ ይለኛል —መሀል ነኝ ይለኛል
ዳሩ ካልተያዘ — መሀል የት ይገኛል?
እውቀት አባ አያልቄ
እውቀት አባ አይፈሬ —ጥያቄ ሲያድለው
ለግራም የራሱ — ግራና ቀኝ አለው
ለቀኝም የራሱ — ቀኝና ግራ አለው
መሃልም ለራሱ — ሌላ መሀል አለው
* * *
እይዉ!
ሰው መጠየቅ ትቷል
ሰው ፍለጋ ትቷል —ሰው ማጣጣም ትቷል
ለመንስኤ ዝሏል —ለአመክንዮ ታክቷል
በጥድፊያ ሊያስታግስ —የመሰንበት ሱሱን
ጥያቄ ነው ይላል —የከሸፈ መልሱን
ነፍስያን ተብትቦ —በስሜት ሰንሰለት
መቀያየጥ ሆኗል —መጠያየቅ ማለት
መመሳሰል ሆኗል —መመላለስ ማለት
* * *
ኩሬ ነው?
ወንዝ ነው?
ሃይቅ ነው?
ባህር ነው? ጎርፍ ነው?
ገባሩ? ጅረቱ? ማእበሉ? ምንጮቹ?
አዞ አለ? አሳ አለ?
.
.
.
እኮ የምን ጥያቄ ! እኮ የምን ክርክር !
በቃ!
“ዋና ነው!” ይልሽና ከነልብሱ ንክር።
አዎ!
“ዋና ነው!” ይልሻል “አጨብጭቢ!” ይልሻል
“ዋናህስ?” አትበይው
አሽሟጠጠች ብሎ — ችሎት ያቆምሻል
ያው!
ችሎቱ የእነሱ —ችሎታው የሌላ
ይልቅ አጨብጭቢ —አዞ እራቱን ይብላ!
ለንክር ጭብጨባ —ለዝፍዝፍ ጭብጨባ
ሆዱ አሳ ሲለው — አዞ ለሚያረባ
* * *
ተመልከች!
ሽንቁራም እውቀትሽ —ንፋሱን ሲነዛ
ከጋላቢሽ ይልቅ —የሚገለብ በዛ
ንፋሳም እውቀትሽ —ውርጩን እየነዛ
ከሚያነደው ይልቅ —የሚያከስለው በዛ
ግልብልብ እውቀትሽ —ወላፈን ደሞዙ
የሚለበለቡት — ከሚበስሉት በዙ።
እይው!
ማእዘን አፍርሶ —ግድግዳ እያደሰ
ወለሉን ሰውቶ —ጣሪያ እየቀለሰ
ቅርንጫፍ ሊያሳምር —ስር እየበጠሰ
እልፍኝ ተደፈረ —አጥር ተገሰሰ
መስማት ጥንቡን —ጣለ ማየት ረከሰ
ቋንቋ መነመነ — ለትርጉም አነሰ
* * *
ቆይ እኔ የምልሽ!
ተፈጥሮ ሂደቷ — እንዲህ ሳይጓደል
ለመሮጥ መንደርደር — ግድ ነበር አይደል?!
ታዲያ! ቀረ እኮ ነው ‘ምልሽ
መንደርደር መመርመር መፈከር መዘርዘር
አኩርፈው የሄዱት — በየት በኩል ነበር?
* * *
የወል ቀማሽ ሁላ
ድፍርስ እየጠጣ — ሽርክት እየበላ
በግርድፍ አኝኮ — ለግርድፍ ተሻምቶ
“ውጫለሁ!” ይልሻል — ወደ ሆዱ ተፍቶ
* * *
የምር ደስ አይልም!
የጥርስን በአንጀት
የጆሮን በምላስ — ʻያፍንጫን በመዳፍ
ግብር እያቀማሙ — ዋጋና ስም መጻፍ
የምር ደስ አይልም!
የልብን ደረት ላይ
የነፍስን ልብስ ላይ— ቀያይጦ በማፍካት
ጣእምን መመርመር — ውበትን መለካት
ደስስስስስ አይልም!
* * *
እምዬ!
አትላፊ አትዳሪ ከእንክርዳድሽ
ይልቅ
ወንፊት ግዢ ለወንፊትሽ
ሰፌድ ግዢ ለሰፌድሽ
* * *
ቀማሽ ሲደራረብ —ጣእም ተቀያየጠ
ባለቤት ሳያጌጥ —ውበት አመለጠ
ከእህሉም አይደለ
ከቅመሙም አይደል
ጨው አንሶም አይደለ
የምላስ ህመም —ነው ጣእም የገደለ
* * *
ምን አረገሽና!
ቀቃዩ ጠባሹ
ከታፊው አማሹ
ወቃጩ ነስናሹ
ለርካሽነትሽ — ይጠየቅ ቀማሹ
ማገዶ ቢራቀቅ
ምጣድ ቢቀያየር — ጋጋሪ ቢንጋጋ
በቀማሽ ልክ ነው —የገበታሽ ዋጋ
* * *
ኧረ ሚዛን! ሚዛን!
ኧረ መዛኝ! መዛኝ!
በልክ የሚሰፍር በልክ የሚገዛኝ!
እንደየቃናችን — ማድመቅ ያላወቀ
ቀማሽ አሳነሰን — እያደባለቀ!!!

2 Comments

  • wondwosson commented on June 8, 2019 Reply

    # the great one!!!!

  • የኔሰው commented on December 17, 2019 Reply

    በረከታችን ነህ !!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *